ከ7ኛ ሳምንት የሊጉ የዛሬ ጨዋታዎች መካከል ሶዶ ላይ ወላይታ ድቻ እና ፋሲል ከነማ ነጥብ ከተጋሩ በኋላ የቡድኖቹ አሰልጣኞች ተከታዮቹን አስተያየቶች ሰጥተዋል።
👉 ” ዛሬ ቡድኔ በሁሉም ነገር የተሟላ ነበር” ገብረክርስቶስ ቢራራ (ወላይታ ድቻ)
ስለጨዋታው
እንዳያችሁት ዘጠና ደቂቃ አልቆ ፍፁም ቅጣት ምት ተሰጥቶብናል፤ ኳሱ እጁን በመነካቱ ዳኛው የራሱን ውሳኔ ወስኗል። ዛሬ ቡድኔ በሁሉም ነገር የተሟላ ነበር። ሙሉ ቡድኔን ነው ያገኘሁት እና ከዚህ በኃላ በደንብ እንሻሻላለን።
ቡድኑ ጫና ውስጥ ስለመሆኑ እና በመጨረሻው ደቂቃ ላይ ስለተፈጠረው ጉዳይ
በፍፁም ጫና ውስጥ አይደለንም። ይሄ ሊግ እኮ አንዴ አሸንፈክ ወደ ላይ የምትወጣበት ነው። ዛሬ እኮ አሸንፈን ቢሆን ኖሮ 9ኛ እና 10ኛ እንሆን ነበር። መጨረሻ ላይ ጨዋታው አንድ ደቂቃ ሲቀረው ነበር ዳኛው የነፋው እና ያው ዳኞችም ሰው ናቸው እና ይሳሳታሉ።
የግብ ዕድሎችን የመፍጠር ችግር
ያው ይህ የሀገራችን እግርኳስ ችግር ነው። እኛ አንድ ጥሩ አጥቂ አለን ፤ በጣም ይጥራል። ነገር ግን የመጀመርያው አጋማሽ ላይ በጣም ጥንቃቄ የነበረው አጨዋወት ሰለመረጥን ነው ብዙ ዕድል ያልፈጠርነው።
ሰለደጋፊው እና ሰለ እዮብ ዓለማየሁ ያለቦታው መሰለፍ
ደጋፊው ትግስት ሊኖረው ይገባል። ይህ ቡድን እኮ ገንዘብ ሳያወጣ በወጣቶች እገነባለው ብሎ ነው የተነሳው እና ልጆቻቸውን በትህግስት ማበረታታት ይገባቸዋል። ቡድን በሂደት ነው የሚሰራው። እዮብ በጣም ጎበዝ ልጅ ነው ከ20 በታች ሲጫወት የነበረውም በዚህ ቦታ ነው። ዛሬ አብዛኛው ኳሶች በሱ በኩል ነው ያጠቃነው እና በፍፁም ሊተች አይገባውም። ደጋፊውም ሁሌ አንድ ጽንፍ ሊይዝ አይገባም።
👉 ” በዚህ ከባድ ጨዋታ አንድ ነጥብ ማግኘታችን በጣም የሚያስደስት ነው ” ሥዩም ከበደ (ፋሲል ከነማ)
ስለ ጨዋታው
እውነቱን ለመናገር ጨዋታው በጣም ከባድ ነበር ፤ በተለይ ከዕረፍት በፊት ምንም ልክ አልነበርንም። ምክንያቱም ኘሪምየር ሊጉን መምራት በጣም ደስታ ውስጥ ያስገባን መስሎኛል። ሊጉ ገና ጀመረ እንጂ አልጨረስንም። ከዕረፍት በኃላ መጠነኛ ለውጦች አድርገናል። ግን ሁሉም ልጆቼ ወርደዋል ማንም ከማንም መለየት አይቻልም። በዚህ ከባድ ጨዋታ አንድ ነጥብ ማግኘታችን በጣም የሚያስደስት ነው። ይህ ሜዳ እንደምንሰማው አይደለም በጣም ጥሩ ሆኗል። ድቻ በዛሬው ጨዋታ ጥሩ ቢሆንም አስደንጋጭ ሙከራ አላደረጉም ነበር።
የሜዳ ውጪ ጨዋታዎች ላይ ያለው የቡድኑ አቋም
እውነት ነው ፤ በሜዳችን በጣም ኃያል ነን። ነገር ግን ከሜዳ ውጪ እንለያያለን። እሱ ደግሞ በቅርብ የምናስተካክለው ነገር ነው። ነገር ግን እዚህ ሜዳ ሦስት ግዜ መጥተን ሁሉንም ተሸንፈናል። አቻ እንኳን መውጣት አልቻልንም ነበር እና ይሄኛው ጥሩ መሻሻል ነው።
© ሶከር ኢትዮጵያ