የፕሪምየር ሊግ ሰባተኛ ሳምንት ቁጥሮች እና እውነታዎች

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሰባተኛ ሳምንትን የተመለከቱ ቁጥራዊ መረጃዎች እና እውነታዎችን እንደሚከተለው አሰናድተናል።

ጎሎች በቁጥራዊ መረጃ

– በአምስተኛ ሳምንት በአጠቃላይ 16 ጎሎች ተቆጥረዋል። ይህም ባለፈው ሳምንት ከተቆጠሩ ጎሎች በ1 ከፍ ያለ ነው።

– በዚህ ሳምንት አንድ ጨዋታ (ሀዋሳ ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ) ጎል ሳይቆጠርበት ተጠናቋል። ከባለተጀው ሳምንት (3) ጋር ሲነፃፀርም የተሻለ ሆኖ ተመዝግቧል። ጎል ሳያስቆጥሩ የወጡ ቡድኖች 6 ሲሆኑ ይህም ከባለፈው ሳምንት አንፃር (9) መሻሻል አሳይቷል።

– እንደ ስድስተኛው ሁሉ በዚህ ሳምንት የተቆጠሩት 16 ጎሎች በ14 የተለያዩ ተጫዋቾች ተቆጥረዋል። አንድ ጎል (የአዳማ ከተማው ሱሌይማን ሰሚድ) በራስ ላይ የተቆጠረ ነው።

– ጎል ካስቆጠሩ 14 ተጫዋቾች መካከል 7 ጎሎች በአጥቂነት ጨዋታውን በጀመሩ ተጫዋቾች ሲቆጠር በተመሳሳይ 7 ጎሎች በአማካይ ሥፍራ ተጫዋቾች ተቆጥሯል። 2 ጎሎች ደግሞ በተከላካይ ሥፍራ ተጫዋቾች (በራስ ላይ የተቆጠረውን ጨምሮ) ተቆጥረዋል።

– ፍፁም ዓለሙ እና ጁኒያስ ናንጂቡ ሁለት ጎሎች በማስቆጠር ከፍተኛውን የጎል ቁጥር ሲያስመዘግብ ቀሪዎቹ 12 ተጫዋቾች አንድ ጎል አስቆጥረዋል።

– ከ16 ጎሎች መካከል 12 ጎሎች ከክፍት ጨዋታ እና ከተሻሙ ኳሶች (ከቅጣት ምት እና ማዕዘን ምት) ሲቆጠሩ 2 ጎል ከፍፁም ቅጣት ምት፣ 2 ጎል ደግሞ ከቀጥታ ቅጣት ምት የተገኙ ናቸው።

– ከዚህ ሳምንት 16 ጎሎች መካከል 15 በእግር ተመትተው ሲቆጠሩ አንድ ጎል ብቻ በግንባር ተገጭቶ ተቆጥሯል።

– ከ16 ጎሎች መካከል 11 ጎሎች ከሳጥን ውስጥ ተመትተው ሲቆጠሩ 5 ጎሎች ከሳጥን ውጪ ተመትተው ጎል ሆነዋል።


ካርዶች

– በዚህ ሳምንት 34 ቢጫ እና አንድ ቀይ ካርዶች የተመዘዙ ሲሆች ከአራተኛው (37) እና ሁለተኛው ሳምንት (35) ቀጥሎ ሦስተኛው ከፍተኛ ሆኖ የተመዘገበ ነው።

– ወልቂጤ ከተማ፣ ሀዋሳ ከተማ እና መቐለ 70 እንደርታ ምንም ማስጠንቀቂያ ያልተመለከቱ ክለቦች ሲሆኑ ሀዲያ ሆሳዕና 6 ካርድ በመመልከት ቀዳሚው ነው።


የሀዲያ ሆሳዕና የመጀመርያ ድል እና አስገራሚ ግጥምጥሞሽ

ሀዲያ ሆሳዕና ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከተመለሰ ወዲህ ለመጀመርያ ጊዜ ሦስት ነጥቦች አሳክቷል። ይህም 25 ተከታታይ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች በኋላ የተገኘ ድል ሆኖ ተመዝግቧል። ነብሮቹ ለመጨረሻ ጊዜ በፕሪምየር ሊጉ ድል ያስመዘገቡት ታህሳስ 21 ቀን 2008 ወላይታ ድቻን 5-1 በመርታት ሲሆን ከዛ በኋላ በተደረጉ 25 ጨዋታዎች ስድስት አቻ እና 19 ሽንፈት አስተናግደዋል።

አስገራሚው ነገር ሆሳዕና ለመጨረሻ ጊዜ ያሸነፈው በ7ኛው ሳምንት ሲሆን ዘንድሮ ወደ ድል የተመለሰውም በ7ኛው ሳምንት መሆኑ ነው።


የአዳማ ከተማ አስከፊ ከሜዳ ውጪ ሪከርድ

– የአዳማ ከተማ የሜዳ ውጪ ሪከርድ እጅግ አስከፊ ሆኖ ቀጥሏል። ቡድኑ ካለፉት 14 ጉዞዎቹ አንድም ድል ሳያሳካ የተመለሰ ሲሆን ካለፉት 21 የሜዳ ውጪ ጨዋታዎች ማሳካት የቻለውም 1 ድል ብቻ ነው። ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና ለ5ኛ ተከታታይ ጨዋታዎች ከሜዳቸው ውጪ ሳያሸንፉ ሲመለሱ ፋሲል ከነማም ከሜዳ ውጪ ጨዋታ ካሸነፈ ሰባት ጨዋታዎች ተቆጥረዋል።

በዚህ ሳምንት…

– ሙጂብ ቃሲም በተከታታይ አራት ጨዋታዎች ላይ ኳስና መረብን አገናኝቷል።

– በሊጉ ብቸኛው ያልተሸነፈ ቡድን የነበረው አዳማ ከተማ በመቐለ 2-0 ተሸንፏል።

– ሀዲያ ሆሳዕና ዘንድሮ ለመጀመርያ ጊዜ ሲዳማ ቡናን አሸንፏል።

– ሀብታሙ ሸዋለም በፕሪምየር ሊጉ ከሚጠቀሱ ጥሩ ፍፁም ቅጣት ምት መቺዎች አንዱ ነው። አማካዩ የመታቸውን ያለፉት ሦስት ተከታታይ ፍፁም ቅጣት ምቶችም ወደ ጎልነት ቀይሯቸዋል።

– ሲዳማ ቡና በሊጉ ከ2 ዓመታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ በተከታታይ ሁለት ጨዋታ ተሸንፏል። ለመጨረሻ ጊዜ በተከታታይ የተሸነፈው ሚያዚያ 2010 በቅዱስ ጊዮርጊስ እና ጅማ አባ ጅፋር ነበር።

– ወላይታ ድቻ ያለፉትን ስድስት ተከታታይ ጨዋታዎች ከድል ርቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ