ሪፖርት | ምዓም አናብስት ወደ አሸናፊነት ተመልሰዋል

በ7ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አዳማ ከተማን በትግራይ ስታዲየም ያስተናገዱት መቐለ 70 እንደርታዎች 2-0 በማሸነፍ ደረጃቸውን አሻሽለዋል።

መቐለዎች በቅዱስ ጊዮርጊስ ሽንፈት ከገጠመው ስብስብ አንተነህ ገ/ክርስቶስ (ቀይ) እና ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስን በሄኖክ ኢሳይያስ እና አሸናፊ ሀፍቱን ተክተው ሲገቡ አዳማዎች ከጅማ አባጅፋር አቻ ከተለያየው ስብስብ ደረጄ ዓለሙ፣ መናፍ ዐወል እና ብሩክ ቃልቦሬን አስወጥተው በጃኮ ፔንዜ ፣ የኃላሸት ፍቃዱ እና ቴዎድሮስ በቀለ ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።


ተመጣጣኝ ፉክክር እና ጥቂት የግብ ሙከራዎች በታዩበት ጨዋታ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ጥሩ የመሸናነፍ ፉክክር የታየበት ነበር። ዳዋ ሆቴሳ ከቅጣት ምት ባደረገው ሙከራ የጀመረው ጨዋታው መቐለዎች ገና በሦስተኛው ደቂቃ በአማኑኤል ገ/ሚካኤል ግብ አስቆጥረው እንቅስቃሴው ከጨዋታ ውጭ ነበር በሚል ተሽሮባቸዋል።

በቀጥተኛ አጨዋወት በርካታ የግብ ዕድሎች የፈጠሩት መቐለዎች በጨዋታው ጥሩ እንቅስቃሴ ባደረገው ጃኮ ፔንዜ ተመልሶባቸዋል። በተለይም አማኑኤል ከያሬድ ከበደ የተሽገረለትን ኳስ መቶ ግብ ጠባቂው የመለሰበት እና አማኑኤል ገ\ሚካኤል ከጃኮ ፔንዜ አንድ አንድ ተገናኝቶ ግብ ጠባቂው በድጋሜ የመለሰበት ኳስ በግዙፉ ግብ ጠባቂ ጥረት የመከኑ ዕድሎች ናቸው። በአማኑኤል በውሳኔ አሰጣጥ ችግር ሁለት ሙከራዎች አድርገው ወደ ግብነት መለወጥ ያልቻሏቸው ሙከራዎችም የሚጠቀሱ ነበሩ።


በአጋማሹ ጥሩ እንቅስቃሴ ከማድረግ አልፈው እምብዛም ወደ ተጋጣሚ ግብ ክልል ተጠግተው የግብ ዕድሎች ያፈጠሩት አዳማዎች በየኃላሸት ፍቃዱ እጅግ ለግብ የቀረበ ሙከራ አድርገው በፍሊፕ ኦቮኖ ተመልሶባቸዋል። የኃላሸት ፍቃዱ ከግብ ጠባቂው አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ነበር ኳሱን ወደ ግብነት ያልቀየረው።

እንደመጀመርያው አጋማሽ ሁሉ ጥቂት የግብ ሙከራዎች የታየበት ሁለተኛው አጋማሽ የባለሜዳዎቹ ብልጫ የታየበት ነበር። ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ ጥቂት ሙከራዎች ያደረጉበት ይህ አጋማሽ ገና በመጀመርያ ደቂቃዎች ነበር ግብ የታየበት። በአርብ ሰባተኛው ደቂቃም ሱሌይማን ሰሚድ ኳስ ለማራቅ በሚጥርበት ወቅት ወደ ራሱ ግብ አስቆጥሮ መቐለዎች መሪ መሆን ችለዋል።

መቐለዎች ከግቡ በኃላም በሶስት አጋጣሚዎች ሙከራዎች አድርገዋል። በተለይም አማኑኤል ገብረሚካኤል ከሳጥኑ ቀኝ ጠርዝ አከባቢ
መቶ ጃኮ ፔንዜ የመለሰበት ኳስ እና በተመሳሳይ አማኑኤል ከርቀት መቶ ግብ ጠባቂው ተፍቶ ያወጣው ኳስ ለግብ የቀረቡ ነበሩ።

ግብ ከተቆጠረባቸው ደቂቃ በኃላ ለተወሰኑ ደቂቃዎች ጥሩ መነሳሳት የነበራቸው አዳማዎችም የተወሰኑ ሙከራዎች አድርገዋል።
ከነዚህም ኃይሌ እሸቱ አክርሮ መቶ ያደረገው ሙከራ እና በጨዋታው መገባደጃ አከባቢ ከነዓን ማርክነህ ከርቀት ያደረገው ጥሩ ሙከራ ይጠቀሳል።

ጨዋታው ሊገባደድ የዋና ዳኛው ፊሽካ በሚጠበቅበት ወቅት አማኑኤል ገብረሚካኤል የጃኮ ፔንዜን መውጣት አይቶ በአየር ላይ ግሩም ግብ በማስቆጠር የመቐለን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችሏል።

ውጤቱን ተከትሎ መቐለዎች ከሽንፈት አገግመው ነጥባቸው ወደ አስራ ሶስት ከፍ ሲያደርጉ አዳማዎች ባሉበት ስምንት ነጥብ ረግተዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ