ኢንቨርቲንግ ዘ ፒራሚድ | ምዕራፍ ስምንት – ክፍል ሰባት

የጆናታን ዊልሰን Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics የአማርኛ ትርጉም የዛሬው መሠናዶ የስምንተኛው ምዕራፍ ሰባተኛ ክፍልን ይዞላችሁ ቀርቧል።


ከአልፍ ራምሴይ በፊት እንግሊዝን ያሰለጠነው ዋልተር ዊንተርቦተም በሃገሪቱ ብሔራዊ ቡድን ባለ ሙሉ መብት አሰልጣኝ አልነበረም፡፡ ይልቁንም የኮሚቴ አባል ብቻ ሆኖ በተሳተፈበት የተጫዋቾች ምርጫ እንዲሰራ እስከ መገደድ ደርሷል፡፡ ራምሴይ ግን ይህን ጣልቃ-ገብነት በይሁንታ የሚቀበል አዕምሮ አልነበረውም፡፡ እርሱ በሥራው የመጨረሻ ወሳኝ ሰው መሆን ይሻል፡፡ ምክንያቱም ይህን ስልጣን ሳይቆናጠጥ የተለያዩ የታክቲክ አማራጭ ሙከራዎችን ማከናወን አይቻለውም፡፡ ለእያንዳንዱ የሜዳ ላይ ሚና የኮሚቴ አባላት ድምጽ የሰጧቸው ምርጥ-ምርጥ ተጫዋቾች የግድ መካተት ሲኖርባቸው የመከላከልና የማጥቃት ሚዛንን መጠበቅ አዳጋች ይሆናል፡፡ በተጫዋቾች መካከል ሊፈጠር የሚችል አመርቂ ጥምረትም ተገቢውን ትኩረት ያጣል፡፡ ይህ ደግሞ የW-Mን ዋነኛ አበርክቶ በውል ሳይረዱ ፎርሜሽኑ ላይ ጭፍን አልያም ሃሳብ የለሽ እምነት የማሳደር ተግባር ነው፡፡ ቀደም ሲል በፎርሜሽኑ ዙሪያ የታየው ልማድም ይኸው ነበር፡፡ ” ሰዎች ‘ማቲውስ፣ ፊኒ፣ ካርተርና የመሳሰሉት ሌሎች ባለክህሎቶች የሚጫወቱበት እቅድ አያስፈልጋቸውም፡፡’ ሲሉ እሰማለሁ፡፡ እኔ ከላይ ከጠቀስኳቸው አብዛኞቹ ተጫዋቾች ጋር ተጫውቻሉሁ፤ ያኔ የእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን ጠንካራ እንደነበር አውቃለሁ፡፡ ይሁን እንጂ በወቅቱ ወጥ የአጨዋወት ዕቅድ ብንይዝ ኖሮ የበለጠ ጠንካራ አቋም ይኖረን ነበር፡፡” ሲል ራምሴይ ጥንቅቅ ያለ ዝግጅት ማድረግን በሚመለከት በጊዜው እንግሊዛውያን ይሰጡ የነበረውን አስተያየት ይቃወማል፡፡

ራምሴይ ሙሉ ስልጣን የተሰጠው ቡድኑን ከተረከበ ከስምንት ወራት በኋላ በ1963 ግንቦት መጨረሻ ላይ ስለነበር ከኮሚቴው ጋር በመሆን ሁለት ጨዋታዎች ለመምራት ተገዷል፡፡ በመጀመሪያ ጨዋታው ኮሚቴውና ራምሴይ በመረጡት የW-M ፎርሜሽን እንግሊዝ ፈረንሳይን በፓሪስ ገጥማ 5-2 ተረታች፡፡ ይህ ሽንፈት ኮሚቴው ፊቱን የራምሴይ ፍላጎት ወደነበረው 4-2-4 ፎርሜሽን እንዲያዞር ገፋፋው፡፡ ምንም እንኳ ራምሴይ ይህን የተጫዋቾች የሜዳ ላይ እንቅስቃሴያዊ አደራደር መጠቀም እንደጀመረ እንግሊዝ በሜዳዋ በስኮትላንድ 2-1 ድል ብትደረግም እርሱ ግን በእነዚያ ቀደምት የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ጊዜው ይህንኑ ፎርሜሽን የሙጥኝ ብሎ ከርሟል፡፡

የ1964ቱ የውድድር ዘመን ከተገባደደ በኋላ በግንቦት ወር የእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን በደቡብ አሜሪካ ሃገራት ጉዞዎች ሲያደርግ የራምሴይን ታክቲካዊ እድገት ለማረጋገጥ አመቺ አጋጣሚ ተፈጠረ፡፡ እንግሊዝ በኒውዮርክ አሜሪካን 10-0 ረመረመች፡፡ ራምሴይም በ1950ው የዓለም ዋንጫ በቤሎ ሆሪዞንቴ እርሱ በተሰለፈበት ጨዋታ አሜሪካ 1-0 ያሸነፈችበትን ውጤት በሚያስንቅ ሰፊ የጎል ልዩነት ድል አድርጎ ለአስራ አራት ዓመት የቆየ በቀሉን ተወጣ፡፡ ይሁን እንጂ በረዣዥም ርቀት በረራዎች የተዳከመው ቡድን ከሶስት ቀናት በኋላ ብራዚልን እንዲገጥም ቀን ተቆረጠለት፡፡ አራት ቡድኖች በሚካፈሉበት ውድድር ላይ እንግሊዝ ብራዚልን መቋቋም ተስኗት 5-1 ተረታች፡፡ በቀጣዩም ግጥሚያ ከፖርቹጋል ጋር አቻ ተለያየች፡፡ ከአርጀንቲና ጋር የሚካሄደው ሶስተኛው ፍልሚያ ግን እጅጉን ወሳኝ ነበር፡፡ አርጀንቲና የቶርናመንቱ ባለድል ለመሆን የአቻ ውጤት በቂዋ ስለሆነ ወደ ጥንቱና ወርቃማ የ<ላኑዌስትራ> ዘመን ትዝታዋ መመለስ አሰበች፡፡ ተጫዋቾቿ ከኳስ ጀርባ እንዲሆኑ ታዘዙ፤ በዚህም የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን ወስደው ተጋጣሚያቸውን ማዛል መረጡ፡፡ ከጨዋታው በኋላ “እንግሊዛውያኑ ተጫዋቾቾ ውስብስብ ካለ ጎዳና ውስጥ ገብተው መውጣት እንደ ተቸገሩ ባላገሮች ድንብርብር አሉ፡፡” ሲል ዴዝሞንድ ሃኬት <ዴይሊ ኤክስፕሬስ> ላይ ጻፈ፡፡ ሶስቱ አናብስት ጨዋታው ላይ ያሳዩት ቀላል የማይባል ብልጫ ግብ እንዲያስቆጥሩ አላገዛቸውም፤ ከእረፍት መልስም ቢሆን ምንም የተለየ ነገር አልፈጠሩም፤ እንዲያውም በመጨረሻ 1-0 ተሸነፉ፡፡ የአርጀንቲናው አንበል ጆዜ ራሞስ ዴልጋዶ ” ዛጋሎ በ1962ቱ የዓለም ዋንጫ ወቅት የተጫወተውን ሚና ለሮቤርቶ ቴልች ሰጠነውና 4-2-4 ለመተግበር ሞከርን፤ እንግሊዛውያኑ በሙር፣ ቻርልተንና ቶምሰን የተዋቀረ ድንቅ ቡድን ነበራቸው፡፡ ነገርግን እኛ በብልሃት ተጫወትን፤ እንግሊዞቹ ከፍተኛ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ መያዛቸው እውነት ቢሆንም ይህ ሊሆን የቻለው የእነርሱን እንቅስቃሴ የሚከታተል አማካይ ተጫዋች ስላላሰለፍን ነበር፡፡” ይላል፡፡

የአርጀንቲናው ሽንፈት ያንገበገባቸው እንግሊዛውያን ተጫዋቾች ቢኖሩም ጋዜጠኛው ሃኬት ይህ ብዙም የተዋጠለት አይመስልም፤ ቁጭታቸው የሰላ ትችት ከመሰንዘር አላገደውም፡፡ ” የእንግሊዝ ተጫዋቾች የለበሱት መለያ ላይ ሶስቱ አናብስት የሚታዩበት አርማ ባረጁ ዥንጉርጉር ሶስት ድመቶች ምስል መተካት ይችላል፡፡” ብሎ ጽፏል፡፡ በወቅቱ የጋዜጠኛው ሃኬት ተቃውሞ የተለመደ ሆኖ ነበር፡፡ በእርግጥ እንግሊዞች በአግባቡ የተሰናዳ እቅድ ይዞ በሚጫወት ቡድን ቢረቱም የትችቱ ሥረ-መሰረት ሌላ ነው፡፡ በተጫዋቾቹ ዘንድ ከዚያ ቀደም እንደታየው፥ ለወደፊቱም ቢሆን መዘውተሩ እንደማይቀር ለሚገመተው ጠንክሮ የመሥራት ችግር መፍትሄ ካለማበጀታቸው ጋር ይያያዛል፡፡ ያን ጊዜ እንግሊዞች በጨዋታ ወቅት የሚስተዋልባቸው ጥረት አመርቂ አልነበረም፡፡ በመለያቸው ላይ የሚታየውን የአንበሳ ወኔና ኩራት መወከልም አልቻሉም፡፡ የ<ዴይሊ ሜይሉ> ብሪያን ጄምስም በተመሳሳይ ምሬት የብሄራዊ ቡድኑን ብቃት የሚመለከት ትክክለኛ ግምገማ አቅርቧል፡፡

” ለጨዋታ የምትሰጡት ግምት አናሳ ካልሆነ እና በምሽት ክበቦች የምታጠፉትን ጊዜ ለመተው ዝግጁ ከሆናችሁ ምንም ነገር ማሸነፍ ትችላላችሁ፡፡ አርጀንቲናውያኑ ምክንያታዊነታቸውን ለማረጋገጥ የሚችሉትን ያህል ይጥራሉ፤ የእግርኳስ መርሆቻቸውም በዚሁ መንገድ የተረቀቁ ናቸው፡፡ አንደኛው መርህ ‘እነርሱ (ተጋጣሚዎቻቸው) ካላገቡ እኛ አንሸነፍም፡፡’ የሚል ይዘት ነበረው፡፡ የአርጀንቲና ተጫዋቾች ከእነርሱ በማይጠበቅ ንዝህላልነት ጥብቅ አደረጃጀታቸውን መጠበቅ ባልቻሉበት ወቅት ብቻ ነው ክፍተት የሚፈጥሩት፡፡” በማለት ጽፏል፡፡ ራምሴይ በአርጀንቲናውያኑ አጨዋወት ከመመሰጥ ይልቅ ለሩሲያዊው ሙዚቃ ቀማሪ ኤሊች ቻይኮቭስኪ ያለውን ፍቅር መግለጽ ይቀለው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ አሰልጣኙ በአህጉሪቱ ጉብኝት በሁለቱ የደቡብ አሜሪካ ታላላቅ የእግርኳስ ሃገራት (ብራዚልና አርጀንቲና) እና እንግሊዝ መካከል ሰፊ ልዩነት ስለመኖሩ አረጋግጧል፡፡ የ1966ቱን የዓለም ዋንጫ ድል አስመልክቶ የእንግሊዝ እግርኳስ ማህበር ባሰናዳው ዘገባ ላይ ያ የላቲን አሜሪካው ጉዞ ምን ያህል ጠቃሚ እንደነበር የሚያሳይ ማስታወሻ ጽሁፍ አለማስፈሩ የሚገርም ሆኗል፡፡

በ1964 የክረምቱ ወራት ራምሴይ የጨዋታ እቅዱን በተመለከተ ድጋሚ በጥልቀት አሰበበት፡፡ የአጨዋወት ሥርዓት (Playing System) ከተጫዋቾችም (Personnel) በላይ ጠቃሚ እንደሆነ የተረዳ መሰለ፡፡ በእርግጥ የእንግሊዛዊውን አሰልጣኝ ቁጥብ ባህርይ ላስተዋለ የውሳኔው አስተማማኝነት ላይ ጥርጣሬ ሊያድርበት ይችላል፡፡ ነገርግን ከ1964 በኋላ በነበሩት ሁለት ዓመታት ውስጥ ጥንቃቄ የታከለባቸው የሒደት ለውጦችን እያሳየ የአለም ዋንጫን ማንሳት መቻሉ አጠያያቂ አይደለም፡፡ በ4-2-4 ፎርሜሽን በሜዳው ቁመት የጎን መስመሮቻቸውን ታክከው የሚሰለፉት (Wide Players) ቦቢ ቻርልተን እና ፒተር ቶምሰን ወደኋላ እየተመለሱ የመጫወት ዝንባሌ አልነበራቸውም፡፡ ሁለቱ የመሃል አጥቂዎች (Centre-Forwards) ጂሚ ግሪቭስና ጆኒ በርንም እንዲሁ ወደኋላ የማፈግፈግ ሚና አላሳዩም፡፡ ራምሴይ ተጫዋቾቹ ይህን ድርብ ኃላፊነት እንዲወጡ ቢጠይቃቸውም እነርሱ ግን በእንቢታቸው ጸኑ፡፡ ጆርጅ ኢስትሃም በመደበኛነት ከመሃል አማካዮች አንደ አንዱ ሆኖ መጫወት ከመጀመሩ በፊት ከመሃል አጥቂ ጎን የሚሰለፍ የፊት መስመር ተጫዋች (Inside Forward) ነበር፡፡ ተጣማሪው ጎርደን ማልንም እንዲሁ፡፡ ራምሴይ 4-2-4 ዝቅተኛ ደረጃ የሚሰጣቸውን ተጋጣሚዎች ለመርታት የሚያስችል ፎርሜሽን መሆኑን ቢገነዘብም ከጠንካራ ተፎካካሪዎች ጋር ለመፋለም ግን አመቺ እንዳልሆነ ገብቶታል፡፡ እንዲያውም የተሻለው ቡድን ገዳም ቀኑ ካልሆነ ፎርሜሽኑ ብዙ ተጋላጭ የሚያደርጉ ጎኖች እንዳሉት አሰላስሏል፡፡ የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን ለሚወስድ ቡድን 4-2-4 ጥሩ አማራጭ ሊሆን ይችላል፤ ነገርግን በመጀመሪያ ደረጃ ኳስን ከተጋጣሚ ቁጥጥር ውጭ ለማድረግ አለማስቻሉ የፎርሜሽኑ አይነተኛ ችግር ነበር፡፡

ራምሴይ የማንችስተር ዩናይትዱን ግዙፍ አማካይ ኖቢ ስታይልስ ሲመርጥ ብዙዎች ግልጽ አልሆነላቸውም ነበር፡፡ ስታይልስ በ4-2-4 ፎርሜሽን ቦታ የሚያገኝ ተጫዋች እንዳልነበር የታወቀ ነው፡፡ የተጫዋቹ ነባር ችሎታ ግንዛቤ ውስጥ ሳይገባ ኳስን ከኋላ እየተቀበለ ወደፊት የማንሸራሸርና የመፍጠር ኃላፊነት በእርሱ ላይ ተጣለ፡፡ ቶምሰን ደግሞ የዚህ የተጫዋቾች ሚና ሽግሽግ ሰለባ ሆኖ አረፈው፡፡ በብራዚሉ ጉዞ በእንግሊዝ ቡድን ውስጥ ምርጡ ተጫዋች ቶምሰን የነበረ መሆኑ ጥያቄ የሚነሳበት አልነበረም፡፡ በሃገሬው ጋዜጦች “ነጩ ፔሌ” የሚል ተቀጽላ እስከማግኘት የደረሰው ቶምሰን በስታይልስ መመረጥ የተነሳ ቦታ አጣ፡፡ ለራምሴይ አዲሱ የአጨዋወት እሳቤ የሊቨርፑሉ የመስመር አማካይ እጅጉን የቅንጦት አማራጭ ሆነ፤ ተመልካችን ለማዝናናት እንጂ የአሰልጣኙን ፍላጎት የሚያሳካ አልመስል አለው፡፡ ስለዚህም ራምሴይ ለእነ ጆን ኮኖሊ፣ ያን ካላያን እና ቴሪ ፔይን ጥሪ ሲያደርግ ቶምሰን ቀስ በቀስ ከአሰልጣኙ እቅድ ውጪ መሆኑን እየተረዳ መጣ፡፡

አዲሱ የውድድር ዘመን ሲጀምር በጥቅምት ወር እንግሊዝ ወደ ሰሜን አየርላንድ አቅንታ ከጎረቤት ሃገር ጋር ተጫወተች፡፡ በዚህም ጨዋታ ራምሴይ 4-2-4ን ተገበረ፡፡ ይሁን እንጂ የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋቾች ከተለመደ ሚናቸው ውጪ ሌላ ኃላፊነት ተሰጥቷቸው ታዩ፤ ቦቢ ቻርልተን ወደኋላ አፈግፍጎ በመሃለኛው የሜዳ ክፍል ላይ የጆርጅ ኢስትሃምን ሚና መወጣት ጀመረ፤ ፔይን ደግሞ በቀኝ መስመር ወደኋላ እየተመለሰ እንደ ዛጋሎ አልያም ሊድቤተር እንዲጫወት ተደረገ፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ እንግሊዝ 4-0 መምራት ብትችልም ጨዋታው ግን 4-3 ተጠናቀቀ፡፡ <ዘ-ሜይል> የተሰኘው ጋዜጣ “ዘጠና የመዝረክረክ ደቂቃዎች” በማለት የራምሴይን ቡድን ተቸ፡፡ አሰልጣኙ ራሱ በቡድኑ የአቋም መንሸራተት ተቆጥቶ ስለነበር ከጋዜጠኞች ጋር እሰጣገባ ውስጥ ተዘፈቀ፡፡ እቅዱን የመቀየር ምንም ፍላጎት አልነበረውምና ለመገናኛ ብዙኃኑ ዘለፋ “ጆሮ ዳባ ልበስ” አይነት አቋም አሳየ፡፡ ከዚያም ምንም በማያስተማምን ብቃት እንግሊዝ ከቤልጂየም 2-2 አቻ የተለያየችበት ጨዋታ ተከተለ፡፡ በየካቲት 1965 ግን የራምሴይ ዋነኛ ግኝት ፍንጭ የታየበት ወቅት ሆነ፡፡ ጎርደን ባንክስ፣ ቦቢ ቻርልተንና ፒተር ቶምሰንን ጨምሮ ስድስት ተጫዋቾች ለእግርኳስ ማህበሩ ጨዋታዎች ሲባል ከብሄራዊ ቡድን ምርጫ ተዘለሉ፡፡ ይሁንና ራምሴይ በእቅዱ መሠረት መሥራቱን አላቆመም፡፡ የዋናው ቡድን አባላት 4-3-3 ፎርሜሽን ተጠቅመው ከሃያ ሶስት ዓመት በታች የወጣት ቡድኑ ጋር የልምምድ ግጥሚያ እንዲያደርጉ አዘጋጃቸው፡፡ በውጤቱም ራምሴይ እጅግ ደስተኛ ሆኖ ታየ፡፡

” ወጣቶቹን ተጫዋቾች በጣም አሞኝቻቼዋለሁ፤ የዋናውን ቡድን ተጫዋቾች መቆጣጠር የሚችሉበትን ሥልት ሳልነግራቸው አስገባኋቸው፡፡ ዋናው ቡድን በመሃለኛው ክፍሉ ላይ ሶስት እጅግ ወሳኝ ተጫዋቾች ነበሩት፡፡ ብሪያን ዳግላስ በቀኝ፣ ጆኒ በርን በመሃል፣ ጆርጅ ኢስትሃም ደግሞ በግራ ተሰልፈው ከወጣቶቹ ጋር ተፋለሙ፡፡ ያኔ <ክንፍ አልባዎቹ በራሪዎች/Wingles Wonders> ተፈጠሩ፡፡” ይላል አልፍ ራምሴይ፡፡ ” በመስመሮች ላይ ብቻ ታክከው የሚጫወቱ ሁለት አማካዮችን መጠቀም ቅንጦት ነው፡፡ በተለይ ተጋጣሚ ቡድን በሚያጠቃ ጊዜ በዘጠኝ ተጫዋች የመጋፈጥ ሁኔታ እንዲፈጠር ያደርጋልና፡፡” ሲል ተለምዷዊዎቹ የመሥመር አማካዮች (Wingers) በመከላከሉ ሒደት የነበራቸውን ዝቅተኛ ተሳትፎ በአጭሩ ያብራራል፡፡

ከ1964-1974 ድረስ የዌልስ ብሄራዊ ቡድንን ያሰለጠነው ዴቭ ቦዌን በመላው ብሪታንያ ከየትኛውም የእግርኳስ ባለሙያ በበለጠ የራምሴይ ምጡቅ እሳቤዎች ተቀባይነት ማግኘት እንደነበረባቸው ያምናል፡፡ ቦዌን እንደሚለው ቡድኖች አራት የኋላ መስመር ተከላካዮችን ማሰለፍ ሲጀምሩ ተለምዷዊ የመስመር አማካዮች (Traditional Wingers) አስፈላጊነት ያከትማል፡፡ ” በሶሥት ተከላካዮች መጫወት ለየት ይላል፤ ከተከላካዮቹ በላይኛው መስመር የሚገኘው ክልል በተጋጣሚ ቡድን የመሃል-ተከላካይ አማካዩ (Centre-Half) ጥላ ሥር ስለሚሆን በዚያ በኩል የሚሰለፈው የመስመር አማካይ ከሌላኛው ተቃራኒ መስመር የሚላኩ ተሻጋሪ ቅብብሎችን የሚሻማበት ጊዜ፣ ነጻነትና ቦታ ይኖረዋል፡፡ አራት ተከላካዮች ሲሆኑ ግን የሚከላከለው ቡድን የመስመር ተከላካዮች የሚያጠቃው ቡድን የመስመር አማካዮች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ያደርጋሉ፡፡ ስለዚህ የመስመር አማካዮቹ እንዳሻቸው የሚጋልቡበት ክፍተት (Acceleration Space) አይኖራቸውም፡፡ በዚህም ሳቢያ ተመራጭነታቸው ገደል ይገባል፡፡ ያ ከሆነ ደግሞ የመስመር አማካዮች ህልውና ያበቃል፡፡” በማለት ያብራራል፡፡

ራምሴይ ሊተገብር ያቀደውን ፎርሜሽን ከወሰነ በኋላ ለዕቅዱ ተስማሚ የሆኑ ምርጥ ተጫዋቾችን ማሰስ ጀመረ፡፡ በሚያዝያ ስታይልስና ጃክ ቻርልተን የመጀመሪያ ጨዋታቸውን እንግሊዝ ከስኮትላንድ ጋር 2-2 አቻ በተለያየችበት ግጥሚያ ማድረግ ቻሉ፡፡ በቀጣዩ ወር አላን ቦል እንግሊዝ ከዩጎዝላቪያ ጋር 1-1 አቻ ስትወጣ የተሰላፊነት ዕድል ተሰጠው፡፡ ደግሞ በቀጠለው ወር እንግሊዝ ከምዕራብ ጀርመን ጋር በኑረንበርግ የወዳጅነት ስታደርግ ራምሴይ ለ4-3-3 ፎርሜሽን ቅድሚያ እንደሚሰጥ ግልጽ አደረገ፡፡ የዎልቭሱ ሮን ፍላወርስ ስታይልስን ተካው፤ ቦል የመሃል አማካይነት ሚና እንዲኖረው ተደረገ፤ የሊድስ ዩናይትዱ ሚክ ጆንስና ኢስትሃም የፊት መስመሩን ይመሩ ጀመር፡፡ ለሃገሩ በዚህ ጨዋታ ብቻ የተጫወተው የኤቨርተኑ ዴሬክ ቴምፕል እና ፔይን ደግሞ ከመስመሮች በመነሳት እየተፈራረቁ በመጫወት ለመሃል ክፍሉም ድጋፍ ማድረግ ቻሉ፡፡ እንግሊዝ ጨዋታውን 1-0 አሸነፈች፤ ቀጠለችና ሲውዲንን 2-1 ረታች፡፡ በስታይልስ ወደ ሜዳ መመለስ ምክንያተሸ የፎርሜሽን ለውጥ ሳይደረግ ቀረ፤ ራምሴይ በዚሁ የተጫዋቾች የሜዳ ላይ እንቅስቃሴያዊ አደራደር መቀጠል መረጠ፡፡ በዚህ የአጨዋወት ሥልት አላን ቦል ሁነኛ ተጫዋች ሆነ፡፡ ቦል በነበረው ከፍተኛ ወኔና አይደክሜ ባህርይ ልክ ብራዚላዊው ዛጋሎ በ1962ቱ የዓለም ዋንጫ ወቅት እንዳደረገው በመስመር አማካይነት (Winger) አልፎአልፎም ለመሃል አማካዮች ድጋፍ በማድረግ (Auxiliary Midfielder) የተዋጣለት ግልጋሎት ማበርከት ቻለ፡፡

ይቀጥላል...


ጆናታን ዊልሰን ዝነኛ እንግሊዛዊ የስፖርት ጋዜጠኛ ሲሆን በተለያዩ ጋዜጦች፣ መጽሄቶች እና ድረገጾች ላይ ታክቲካዊና ታሪካዊ ይዘት ያላቸው የእግርኳስ ትንታኔዎችን የሚያቀርብ ጉምቱ ጸኃፊ ነው፡፡ ባለፉት አስራ ሦስት ዓመታትም አስር መፅሐፍትን ለህትመት አብቅቷል፡፡