ሀዋሳ ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ በሰባተኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ያለ ግብ አቻ ከተለያዩ በኋላ የሁለቱ ክለብ አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተውናል፡፡
👉 “ተጫዋቾች እየተጨነቁ እየተጫወቱ አይሆንም” አዲሴ ካሳ (ሀዋሳ ከተማ)
ስለጨዋታው
ጨዋታው ጥሩ ነው፤ በሁለታችንም በኩል ውጤት ለማምጣት ዕድሎችን ፈጥረናል። ሁለታችንም የፈጠርናቸውም መጠቀም አልቻልንም። ያው ኳስ ጨዋታው ጎል ማግባት ነው ጎል ስታገባ ቡድንህ ያሸንፋል ግን ሞክረናል። መቐለም ባለፈው እንዲሁ ነው የተከሰተው፤ የምታገኘውን አጋጣሚ መጠቀም ከቻልክ ታሸንፋለህ። በቃ ይህ የኳስ ጨዋታው ህግ ነው። እነሱም ጥሩ ናቸው፤ ሊገቡ የሚያስቡበት መንገድ በጣም ጥሩ ነው። የነሱ የዛሬው አቀራረብ ለየት ያለ ነው። በፊት ጊዮርጊስ የሚያደርገውን አይደለም ዛሬ ያደረገው።
በተደጋጋሚ በሜዳ ላይ ነጥብ ስለመጣል
ነጥብ መጣል ምን ማለት እንደሆነ አልገባኝም። ይሄ ኳስ ጨዋታ ነው። በኳስ ጨዋታ ነጥብ ታገኛለህ፤ ነጥብ ታጣለህ። እዚህ ስትጥል ውጪ ላይ እየያዝን ነው እኮ። እዚህም የምናገኘውን ውጪም ላይ እያገኘን ነው፡፡ እዚህ ነጥብ ጥለህ ከሜዳው ውጪ ምትጥል ከሆነ ጥያቄው ልክ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ቡና እና ሲዳማ ቡና በስተቀረ አምስት ጨዋታ ላይ ሁለት ጎል ነው የገባብን። ስለዚህ ተከላካያችን ጥሩ ነው፡፡
ትልቁ ነገር የተጫዋቾቻችን ስነልቦና ነው። እኔ ተጫዋቾቹን ማመስገን እፈልጋለሁ። የመጫወት ፍላጎታቸው ካለፉት ሁለት ጨዋታ በኃላ ተመልሷል፡፡ ያሉንን ልጆች ማበረታት ያስፈልጋል፤ ማነሳሳት ያስፈልጋል። ስለዚህም አንድ ቡድን የሚበረታታ ከሆነ የባለቤትነት ስሜት የሚኖር ከሆነ ቡድንህ እየጨመረ ይሄዳል። ግን ልጆች እየተጨነቁ ከተጫወቱ አይሆንም።
የዳንኤል ደርቤ ቅያሪ
ዳኒ ልምድ ያለው ተጫዋች ነው። የሚመራውም እሱ ነው። በትክክል አይታችሁት ከሆነ ሁለት ሶስት ኳሶች መስመር ላይ ነፃ ቦታ ላይ እየተላኩ ዳኒ እየቆመ ነበር። አንድ የመስመር ተጫዋች ነፃ ቦታ ላይ የተላከ ኳስ ላይ ሮጦ የማይታገል ከሆነ የሆነ ችግር አለበት ማለት ነው። ተመልሶም የመከላከል ወረዳው ላይም አይገባም ነበር፡፡
👉 “የግብ ጠባቂያቸው ጥንካሬ ጎል ማስቆጠር እንዳንችል አድርጎናል” ሰርዳን ዚቮጅኖብ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)
ስለ ጨዋታው
ጨዋታው በጣም ጥሩ ነበር ብዙ ዕድሎችን ፈጥረናል፡፡ ነገር ግን ኳስ ወደ ግብ ለመግባት አልፈቀደችም፤ ምን ማለት ይቻላል? በጣም ተጫውተናል ብዙ ዕድሎችንም ፈጥረናል ጎል ላይ ብዙ ኳሶችን መተናል ኳሱን ከነሱ በተሻለ መያዝ ብንችልም ግን አላገባንም። ቢሆንም ጥሩ ነው። ከሜዳ ውጪ አንድ ነጥብ መጥፎ አይደለም። ከአሁን በኃላ ከባድ ጨዋታዎች አለብን። ስለቀጣዩ ነው ልናስብ የሚገባው። በሳምንት ሶስት ጨዋታዎችን እያደረግን ስለሆነ በደንብ ማገገም ይኖርብናል፡፡ ፕሮግራሙም ከባድ ነው ፡፡
ጎል ያላስቆጠሩበት ምክንያት
ላለማስቆጠራኝ ግብ ጠባቂያቸው ረድቷቸዋል። ከአስር በላይ መሞከር ችለናል፡፡ ወደ ነሱ ግብም በተደጋጋሚ ደርሰናል። የበረኛቸው ጥንካሬ ማስቆጠር እንዳንችል አድርጎናል። በአጠቃላይ ዕድለኛች አልነበርንም፡፡ የቡድኔ ጥንካሬ አሁን በደንብ እየጎላ መጥቷል። ተጫዋቾቹ ያደረጉት ጥንካሬን ሳላደንቅ አላልፍም። የተቸገርነው አንድ እና አንድ ጎል አለማግባችን ነው፡፡
ስለ ውጤቱ
በውጤቱ አላመንኩበትም፤ አጨዋወታችን ግን ደስ ይል ነበር። ሁለት ነጥብ ነው አጥተን አንድ ነጥብ አግኝተናል። ከሜዳ ውጪ ለሚጫወት ደግሞ ይሄ መጥፎ አይደለም። በአጭር ጊዜ ውስጥ ተደጋጋሚ ጨዋታን ማድረግ ቢከብድም ገና ቀሪ ሀያ ሶስት ጨዋታዎች አሉን። እነዛን እያሸንፍን ከመጣን አስደሳች ውጤቶች ይኖሩናል ብዬ አምናለሁ፡፡
© ሶከር ኢትዮጵያ