ሪፖርት | ፋሲል ከነማ በመጨረሻ ደቂቃ ጎል ከወላይታ ድቻ ጋር ነጥብ ተጋርቷል

በ7ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ ሶዶ ላይ ፋሲል ከነማን ያስተናገደው ወላይታ ድቻ ባለቀ ሰዓት በተቆጠረበት የፍፁም ቅጣት ምት ግብ በ1-1 ውጤት ጨዋታውን ሲያጠናቅቅ የዐፄዎቹ አንድ ነጥብ ይዘው መመለስ ችለዋል።

ወላይታ ድቻ ከሜዳው ውጪ በ6ኛው ሳምንት የሊግ መርሐግብር በሰበታ ከነማ ሽንፈት ካሰተናገደበት ስብስብ ውስጥ የሁለት ተጫዋቾችን ለውጥ በማድረግ ይግረማቸው ተስፋዬን በእዮብ ዓለማየሁ እና እንድሪስ ሰዒድን በተመስገን ታምራት በመተካት ወደ ሜዳ ሲገባ እንግዳው ፈሲል ከነማ በሜዳው ባህርዳር ከነማን 3-0 ካሸነፈበት አሰላለፍ ውስጥ የአንድ ተጫዋች ለውጥ ብቻ በማድረግ ሐብታሙ ተከስተን በጀብሪል አህመድ በመተካት ጨዋታውን ጀምሯል።

በቀዝቃዛ እንቅስቃሴ የጀመረው የመጀመርያው አጋማሽ ብዙ የግብ ዕድሎች ያልተፈጠሩበት እና የባለሜዳዎቹ ፍፁም የጨዋታ የበላይነት የታየበት ሲሆን የሊጉ መሪ የነበረው ፋሲል ከነማ በአንጻሩ እጅግ ወርዶ የታየበት አጋማሽ ነበር። በተለይም የነጥብ ማጣት ጭንቀት ውስጥ የገቡት ድቻዎች በሜዳው 3 ነጥብ ለማግኘት በሚመስል መልኩ የተንቀሳቀሱ ቢሆንም እንደነበራቸው የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የጠራ የግብ ዕድል አለመፍጠራቸው አግራሞትን የጫረ ነበር። ድቻዎች በተለይም መሀል ላይ በተስፋዬ አለባቸው እና በረከት ተስፋዬ ጠንካራ ታታሪነት የፋሲልን አጨዋወት የገቱ ከመሆኑም በላይ ወደ ሁለቱም መስመሮች በሚያሻግሯቸው ኳሶች የፋሲልን ተከላካይ ክፍል ሲያስጨንቁ ነበር። ሆኖም ግን በአጋማሹ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ከሦስት ያልበለጡ ሙከራዎች ብቻ ነበር የተመለከትነው። እነሱም በፋሲል በኩል ገና በ2ኛው ደቂቃ ላይ ዓለምብርሃን ይግዛው ከርቀት አክርሮ መትቶት መክብብ ደገፉ እንደምን ያወጣበት እና በተመሳሳይ በ10ኛው ደቂቃ ላይ ሱራፌል ዳኛቸው ከርቀት የመታው ኳስ በግብ አናት ላይ የወጣበት ሙከራዎች ሲታዩ በድቻዎች በኩል በ43ኛው ደቂቃ ላይ ቸርነት ጉግሳ በግራ በኩል ሰብሮ ጥሩ አጋጣሚ የፈጠረ ቢሆንም ለቡድን ጓደኞቹ ለማቀበል ሲሞክር የፋሲል ተከላካዮች እንደምንም ያወጡበት አጋጣሚ ይጠቀሳል። በዚህም የመጀመርያው አጋማሽ ግብ ሳይቆጠርበት ቡድኖቹ ወደ ዕረፍት አምርተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው አንፃር ጥሩ ፍክክር የታየበት በጨዋታው የተገኙ ሁለት ግቦችም የተስተናገዱበት ነበር። በመጀመርያው አጋማሽ ላይ ጥሩ የነበሩት ባለሜዳዎቹ ድቻዎች ሁለተኛም አጋማሽ ላይም ያንኑ ብልጫ በማሳየት ተጋጣሚያቸውን ሲያሰጨንቁ ተስተውሏል፤ በአንጻሩ አፄዎቹ በዚህኛው አጋማሽ አልፎ አልፎ ወደ ጨዋታው ለመግባት ሲሞክሩ የተስተዋለ ሲሆን በተለይም በ52ኛው ደቂቃ ሽመክት ጉግሳ ከፍ አድሮጎ ያሳለፈለትን ኳስ ሙጂብ ቃሲም ሳይደርስባት የቀረው እና በ55ኛው ደቂቃ በዛብህ መለዮ በግራ ማዕዘን ምት አከባቢ ያገኘውን ጥሩ ኳስ ቢያሻማም ሙጂብ ዘሎ ሳይደርስባት የቀረው አጋጣሚ በቡድኑ በኩል ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ።

ድቻዎች ፍጽም የበላይ ሆነው ባመሹበት በዚህ ጨዋታ በ65ኛው ደቂቃ ቸርነት ጉግሳ በግራ መስመር አክርሮ የመታትን ኳስ ሳማኬ እንደምንም ሲያድንበት ከ4 ደቂቃ በኋላም ፀጋዬ አበራ በግራ ማዕዘን ምት አከባቢ በጥሩ ሁኔታ የሞከራትም ኳስ በሳማኬ ጥረት መክናለች። ይህ ጫናቸው የቀጠለው ድቻዎች በፋሲል ከነማ የግራ ግብ ክልል ስር በረከት ተጠልፎ የተሰጠውን ቅጣት ምት በዕለቱ ታታሪ የነበረው ባዬ ገዛሀኝ በ72ኛው ደቂቃ ላይ በድንቅ ሁኔታ በመምታት ኳስን ከመርብ ጋር አገናኝቶ ለባለሜዳዎቹ የመጀመርያውን እና መሪ የሆኑበትን ግብ አስገኝቶላቸዋል። ከጎሏ መቆጠር በኋላ ድቻዎች መነቃቃታቸው ሲቀጥል ዕንገዶቹ ፋሲሎች ደግሞ ጎል ለማስቆጠር በሚያረጉት እንቅስቃሴ ሽኩቻዎች እና ግጭቶች የበዙበት እንቅስቃሴ እንዲታይ ሆኗል። በተለይም ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ዓለምብርሃን ይገዛው በ80ኛው ደቂቃ ላይ ከግብ ክልል ውጪ ያገኛቸውን ሁለት የአየር ላይ ኳሶች በቀጥታ ወደ ጎል ቢሞክረም የድቻ ተከላካዮች ተደረበው ወጥተውበታል። 

በዚህ ወጥረት በቀጠለው ጨዋታ በቀኝ መስመር ወደ ድቻ ግብ ክልል የተላከችውን ኳስ እዮብ አለማየው በእጁ የነካትበት አጋጣሚ ለፋሲል ከነማ የፍፁም ቅጣት ምት ያስገኘ ሲሆን ሙጂብ ቃሲምም በ90ኛው ደቂቃ ላይ ፋሲል ከነማን ከሽንፈት ያዳነች ጎል አስቆጥሯል። በዚህም ጨዋታው ለባለሜዳዎቹ እጅጉን በሚያስቆጭ አጋጣሚ ለፋሲል ከነማ ደግሞ ጥሩ ባልነበረበት ዕለት ጣፋጭ አንድ ነጥብ አስገኝቶለት ተጠናቋል።

የመሐል ዳኛው ከ90 ደቂቃ እና የባከኑ 4 ደቂቃዎች አልቀዋል በማለት ጨዋታውን ሲያጠናቅቁ የወላይታው ድቻው አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ የጨዋታው ደቂቃ አላለቀም በማለት ወደ አራተኛው ዳኛ እና ኮሚሽነሩ ጋር ሄደው አቤቱታ በማቅረባቸው ጨዋታው እንደገና ተጀምሮ ለአንድ ደቂቃ ያህል ተካሂዶ መጠናቀቁ የዕለቱ አነጋጋሪ ክስተት ሆኖም አልፏል።

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ