“የደጋፊውን ሰላማዊ ተቋውሞ ክለቡ ይደግፋል” አቶ ሙልጌታ ደሳለኝ

የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ በተደጋጋሚ በደጋፊዎቹ እና በፀጥታ ሃይል አባላት ጋር በሚፈጠሩ ችግሮች እና ግጭቶች ላይ ክለቡ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መነጋገር እንደሚፈልግ ተነግሯል፡፡ ክለቡ ባሳለፍነው ዕሁድ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ በሃዋሳ ከተማ 1-0 ሲሸነፍ በተፈጠረው ክስተት እነዲሁም ሐሙስ ዕለት ከሃድያ ሆሳና ጋር በተደረገ የኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታ ደጋፊዎቹ ከፖሊስ ጋር ግጭት ውስጥ ገብተዋል፡፡

 
የክለቡ የህዝብ ግንኙነት አቶ ሙልጌታ ደሳለኝ ዛሬ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት ደጋፊው ሊከብር እንዲገባ አስገንዝበዋል፡፡ “ክለቡ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መነጋገር ይፈልጋል፡፡ መነሻው ምንም ይሁን ምን ፀጥታን ለማስከብር ሰላማዊ መንገድን መጠቀም አግባብ ነው፡፡ ይህ እግርኳስ ነው ደጋፊው የመጣው እግርኳስን ለመመልከት ነው፡፡ ይህንን በተመለከተ ከደጋፊ ማህበሩ ጋር ተነጋግረን እሁድ ስብሰባ ጠርተናል፡፡ ለስብሰባው ፍቃድ ተከልክለን ቆይተናል፡፡ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ለመነጋገር ግዜው አሁን ነው” ብለዋል፡፡

 
አቶ ሙልጌታ አክለው “የደጋፊውን ሰላማዊ ተቋውሞ ክለቡ ይደግፋል ደጋፊው በ60ኛው ደቂቃ ጨዋታውን ትቶ በመውጣት ያላው ተቋውሞ በሰላማዊ መንገድ ነበር የገለፀው፡፡ ከስታዲየም አትወጡም የተባሉ ደጋፊዎቻችን ነበሩ፡፡ እንደነዚህ ዓይነት ችግሮች ደጋፊዊን ለእንግልት እና ጉዳት እያጋለጡት ነው፡፡ ይህም ጉዳይ ባስቸኳይ ዕልባት ሊበጅለት ይገባል፡፡”

 
የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ከሃዋሳ ከተማ ጋር ሲያደርገው የነበረው ጨዋታ ከግማሽ ሰዓት በላይ ተቋርጧ የነበረ ሲሆን ክለቡ በጉዳዩ ላይ ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን አቤቱታ አለማቅረቡን ለማወቅ ተችሏል፡፡
“የጨዋታ ኮሚሽነሩ የተመለከቱትን በጨዋታ ሪፖርቱ ላይ አስፍረዋል የሚል ዕምነት አለን፡፡ አዲስ አበባ ስታዲየም ብቻ ሳይሆን የተለያዩ አጥር የሌላቸው የክልል ስታዲየሞች ውስጥ የሚደረጉ ጨዋታዎች ሊታሰብባቸው ይገባል” በማለት አቶ ሙልጌታ ሃሳባቸውን አጠናቅቀዋል፡፡

ያጋሩ