ቅድመ ዳሰሳ | ሰበታ ከተማ ከ ጅማ አባ ጅፋር

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ስምንተኛ ሳምንት ነገ በሚደረግ አንድ ጨዋታ ሲጀመር ሰበታ ከተማ ጅማ አባ ጅፋርን ያስተናግዳል።

ጥሩ ካልሆነ አጀማመር በኋላ ቀስ በቀስ ወደ ሊጉ ቅኝት እየገባ የሚገኘው ሰበታ ከተማ በሳምንቱ አጋማሽ በሽረ ከገጠመው ሽንፈት አገግሞ ደረጃውን ለማሻሻል ወደ ሜዳ ይገባል።

የሰበታ ከተማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም
ተሸነፈ አሸነፈ አቻ አሸነፈ አቻ

የቡድናቸውን አጨዋወት ከተጋጣሚያቸው እና ከጨዋታው ባህርይ አንፃር እየቃኙ የሚገኙት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ነገ ከጅማ አባ ጅፋር ከባድ ፈተና እንደሚገጥማቸው ይጠበቃል። በተለይም ከሜዳው ውጪ ሲጫወት ጠጣር በሆነ የመከላከል አደረጃጀት የሚጫወተው ጅማን እንደመግጠማቸው ኳሱን ለመቆጣጠር ባይቸገሩም በማጥቃት ወረዳው ላይ የተሳኩ ቅብብሎች ለማድረግና ክፍተት ለማግኘት ከፍተኛ ትግል ይጠብቃቸዋል። 

ከስሑል ሽረ ጋር ባደረጉት የሊጉ የመጨረሻ ጨዋታ በሁለቱም አጋማሾች የተለያዩ አጨዋወቶች የተገበሩት ሰበታዎች በመጀመርያው አጋማሽ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወስደው ባከናወኑት ጨዋታ የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ሲቸገሩ ተስተውሏል። በዚህም በነገው ጨዋታ በርካታ ዕድሎች የፈጠሩበት ቀጥተኛ እና የመስመር አጨዋወት ይመለሳሉ ተብሎ ሲጠበቅ ባለፈው ጨዋታ በጉዳት ያልተሰለፈው አስቻለው ግርማ ከጉዳት መመለሱ ተከትሎም አጨዋወታቸው ይበልጥ መስመር ላይ ያተኮረ ይሆናል ተብሎ ይታመናል።
ሰበታ ከተማዎች ተከላካዮቹ አንተነህ ተስፋዬ እና ሳቪዮን በጉዳት አሁንም የማይጠቀሙ ሲሆን አስቻለው ግርማ እና ባለፈው ጨዋታ ተጠባባቂ ወንበር ላይ ሆኖ ጨዋታውን የጀመረው ባኑ ዲያዋራ ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ሆነዋል፡፡

ጅማ አባ ጅፋር ከአስቸጋሪ የሜዳ ውጪ ሁነቶች በተቃራኒ ጥሩ የሚባል የውድድር ዘመን ጉዞ እያደረገ ይገኛል። ረቡዕ ወልቂጤ ላይ ያሳካውን ድልም በሌላው አዲስ አዳጊ ላይ በመድገም ወደ መሪዎቹ መጠጋትን አልሞ ወደ ሜዳ ይገባል።

የጅማ አባ ጅፋር ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም
አሸነፈ አቻ አሸነፈ አቻ ተሸነፈ

አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው እጅግ ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀትን በጅማ የገነቡ ሲሆን በተለይ ከሜዳ ውጪ በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ቀይ ለባሾቹ ላይ ጎል ማስቆጠር ፈታኝ እየሆነ መጥቷል። በነገው ጨዋታም ጠጣሩን አቀራረብ ይዘው ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ሲጠበቅ ሁለቱ አጥቂዎች ያኩቡ እና ብዙዓየሁ ላይ ያተኮረ የመልሶ ማጥቃት በመሰንዘር ጎል ለማስቆጠር ጥረት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

ጅማ አባ ጅፋር ግብ ጠባቂው ሰዒድ ሀብታሙ፣ አማካዩ ሄኖክ ገምቴሳ እና አጥቂው ብሩክ ገብረአብን በጉዳት አይሰልፍም።

እርስ በርስ ግንኙነት

– የነገው ጨዋታ በሁለቱ ቡድኖች መካከል በሊጉ ለመጀመርያ ጊዜ የሚደረግ ነው።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሰበታ ከተማ (4-3-3)

ዳንኤል አጃይ

ጌቱ ኃ/ማርያም – ወንድይፍራው ጌታሁን – አዲስ ተስፋዬ – ኃ/ሚካኤል አደፍርስ

ታደለ መንገሻ – መስዑድ መሐመድ – ዳዊት እስጢፋኖስ

ባኑ ዲያዋራ – ፍፁም ገ/ማርያም – አስቻለው ግርማ

ጅማ አባ ጅፋር (4-4-2)

መሐመድ ሙንታሪ

ወንድማገኝ ማርቆስ – ከድር ኸይረዲን – መላኩ ወልዴ – ኤልያስ አታሮ

ሀብታሙ ንጉሴ – ንጋቱ ገ/ሥላሴ – ኤልያስ አህመድ – ኤርሚያስ ኃይሉ

ያኩቡ መሐመድ – ብዙዓየሁ እንደሻው


© ሶከር ኢትዮጵያ