የአሰልጣኞች አስተያየት | ጅማ አባጅፋር 1-0 ወልቂጤ ከተማ

በጅማ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ከተደገረው የጅማ አባጅፋር እና የወልቂጤ ከተማ ጨዋታ በኋላ የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።

👉”ጨዋታው ሁለተኛ የሜዳችን ላይ ጨዋታ እንደመሆኑ ውጤቱን እንፈልገው ነበር” ጳውሎስ ጌታቸው (ጅማ አባጅፋር)

ስለጨዋታው

ጨዋታው በጣም የሚስብ እና በሁለታችንም በኩል በርከት ያሉ የግብ ማግባት አጋጣሚዎች የተፈጠሩበት ነበር። ጨዋታው ሁለተኛ የሜዳችን ላይ ጨዋታ እንደመሆኑ ውጤቱን እንፈልገው ነበር። ጨዋታውንም በማሸነፋችን በደረጃ ሰንጠረዡ ላይ ከፍተኛ መሻሻል አምጥተናል። ከውጤቱ በላይ ግን እኔ መናገር የምፈልገው ስላሉን አዳዲስ እና ወጣት ተጨዋቾች ነው። እሮጠው ያልጠገቡ ተጨዋቾች ስለሆኑ በጣም እየጠቀሙን ነው። ቅያሪያችንም በጣም ጥሩ ነበር። በአጠቃላይ ግን ጨዋታው በጣም ጥሩ ጨዋታ ነበር።

ቡድኑ ከሜዳው ውጪ ስላለው እንቅስቃሴ

ከሜዳችን ውጪ ጨዋታን እንደምናሸንፍ እርግጠኛ ነኝ። ከተጨዋቾቼ ጋር እየተነጋገርን ጨዋታዎችን ከሜዳችን ውጪም ለመግደል እንጥራለን። ነገር ግን ተጨዋቾቼ ላይ የጉልበት መጨረስ ነገር እያየሁ ነው። ይህም የሆነው ውድድሮቹ ተደራራቢ ስለሆኑ ነው። ይህንን ችግር ደግሞ ተጨዋቾችን እያፈራረኩ በመጫወት ለመፍታት እሞክራለሁ። በቀጣይ ግን ያሉብንን ክፍተቶች አስተካክለን ከሜዳችን ውጪ አሸንፈን ለመምጣት እና ደጋፊዎቻችንን ለማስደሰት እንሞክራልን።


👉”ተከላካዮቼ ላይ በተፈጠረ የመዘናጋት ችግር አሸንፈውናል፤ ጅማዎችን እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ” ደግአረግ ይግዛው (ወልቂጤ ከተማ)

ስለጨዋታው

ጨዋታው ጠንካራ ጨዋታ ነበር። ጨዋታው ከሜዳችን ውጪ ቢሆንም ሶስት ነጥብ ይዞ ለመመለስ አጥቅተን መጫወት አለብን ተባብለን ነበር ወደ ሜዳ የገባነው። በሜዳውም የታየው ይህ ነው። ነገር ግን ተከላካዮቻችን ላይ በተፈጠረ መዘናጋት እነሱ (ጅማ አባጅፋር) አሸንፈውን ወተዋል። በዚህ አጋጣሚ ጅማዎችን እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ።

ውጤቱ ከእቅዳቸው አንፃር

በቅድሚያ እቅዳችን ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ መቅረብ የሚል ነው። በየጨዋታውም እያየን ያለነው የተጨዋቾችን እንቅስቃሴ ይህንን የሚያጠናክር ነው። የሚችሉትን እና አቅማቸው የፈቀደውን ተጨዋቾቼ እያደረጉ ነው። በጨዋታዎች ውስጥ ማሸነፍ እና መሸነፍ ያለ ነገር ስለሆነ የዛሬው ውጤት ምንም ማለት አደለም። በቀጣይ ግን ያሉብንን ክፍተቶች አርመን የዛሬውን ውጤት ለመቀልበስ እንሞክራለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ