ፕሪምየር ሊግ 7ኛ ሳምንት | የሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ምርጥ 11

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ7ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ማክሰኞ እና ረቡዕ መካሄዳቸው ይታወሳል። በጨዋታዎቹ በንፅፅር ጥሩ እንቅስቃሴ ያሳዩ 11 ተጫዋቾችንም እንደሚከተለው አናድተናል።

* ምርጫው የሚከናወነው የሶከር ኢትዮጵያ ሪፖርተሮች እንዲሁም ጨዋታዎችን በሚከታተሉ ባሙያዎች ለተጫዋቾች በሚሰጡት የተናጠል ነጥብ መነሻነት ነው።

አሰላለፍ 3-5-2


ግብ ጠባቂ

ቤሊንጋ ኢኖህ (ሀዋሳ ከተማ)

ወጣ ገባ አቋም በማሳየት ላይ የሚገኘው ካሜሩናዊው አንጋፋ ግብ ጠባቂ ባለፉት ጨዋታዎች ስህተቶችን ሲሰራ የነበረ ቢሆንም በትላንትናው ጨዋታ ዳግም ድንቅ ብቃቱን ያገኘ ይመስላል። በተለይ የቅዱስ ጊዮርጊስ አጥቂዎች ጌታነህ፣ ሳላዲን እና አቤል የሚያደርጓቸውን ለግብነት የቀረቡ ሙከራዎች በማዳን ሀዋሳ ጎል ሳይቆጠርበት እንዲወጣ አስችሏል። ለሁለተኛ ጊዜ በሳምንቱ ምርጥ ቡድን ውስጥ ተካቷል።


ተከላካዮች

አሌክስ ተሰማ (መቐለ 70 እንደርታ)

በጥሩ ወቅታዊ ብቃት የሚገኘው እና ከአዳማ ከተማ በነበረው ጨዋታ ቡድኑ ግብ ሳያስተናግድ እንዲወጣ ጥሩ ድርሻ የነበረው ይህ ተከላካይ ከግዙፉ ላውረንስ ኤድዋርድ የነበረው ጥምረት እና በግሉ በጨዋታው የነበረው ተፅዕኖ በሳምንቱ ምርጥ ቡድን ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ እንዲካተት አስችሎታል። ፈጣኖቹን የአዳማ ከተማ አጥቂዎች እንቅስቃሴ በመግታት ረገድ ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴ ያደረገው አሌክስ ተሰማ ቡድኑ በመከላከል ላይ የነበረውን ደካማ ጎን እንዲሻሻል የጎላ አስተዋፅኦ ካደረጉ ተጫዋቾች አንዱ ነው።

አዩብ በቀታ (ሀዲያ ሆሳዕና)

ሀዲያ ሆሳዕና በሊጉ የመጀመርያ ሦስት ነጥብ እንዲያሳካ ቁልፍ ሚና ከተወጡ ተጫዋቾች አንዱ ነው። ፈጣኖቹን የሲዳማ ቡና ተከላካዮች በመቆጣጠር ረገድ ጥሩ ጊዜ ያሳለፈው አዩብ ትኩረቱ እና ከሌሎች ተጣማሪዎቹ ጋር የነበረው መናበብ ጥሩ የሚባል ነበር።

ከድር ኸይረዲን (ጅማ አባ ጅፋር)

ለጻውሎስ ጌታቸው ጥብቅ የመከላከል አደረጃጀት የከድር ሚና ላቅ ያለ ነው። የቡድኑን የተከላካይ መስመር የሚመራበት እና የአየር ላይ ፍልሚያዎችን የሚያሸንፍበት መንገድ ልዩ ነው። በትላንትናውም የጅማ ዩኒቨርስቲ ጨዋታ ከድር የወልቂጤን የአጥቂ መስመር ተጨዋቾች ጥቃት የሚመክትበት ስልት ቡድኑን ተጠቃሚ አድርጎ ሦስት ነጥቦች ይዞ እንዲወጣ አስችሏል።


አማካዮች

ሱራፌል ዳንኤል (ሀዲያ ሆሳዕና)

ሃዲያ ሆሳዕና የሊጉን የመጀመሪያ 3 ነጥብ በደጋፊው ፊት ሲያገኝ የታታሪው የመስመር ተጫዋች ብቃት ወሳኝ ነበር። ተጨዋቹ በ37ኛው ደቂቃ ቡድኑን መሪ የምታደርግ ጎል በግምባሩ ከማስቆጠሩ በተጨማሪ ሲያደርጋቸው የነበሩ የመስመር ላይ ሩጫዎች ፋይዳ ነበራቸው። በትላንቱ ጨዋታ በመከላከልም ሆነ በማጥቃት እንቅስቃሴ ጥሩ የነበረው ሱራፌል ለመጀመሪያ ጊዜ የሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ምርጥ ቡድን ውስጥ ተካቷል።

ዳንኤል ኃይሉ (ባህር ዳር ከተማ)

ባለፉት ጨዋታዎች ላይ የተሰለፈው ፍቅረሚካኤል ዓለሙን ቦታ ሸፍኖ የተጫወተው ዳንኤል ኢትዮጵያ ቡናን ባሸነፉበት ጨዋታ ላይ ቡድኑን ሚዛን በመጠበቅ ረገድ ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ቡድኑ ጫና ውስጥ በነበረበት ወቅትም ለተከላካይ መስመሩ ሽፋን በመስጠት ጥሩ አስተዋጽኦ አበርክቷል። የቡድኑ የመክፈቻ ጎልንም ማስቆጠር ችሏል።

ፍቅረየሱስ ተ/ብርሃን (ኢትዮጵያ ቡና)

ለአዲሱ የካሣዬ አራጌ የጨዋታ ዘይቤ ምቹ የሆነው ፍቅረየሱስ ከጨዋታ ጨዋታ መሻሻሎችን እያሳየ ይገኛል። የቡድኑን የማጥቃት ሂደት በሚያፋጥንበት መንገድ የሚታወቀው ተጨዋቹ በትላንትናውም የባህር ዳር ጨዋታ የበለድኑ የማጥቃት ሒደት ላይ አስተዋፅኦው የጎላ ነበር። ከአጠገቡ ካሉት ሌሎች ተጨዋቾች ጋር በአግባቡ የተጣመረው ፍቅረየሱስ ቡድኑን ከሽንፈት ባይታደግም በጨዋታው አንድ ጎል ማስቆጠር ችሏል።

ፍፁም ዓለሙ (ባህር ዳር ከተማ)

በሊጉ ጥሩ ጊዜን እያሳለፉ ካሉ ተጨዋቾች መካከል ግንባር ቀደሙ ፍፁም ዓለሙ ነው። በባህር ዳር ከተማ ቡድን ውስጥ ለመዋሃድ ጊዜ ያልፈጀበት ፍፁም ቡድኑን ውጤታማ የሚያደርጉ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ ይገኛል። ከእንቅስቃሴም ባለፈ ተጨየጫዋቹ ከመሃል ሜዳ እየተነሳ ጎሎችን እያስቆጠረ ወሳኝ ነጥቦችን ቡድኑ እንዲያገኝ እያደረገ ይገኛል። በትላንቱም የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ሁለት ጎሎችን ለባህር ዳር በማስቆጠር የሊጉ ሁለተኛው ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኗል።

ግርማ ዲሳሳ (ባህር ዳር ከተማ)

በሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታዎች በጉዳት ምክንያት ለቡድኑ ግልጋሎት ያልሰጠው ግርማ ወደ ጨዋታ ከተመለሰ በኋላ ወደ ቀድሞ ብቃቱ እየተመለሰ ይመስላል። ፍጥነቱን እና ክፍሎቱን ተጠቅሞ በሚያደርጋቸው የመስመር ላይ እንቅስቃሴዎች የሚታወቀው ግርማ ትላንት ቡድኑ ኢትዮጵያ ቡናን ሲረታ ጥሩ ብቃት አሳይቷል። ተጨዋቹ ከእንቅስቃሴም በዘለለ ፍፁም ዓለሙ ላስቆጠረው ሦስተኛ ጎል ኳስን አመቻችቶ አቀብሏል።


አጥቂዎች

አቡበከር ናስር (ኢትዮጵያ ቡና)

ይህ ቀልጣፋ እና ፈጣን አጥቂ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳየ ያለው መሻሻል የሚያስደንቅ ነው። በወረቀት ላይ ከመስመር የሚነሳው አቡበከር አሁን አሁን የተጋጣሚ የተከላካይ ክፍል ፈተና ሆኗል። በተለይ ከተከላካዮች ጀርባ እየሮጠ የሚገባበት መንገድ፣ ከርቀት የሚመታቸው ኳሶች እና ለቡድን አጋሮቹ የሚያቀብላቸው ቁልፍ ኳሶች ተጨዋቹ ምን ያህል ወደ ታላቅነት እየተንደረደረ እንደሆነ የሚያሳብቁ ናቸው። ቡድኑ ኢትዮጵያ ቡና በትላንትናው ጨዋታ 3-2 ቢሸነፍም ሲያደርጋቸው የነበሩ ጥረቶች በሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ምርጥ ቡድን ውስጥ ለተከታታይ ሁለተኛ ጊዜ አስገብቶታል።

ጁኒያስ ናንጂቡ (ወልዋሎ)

ለተለያዩ የጨዋታ አማራጮች የተመቸው ይህ አጥቂ በትላንትናው ጨዋታ ሁለት ግቦችን ከማስቆጠሩ ጎን ለጎን በጨዋታው ድንቅ እንቅስቃሴን በማድረግ ቡድኑን ጠቅሟል። በትላንቱም ጨዋታ ተጨዋቹ ከቡድን አጋሩ ኢታሙና ኬይሙኒ ጋር የነበረው መናበብ የወልዋሎን የፊት መስመር አስፈሪ አድርጎት ውሏል።


ተጠባባቂዎች

መሐመድ ሙንታሪ (ጅማ አባ ጅፋር)
መሐመድ ዐወል (ወልቂጤ ከተማ)
ኤልያስ አህመድ (ጅማ አባ ጅፋር)
አማኑኤል ዮሐንስ (ኢትዮጵያ ቡና)
አቤል ያለው (ቅዱስ ጊዮርጊስ)
ኢታሙና ኬይሙኔ (ወልዋሎ)
ባዬ ገዛኸኝ (ወላይታ ድቻ)


© ሶከር ኢትዮጵያ