ሪፖርት | ወልዋሎ ከሜዳው ውጪ ጣፋጭ ድልን በመቀዳጀት ወደ ሊጉ መሪነት ተመልሷል

ድሬዳዋ ላይ የተደረገው የድሬዳዋ ከተማ እና የወልዋሎ ዓ/ዩ ጨዋታ በተጋባዦቹ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

አሰልጣኝ ስምዖን ዓባይ ከባለፈው ሳምንት የሲዳማ ቡና ጨዋታ ያሬድ ዘውድነህ እና ዋለልኝ ገብሬን በቢኒያም ጥዑመልሳን እና ዳኛቸው በቀለ ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል። አሰልጣኝ ዮሐስ ሳህሌ በበኩላቸው በሜዳቸው ከሃዋሳ ከተማ ጋር ነጥብ ከተጋሩበት ጨዋታ ዳዊት ወርቁ እና ሠመረ ሃፍታይን በሚካኤል ለማ እና ጣዕመ ወ/ኪሮስ ለውጠው ለጨዋታው ቀርበዋል።

ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያዎቹ 10 ደቂቃዎች ላይ ጥቃቶችን እርስ በእርስ መሰናዘር ተስኗቸው ታይቷል። በአንፃራዊነት በኳስ ቁጥጥር እና በመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴዎች የተሻሉ የነበሩት ባለሜዳዎቹ በ11ኛው ደቂቃ እጅግ ለግብነት የተቃረበ አጋጣሚ አምልጧቸዋል። በዚህ ደቂቃ በተሰራ ጥፋት የተገኘውን የቅጣት ምት ቢኒያም ጥዑመልሳን ወደ ግብ በቀጥታ መትቶት ግብ ጠባቂው ጃፋር ደሊል በጥሩ ብቃት አምክኖበታል። ይህንን ሙከራ ያደረገው ቢኒያም በተደጋጋሚ በአንድ ሁለት ቅብብሎች ወደ ወልዋሎ የግብ ክልል በመሄድ ሙከራዎችን ለማድረግ በግሉ ቢጥርን ተከላካዮች ሲያከሽፉበት ተስተውሏል።

ወልዋሎዎች በበኩላቸው በ16ኛው ደቂቃ ጥሩ አጋጣሚ ፈጥረው ነበር። በዚህ ደቂቃ ኢታሙና ኬይሙኒ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ጁንያንስ ናንጂቦ ሞክሮት መረብ ላይ ልታርፍ የተቃረበችውን ኳስ ከግብ ጠባቂው ፍሬው ጌታሁን ፈጥነው የደረሱት የድሬዳዋ ተከላካዮች ኳሷን አውጥተዋታል። ጨዋታው ከተጀመረ ከ20ኛው ደቂቃ በኋላ ተመጣጣኝ የኳስ እንቅስቃሴ እና የግብ ሙከራዎች ታይተዋል። ቀስ በቀስ እየተነቃቁ የመጡት ወልዋሎዎችም በ24ኛው ደቂቃ ጁንያንስ ናንጂቦ ጎል አስቆጥረው መሪ ሆነዋል።

በጨዋታው መሪ የሆኑት ወልዋሎዎች ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር እንዲሁም ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ የአቻነት ጎል ለማግኘት ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ማድረግ ቀጥለዋል። ነገር ግን ሁለቱም ቡድኖች ፍሬያማ የሆነ እንቅስቃሴ ማድረግ ተስኗቸው የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ሁለቱም ቡድኖች የተጨዋች ቅያሪዎችን በማድረግ በተሻለ ለመንቀሳቀስ ሞክረዋል። አጋማሹ እንደተጀመረም ባለሜዳዎቹ ድሬዳዋዎች በሪችሞንድ ኦዶንጎ የርቀት ኳስ የወልዋሎን የግብ ክልል መጎብኘት ጀምረዋል። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ባጅዋ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረስ ግብ ለማስቆጠር ጥሯል። ከእነዚህ ሁለት ሙከራዎች በተጨማሪም ቡድኑ በ55ኛው ደቂቃ አማረ በቀለ ከመስመር አሻምቶት ያሬድ ታደሰ ወደ ግብ በመታው ነገር ግን የግቡ አግዳሚ በመለሰው አጋጣሚ እጅግ ለአቻነት ተቃርበው ነበር።

በአጋማሹ ጅማሬ የጨዋታ ብልጫ የተወሰደባቸው ወልዋሎዎች በ60ኛው ደቂቃ መሪነታቸውን አስፍተዋል። የድሬዳዋ ተከላካዮች መዘናጋትን ተከትሎ የተገኘውን ኳስ ጁንያንስ ናንጂቦ ለቡድኑ እና ለራሱ ሁለተኛ ግብ በማስቆጠር የቡድኑን የራስ መተማመን ከፍ አድርጓል። ጥረታቸውን ከንቱ የሚያደርግ ጎል ሳያስቡት የተቆጠረባቸው ድሬዎች በባጅዋ፣ ያሬድ እና ቢኒያም አማካኝነት ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ማድረግ ቀጥለዋል። ነገር ግን ቡድኑ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ የስልነት ችግር ታይቶበት ግብ ማስቆጠር አልቻለም። ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ሊጠናቀቅ 2 ደቂቃዎች ሲቀሩትም ግዙፉ አጥቂ ሪችሞንድ አዶንጎ የጨዋታውን የመጨረሻ ሙከራ አድርጎ የግቡ ቋሚ መልሶበታል።

ጨዋታውም በተጋባዦቹ ወልዋሎ ዓ.ዩ 2-0 አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ ባለሜዳዎቹ ድሬዳዋዎች ባሉበት 14ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ ወልዋሎዎች ደግሞ ዳግም ሊጉን በ14 ነጥብ መምራት ጀምረዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ