ሪፖርት | ጅማ አባጅፋር ወልቂጤን አሸንፏል

በ7ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ላይ ጅማ አባጅፋርን ከወልቂጤ ከተማ ያገናኘው ጨዋታ በባለዳው 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ጅማዎች ከስድስተኛው ሳምንቱት ወደ አዳማ ተጉዞ ከአዳማ ጋር አቻ ከተለያየው ስብስባቸው ውስጥ ሰዒድ ሀብታሙ፣ ሄኖክ ገምቴሳ እና ሱራፌል ዐወልን አስወጥተው በምትካቸው መሀመድ ሙንታሪ፣ ያኩቡ መሐመድ እና ሀብታሙ ንጉሴ ቀይረው ሲያስገቡ በአንፃሩ ወልቂጤ ከተማዎች ዳግም ንጉሴ፣ በረከት ጥጋቡና ሄኖክ አወቀን አስወጥተው መሐመድ ሻፊ፣ አሳሪ አልመሐዲን እና ሙሐጅር መኪ በምትካቸው አስገብተዋል።

ባለሜዳዎቹ ጅማ አባጅፋሮች በመጀመሪያዎቹ 25 ደቂቃዎች ላይ ወልቂጤዎች የኳስ ቁጥጥር የበላይነት እንዳይኖራቸው ለማድረግ ጥረቶችን ሲያደርጉ ታይቷል። ይህ የጅማ አጨዋወት ምቾት ያልሰጣቸው ወልቂጤዎች ረጃጅም ኳሶችን በማሻገር የግብ ማግባት ሙከራዎችን አድርገዋል። በዚህ የጨዋታ እንቅስቃሴም ወልቂጤዎች በ4ኛው እና በ18ኛው ደቂቃ በጃኮ አራፋት አማካኝነት ረጃጅም ኳሶችን ፍሬያማ ለማድረግ ጥረው መክኖባቸዋል።

በጨዋታው በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ከተከላካይ ጀርባ በሚጣሉ ኳሶች ለማጥቃት ጥረት ሲያደርጉ የተስተዋሉት የጅማዎች ብዙዓየሁ እንደሻው ላይ ያነጣጠረ ኳስ ወደ ፊት ልከው ጥሩ ጥቃት ሰንዝረዋል። ከዚህ ውጪ ጅማዎች እንደ አጀማመራቸው ተጋጠቀሚን ምቾት የሚነፍጉ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ጨዋታቸውን ቀጥለዋል።

በሂደት የተሻለ የጨዋታ እንቅስቃሴ እያሳየ የመጣው ጨዋታው የግብ ሙከራዎችን ማስተናገድ በድጋሚ ጀምሯል። በ35ኛው ደቂቃም ሱራፌል በረጅሙ ለብዙዓየሁ ያሻገረውን ኳስ ብዙዓየሁ ያልተጠቀመበት እንዲሁም ጃኮ እና አብዱልከሪም ያደረጉትን የግብ ማግባት ሙከራ መሐመድ ሙንታሪ ያመከነባቸው አጋጣሚዎች በሁለቱ ቡድኖች በኩል የተደረጉ ሙከራዎች ናቸው።

የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩትም ጫላ ተጨዋቾችን ቀንሶ ወደ ግብ የመታት ኳስ በአጋማሹ መገባደጃ ላይ የታየች ጥሩ ሙከራ ሆና ተመዝግባለች። የመጀመሪያው አጋማሽም ምንም ግብ ሳይስተናገድበት 0-0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ሰራተኞቹ ከጨዋታው ሙሉ ሦስት ነጥብ ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። በአንፃሩ ጅማዎች በመልሶ ማጥቃት አስፈሪነታቸው በማጠናከር አጋማሹን ጀምረዋል።

ተጋባዦቹ ወልቂጤዎች ገና አጋማሹ እንደተጀመረ በደቂቃዎች ውስጥ በጫላ እና በአብዱልከሪም አማካኝነት የግብ ማግባት ሙከራ አድርገው መሐመድ ሙንታሩ አድኖታል። ጅማዎች በበኩላቸው በ65ኛው ደቂቃ ጥሩ የግብ ማግባት አጋጣሚ ፈጥረው መክኖባቸዋል። በዚህ ደቂቃ ሀብታሙ ንጉሴ ከወልቂጤ ተጫዋቾች ጋር ታግሎ ያገኘውን ኳስ ለብዙዓየሁ አመቻችቶ ብዙአየሁ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። በደጋፊያቸው ፊት ሦስት ነጥብ ማስመዝገብ የፈለጉት የአሰልጣኝ ጻውሎስ ጌታቸው ተጨዋቾች በ74ኛው ደቂቃ ኳስ እና መረብን አገናኝተዋል። በዚህ ደቂቃ የተገኘውን የመዓዘን ምት የተሻማን ኳስ በመጠቀም ንጋቱ ገብረሥላሴ ቡድኑን መሪ አድርጓል።

ከግቡ መቆጠር በኋላ እጅጉን ጫና ያደረጉት ወልቂጤዎች በጫላ እና አብዱልከሪም አማካኝነት ተደጋጋሚ ሙከራዎችን አድርገዋል። ነገር ግን ቡድኑ ፍሬያማ መሆን ሳይችል ከጨዋታው ሦስት ነጥብ አስረክቦ ወጥቷል።

ውጤቱን ተከትሎ ጅማ አባጅፋሮች ከነበሩበት 13ኛ ደረጃ ወደ 6ኛ ደረጃ ሲሸጋገሩ ወልቂጤዎች ደግሞ ከነበሩበት 10ኛ ደረጃ 2 ደረጃዎችን ሸርተት በማለት 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ