የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ከዛሬ ጀምሮ ይከፈት ይሆን?

የኢትዮጵያ ወንዶች እና ሴቶች ተጫዋቾች የውድድር ዘመን አጋማሽ (የጥር የዝውውር መስኮት) አስቀድሞ በተገለፀው መሠረት ዛሬ ስለመከፈቱ አጠራጥሯል።

ከዚህ ቀደም በተለምዶ የፕሪምየር ሊጉ የመጀመርያ የውድድር ዘመን (አንደኛ ዙር) አጋማሽ ሲጠናቀቅ የሚከፈተው የዝውውር መስኮት ከዘንድሮው ጀምሮ አሰራሩን በመቀየር የዓመቱ አጋማሽ የዝውውር መስኮት (ዛሬ) ጥር 1 ጀምሮ እስከ ጥር 30 ቀን 2012 (ከጃንዋሪ 10 እስከ ፌብሩዋሪ 8) ድረስ ክፍት ይሆናል። ይህንንም የኢትዮጵባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ክረምት ላይ ይፋ ማድረጉ አይዘነጋም።

ሆኖም ከፌዴሬሽኑ አካባቢ ባገኘነው መረጃ መሠረት ሊጉ ገና ጅማሬው ላይ በመሆኑ አስቀድሞ የወጣውን የዝውውር ቀናት በመቀየር የአንደኛው ዙር ማጠናቀቂያ ላይ ለማድረግ ስለመታቀዱ ሰምተናል። የውጪ ተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ግን በቅድሚያ ፊፋ ላይ በተመዘገበው (ከጥር 1-30 / ከጃንዋሪ 10 – ፌብሩዋሪ 8) መሠረት ከዛሬ ጀምሮ እንደሚከናወን ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዘንድሮ በታሪኩ እጅግ ዘግይቶ ኅዳር 21 መጀመሩ የሚታወስ ሲሆን እስካሁን የ7 ሳምንት ጨዋታዎች ብቻ ከመካሄዳቸው አንፃር ገና ጅማሮው ላይ ይገኛል ማለት ይቻላል። በዚህም ምናልባትም አስቀድሞ በተገለፀው ቀን ዛሬ የዝውውር መስኮቱ የሚከፈት ከሆነ አብዛኛዎቹ ክለቦች ከጊዜው በፍጥነት መድረስ እና ከበጀት እጥረት አንፃር ተጫዋቾችን ለማዘዋወር ገበያ የመውጣታቸው ሁኔታ አጠራጣሪ ነው።

* በፌዴሬሽኑ በኩል በጉዳዩ ዙርያ አዲስ መረጃ ካገኘን የምናሳውቅ መሆኑን ለመግለፅ እንወዳለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ