ሪፖርት | ሀዲያ ሆሳዕና የዓመቱን የመጀመርያ ድል አሳክቷል

በሰባተኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በሜዳው አቢዮ ኤርሳሞ መታሰቢያ ስታዲየም ሲዳማ ቡና ያስተናገደው ሀዲያ ሆሳዕና 2- 1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የሊጉ የመጀመርያ ሦስት ነጥቡን አሳክቷል።

ሀዲያ ሆሳዕና በኢትዮጵያ ቡና ከተሸነፈው ስብስቡ የሁለት ተጫዎች ለውጥ በማድረግ ትዕግስቱ አበራ እና አብዱልሰመድ ዓሊ በማስቀመጥ ፀጋሰው ዲማሞ እና በኃይሉ ተሻገርነረ ሲያሰልፍ ሲዳማዎች በበኩላቸው ከድሬዳዋ ከተማ በሜዳው ሽንፈት ካስተናገደው ስብስባቸው አማኑኤል እንዳለ፣ ሰንደይ ሙቱኩ፣ አበባው ዮሐንስ እና ሚካኤል ሀሲሳን በማሳረፍ በተስፉ ኤልያስ፣ ዮሴፍ ዮሐንስ፣ ጊት ጋትኮች እና ዳዊት ተፈራ ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ፌደራል ዳኛ ኢብራሂም አጋዥ በመራው በዚህ ጨዋታ የመጀመርያው አጋማሽ በሁለቱም ቡድን በኩል በማራኪ እንቅስቃሴ የታጀበ ፉክክር ተስተዋለበት ሲሆን በባለሜዳው ቀዳሚ የሚያደርገውን ግብ ፍለጋ ተጭኖ ተጫውቷል። በተቃራኒው ሲዳማ ቡና ፈጣን አጥቂዎቹን በመጠቀም ኳሶቹን በማሻገር ጥንቃቄ የተሞላበት እንቅስቃሴ አድርገዋል።

በመጀመርያው ደቂቃ ወደ ተጋጣሚያቸው የጎል ክልል በመድረስ ይገዙ ቦጋለ ባደረገው የግብ ሙከራ ጥቃት የሰነዘሩት እንግዶቹ በመስመር በሚሻሙ ኳሶች ቶሎ ቶሎ ለመድረስ ቢሞክሩም በመጀመሪያው አጋማሽ ከይገዙ ሙከራ ውጪ ይህ ነው የሚባል የጠራ የግብ እድል ሳይፈጥሩ ቀርተዋል።

በአንፃራዊነት የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ይዘው መጫወት የቻሉት ባለሜዳዎቹ መልካም የጎች አጋጣሚዎችን መፍጠር ችለው ነበር። በተለይም ሱራፌል ዳንኤል ወደ ጎል አክርሮ የመታውና በግብ ጠባቂ መሳይ አያኖ ቁጥጥር ስር ዋለችው እንዲሁም በደስታ ጊቻሞ እና በይሁን እንደሻው አማካኝነት ያደረጓቸው የጎል ሙከራዎች ተጠቃሽ ነበሩ።

ሀዲያ ሆሳዕናዎች ጫና መፍጠራቸውን ቀጥለው በ37ኛው ደቂቃ ላይ ከመስመር የተሻገረውን ኳስ ሱራፌል ዳንኤል በግንባሩ በመግጨት ባስቆጠረው ጎል መሪ ሆነው የመጀመርያው አጋማሽ ተጠናቋል።

እንግዶቹ ሲዳማ ቡናዎች ሙሉ ለሙሉ በሚያስብል መልኩ ተሽለው በታዩበት ሁለተኛው አጋማሽ በቁጥር በርካታ የግብ ሙከራዎች በሁለቱም ቡድን አስመልክቷል። በተለይም በ65ኛው ደቂቃ በሀብታሙ ገዛኸኝ የግንባር ኳስ ለአቻነት ተቃርበው የነበሩት ሲዳማዎች በሁለቱንም መስመሮች የሚፈጥሩት ጫና ፍሬ አፍርቶ በ69ኛው ደቂቃ አቻ ሆነዋል። ከ16:50 ውጭ አማኑኤል እንዳለ አክርሮ የመታው ኳስ ከመረብ አርፎ ነበር ሲዳማ አቻ መሆን የቻለው።

ሆኖም የሲዳማ አቻነት ጎል ብዙም አልቆየም። በፍጥነት ወደ መሪነታቸው ለመመለስ ምላሽ ለመስተጥ የተንቀሳቀሱት ነብሮቹ ከአራት ደቂቃዎች በኋላ መሪነታቸውን በቢስማርክ ኦፖንግ አማካኝነት ማግኘት ችለዋል። ከሄኖክ አርፊጮ የተሻማው ኳስ በሳጥን ውስጥ በተጫዋቾች ከተነካካ በኋላ ጋናዊው አጥቂ አግኝቶ ነበር ወሳኟን ጎል ያስቆጠረው።

ከጎሉ በኋላ በሁለቱም በኩል ጥሩ የጎል አጋጣሚዎች የተፈጠሩ ሲሆን በተለይም በሆሳዕናዎች በኩል ፍራኦል እና በቢስማርክ አፒያ ከሳጥን ውጭ አክርረው በመምታት ያደረጓቸው ሙከራዎች ይጠቀሳሉ። ጨዋታውም ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠርበት በሆሳዕና 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ ምንም እንኳ ከግርጌው ባይላቀቁም በአዲሱ የውድድር ዓመት የመጀመርያ ሦስት ነጥባቸውን ማሳካት ሲችሉ ሲዳማዎች በአንፃሩ ሁለት ተከታታይ ሽንፈት በማስተናገድ ወደ ስምንተኛ ደረጃ ወርደዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ