ኢትዮ ኤሌክትሪክ በአሰልጣኝ እየሩሳሌም ነጋሽ ጉዳይ መግለጫ ሰጠ

በኢትዮ ኤሌክትሪክ እና በአሰልጣኝ እየሩሳሌም መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት በተመለከተ ክለቡ ለሚዲያ አካላት ማብራሪያ ሰጥቷል።

ዛሬ 09፡00 ላይ የኢትዮ ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ የጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ ከክለቡ የሴቶች ቡድን የቀድሞዋ አሰልጣኝ እየሩሳሌም ነጋሽ ጋር የተፈጠሩ አለመግባባቶችን ተከትሎ ክለቡ እስካሁን የሄደበትን መንገድ ለሚዲያዎች ግልፅ ማድረግን ያለመ ነበር። የክለቡ ፕሬዘዳንት አቶ ኢሳያስ ደንድር ፣ ስራ አስኪያጁ አቶ ለማ ደበላ እና የደጋፊ ማህበር አመራሮች በተገኙበት በዚህ መግለጫ ላይ ከአሰልጣኟ ጋር ስለተለያዩበት ሂደት በየተራ ማብራሪያዎችን ሰጥተዋል።

እንደ ስራ አስኪያጁ አቶ ለማ ደበላ ገለፃ አሰልጣኝ እየሩስአሌም ከነሐሴ 28 2010 ጀምሮ ለሁለት የውድድር ዓመታት በሚያቆይ ውል ከክለቡ ጋር በመስማማት የማትፈልጋቸውን ነባር ተጫዋቾች ውል በማቋረጥ እና በአዳዲሶች በመተካት በ47 ቀናት የቅድመ ውድድር ዝግጅት እንዲሁም 1.6 ሚሊየን ብር አጠቃላይ ወጪ ቡድኑን በማደራጀት የውድድር ዓመቱን መጀመር ችላለች። ሆኖም ውድድሩ ከተጀመረ በኋላ ቡድኑ ከ16 ጨዋታዎች 12 ጨዋታዎችን በሽንፈት ደምድሟል። ያም በመሆኑ ክለቡ በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ አምስት የሚደርሱ ማስጠንቀቂያዎችን ለአሰልጣኟ በደብዳቤ ከሰጠ በኋላ ምንም እንኳን በውሉ ነጥብ 3.8 ላይ እንደሰፈረው ካለክፍያ ማሰናበት ቢችልም ከሦስት ወራት ደሞዝ ጋር ለማሰናበት ውሳኔ ላይ ቢደርስም ጉዳዩ በአሰልጣኟ በኩል ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቶ ወደ ፌዴሬሽኑ የዲስፕሊን እና ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴዎች ደርሷል።

የክለቡ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ደንድርም በበኩላቸው ከላይ የተቀመጠውን ዝርዝር በሰፊው ካብራሩ በኋላ ፌዴራሽኑ በሰጠው ውሳኔ ክለቡ አሰልጣኟን ወደ ስራዋ መመለስ ወይንም የአስር ወር ደምወዟን የመክፍል ግዴታ ውስጥ እንደገባ ተናግረዋል። ሆኖም ለጉዳዩ ዕልባት ለመስጠት ክለቡ በውሳኔው ተስማምቶ ቀሪውን የአሰልጣኟን የአስር ወር ደመወዝ ለመክፈል ከስምምነት የደረሰ ቢሆንም ወጪው ድንገተኛ ከበጀት ውጪ በመሆኑ ክለቡ በአንድ ጊዜ የመክፈል አቅም ስለሌለው በቅድሚያ አርባ ሺህ ብር ክፍያ እና በቀጣይ አራት ወራት በሚደረጉ ተመሳሳይ የአርባ ሺህ ብር ክፍያዎችን ለመጨረስ ፍቃደኛ ሆኗል። በአንድ ጊዜ መክፈል ግዴታ ከሆነ ደግሞ ክለቡ ፌዴሬሽኑ እጅ ላይ ካለው ገንዘብ ላይ ተቀናሽ ተደርጎ በአንድ ጊዜ እንዲከፈል ለፌዴሬሽኑ ጭምር በደብዳቤ ሀሳብ አቅርቧል። እንደ አመራሮቹ ገለፃ ከሆነ ግን ሀሳቡ በአሰልጣኟ ዘንድ ተቀባይነት ያላገኘ ሲሆን የክለቡ ውሳኔ የይግባኝ መልስ ለማግኘት ሦስት ወራት መፍጀቱም ጉዳዩን ይበልጥ አወሳስቦታል።

እንደ አመራሮቹ ገለፃም ከዚህ በተለየ በተለያዩ የማህበራዊ ገፆች ላይ ጉዳዩን አስመልክቶ ክለቡ የሚሰነዘሩ አስተያየቶች ከእውነት የራቁ መሆናቸውን እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ በሴቶች እግር ኳስ ላይ ያለውን ትኩረት በመጨመር ከ 20 ዓመት በታች ቡድን ጭምር ለማቋቋም በሂደት ላይ እንደሚገኝ ይፋ አድርገዋል።

ለዛሬው የክለቡ መግለጫ በአሰልጣኝ እየሩሳሌም ነጋሽ በኩል የሚሰጥ ምላሽ ካለ የዝግጅት ክፍላችን ለማስተናገድ በሩ ክፍት መሆኑን እንገልፃለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ