የአሰልጣኞች አስተያየት | ድሬዳዋ ከተማ 0-2 ወልዋሎ

በ7ኛ ሳምንት የሊጉ መርሃ ግብር ወልዋሎ ከሜዳው ውጪ ድሬዳዋ ከተማን ካሸነፈበት ጨዋታ በኋላ የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች ለጋዜጠኞች ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።


👉”በጨዋታው የነበረን የፍላጎት እና የጉጉት ስሜት ተሽለን እንድንወጣ አድርጎናል” ዮሐንስ ሳህሌ (ወልዋሎ)

ስለ ጨዋታው

እኛ በፍላጎት ደረጃ የተሻልን ነበርን። በሶስት ጨዋታ አለማሸነፋችን እና ጎል አለማስቆጠራችን ተጨዋቾቼ ላይ የቁጭት ስሜት ፈጥሯል። ስለዚህ የነበረን የማሸነፍ ፍላጎት እና ጉጉት በጨዋታው ከእነሱ እንድንሻል አድርጎናል። የእነሱን ማንነት እስከምናቅ ጊዜ ድረስ ጎል አለማግባታችን ጥሩ ነው። ልክ የእነሱን አጨዋወት ካየን በኋላ መጫን እንዳለብን ተማምነን ወደ ፊት መጓዝ ጀምረናል።

ስለ ቡድኑ እንቅስቃሴ

ቡድኑ በጉዳት እና በቅጣት ተጨዋቾችን እያጣ ነው ያለው። በተለይ ወሳኝ እና ልምድ ያላቸውን ተከላካዮች ባለፉት ጨዋታዎች አተናል። አሁን ቡድኔ ውስጥ ወጣት ተጨዋቾች በአብዛኛው ስላሉ የልምድ አለመኖር ጉዳይ ሊኖር ይችላል። ወደፊት ግን ለእነዚህ ወጣት ተጨዋቾች ልምድ ሰተን በራስ መተማመናቸውን እናሳድጋለን። እስከዛ ግን የውጤት መበላሸትም ሊመጣ ይችላል። ሊጉ ገና ቢሆንም እኛ የምንፈልገው የመጀመሪያ ዙሩን ከወራጅ ቀጠና ውጪ ባለ ደረጃ ማጠናቀቅ ነው። በሁለተኛ ዙር ሊጉ እየተጠናከረ ስለሚሄድ ያኔ ጫና ውስጥ እንዳንገባ ነው ስራዎችን ቀድመን ለመስራት እየሞከርን ያለነው።


👉”እንደ ውጤት ይዘው በመጡት ነገር ማሸነፋቸው ይገባቸዋል። ነገር ግን እኛ በእንቅስቃሴ የተሻልን ነበርን” ስምዖን ዓባይ (ድሬዳዋ ከተማ)

ስለ ጨዋታው

እነሱ ይዘውት በመጡት ነገር አሸንፈውን ወተዋል። በጨዋታው በቀረቡበት መንገድ እንደሚመጡ መጀመሪያ እናውቅ ነበር። ይህንንም ተከትሎ ለተጨዋቾቼ ስራዎችን ሰጥቼ ነበር። ነገር ግን የሰጠውት ስራ በተጨዋቾቼ ምንም ሊተገበር አልቻለም። ምናልባት ይህ ጉዳይ ከጉጉት የመጣ ሊሆን ይችላል። በአጠቃላይ ግን በመልሶ ማጥቃት እና ያገኙትን አጋጣሚ በአግባቡ በመጠቀማቸው አሸንፈውን ወተዋል። እኛ የእነሱን ታክቲክ ማሸነፍ አልቻልንም፣ እነሱ ደግሞ የኛን ታክቲክ በልጠው ጎል አስቆጥረውብናል። እንደ ውጤት ይዘው በመጡት ነገር ማሸነፋቸው ይገባቸዋል። ነገር ግን እኛ በእንቅስቃሴ የተሻልን ነበርን። ከምንም በላይ ግን የተከላካይ መስመሬ ላይ ትልቅ ችግር አለ።

ቡድኑ ስለነበረበት ደካማ ጎን

የሚመጡትን የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች ማስቆም አልቻልንም። ሁለቱንም ጎሎች አንድ አጥቂ ነው ያገባብን። ይህንን አንድ አጥቂ ደግሞ የእኔ 4 ተከላካዮች በጋራ ማስቆም አልቻሉም። በአጠቃላይ የተከላካይ መስመሬ ላይ ትልቅ ጥያቄ አለ።

ስለ ቀጣዩ ከሜዳ ውጪ ጨዋታ

ቀጣዩ ጨዋታ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ነው። ይህ ጨዋታ ደግሞ በጣም ከባድ ጨዋታ ነው። ተሸንፈህ እና አሸንፈህ ስትሄድ ያለው ስሜት የተለያየ ነው። ነገር ግን ባሉኝ ተጨዋቾች ስህተቶቻችንን ለመቅረፍ ሞክረን ለጨዋታው እንቀርባለን።

© ሶከር ኢትዮጵያ