በተጫዋችነት ዘመኑ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በርካታ የስኬት ዓመታትን ያሳለፈው ሳምሶን ሙሉጌታ “ፍሌክስ” የታዳጊ ቡድኑ አሰልጣኝ ሆኖ ተመርጧል።
ከ2011 ጀምሮ በአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ስር በሚደረገው ከ17 ዓመት በታች የታዳጊዎች ውድድር ላይ እየተሳተፈ የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ዘንድሮም ለሚኖረው ተሳትፎ የቀድሞ አሰልጣኝ ደረጄን ከ20 ዓመት በታች ቡድኑን እንዲያሰለጥን መደረጉን ተከትሎ ከ17 ዓመት በታች የቡድኑ በዋና አሰልጣኝነት እንዲመራ የቀድሞ ስኬታማ ተጫዋቹ ሳምሶን ሙሉጌታን እንደሾመ መረጃዎች አግኝተናል። በቅርቡም አሰልጣኝ ሆኖ የመሾሙ ጉዳይ ይፋ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
ከ1991 አንስቶ ለአስራ አራት ዓመታት የፈረሰኞቹን የኋላ ክፍል ሲመራ የቆየውና ከ2001-2004 በአንበልነት ያገለገለው ሳምሶን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በቆየባቸው ዓመታት 10 የሊግ ዋንጫዎችን ጨምሮ በርከት ያሉ ድሎችን ያሳካ ሲሆን በመቀጠልም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ኢትዮጵያ መድን እና ዐምና የእግርኳስ ህይወቱ የመጨረሻ ወደ ሆነው ደቡብ ፖሊስ አምርቶ መጫወቱ ይታወሳል።
የተለያዩ ክለቦች ታዳጊ ቡድናቸውን በቀድሞ ስመጥር ተጫዋቾቻቸው እየሰለጡ መገኘታቸው ለታዳጊዎች ጥሩ ልምድ እና መልካም ስብዕና ኖሯቸው እንዲያድጉ ጠቀሜታው የጎላ ከመሆኑ ባሻገር የቀድሞ ተጫዋቾች ወደ አሰልጣኝነት ሙያ መሸጋገርያ ድልድይ እየሆናቸው ይገኛል።
© ሶከር ኢትዮጵያ