የፋሲል ከነማ አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ የቀድሞው የክለቡ ተጫዋች ሙሉቀን አቡሃይን ወደ አሰልጣኝ ቡድናቸው ቀላቅለውታል ።
ከፋሲል ከነማ ታዳጊ ቡድን ጀምሮ ከ18 ዓመታት በላይ የከተማውን የውስጥ ውድድር ጨምሮ ብሄራዊ ሊግ፣ ሱፐር ሊግ እንዲሁም ክለቡ ወደ ፕሪምየር ሊግ ሲያድግ የቡድኑ አንበል ነበረው ሙሉቀን 2010 ላይ ፋሲል ከነማን ለቆ ወደ ኢኮስኮ በማምራት አንድ አመት ከተጫወተ በኋላ ጫማውን መስቀሉ ይታወሳል። ሙሉቀን የእድሜውን ግማሽ ወደቆየበት ክለብ በመመለስ የረዳት አሰልጣኝነትን ቦታን የተረከበ ሲሆን ከሌላኛው ረዳት አሰልጣኝ ኃይሉ ነጋሽ ጋር በመሆን የአሰልጣኝ ሥዩም ከበደን ፋሲል ከነማ ያገለግላል።
ከክለቡ ጋር የገባው ውል ለምን ያህል ጊዜ እንደሆነ ወደፊት የሚገለፅ ሲሆን ወደ ክለቡ በሌላ ሚና በመመለሱ መደሰቱን ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጿል። “በጣም ደስ ብሎኛል፤ በርካታ ዓመታትን ያሳለፍኩበት እንዲሁም ብዙ መስዕዋትነት ወደከፈልኩት ክለቤ በሌላ ሚና መመለሴ እጅግ አስደስቶኛል። ለክለቤ በተጫዋችነት ያለኝን ነገር ሁሉ ስሰጥ ነበር። አሁን ደግሞ ከዛ በተሻለ ክለቤን ለማገልገል ነው የተመለስኩት።” ብሏል
ተጫዋች በነበረበት ወቅት የመጀመሪያ ደረጃ አሰልጣኝነት ኮርስ መውሰዱን የሚገልፀው ሙሉቀን እግርኳስ ካቆመ በኋላም ተጨማሪ ስልጠናዎች ስለመውሰዱ ተናግሯል። ” እንደ አጠቃላይ የወደፊት እቅዴ ራሴን በሙያው እያሳደግኩ አሁን ካለሁበት ደረጃ ወደፊት የምሄድበትን መንገድ እፈጥራለሁ። ከሌሎች አጋሮቼ ጋር በመሆንም ለክለቡ ያለኝን ሁሉ መስጠት እፈልጋለሁ። ፋሲል ትልቅ ደጋፊ ያለው ታላቅ ክለብ ነው። ላደኩበት ለዚህ ክለብ ደግሞ ትልቅ ነገር መስራት እፈልጋለሁ።” ሲል ገልጿል።
© ሶከር ኢትዮጵያ