ሪፖርት | ሰበታ ከተማ ጅማ አባጅፋርን አሸነፈ

በ8ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመክፈቻ ጨዋታ አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ጅማ አባ ጅፋርን ያስተናገደው ሰበታ ከተማ ወደ አሸናፊነት የተመለሰበትን የ3-1 ድል አሳክቷል።

ሰበታዎች ባሳለፍነው ሳምንት በትግራይ ስታዲየም በስሑል ሽረ ከተረታው ስብስብ ውስጥ ሁለት ቅያሬዎችን ሲያደርግ በዚህም ጌቱ ኃይለማርያም እና ናትናኤል ጋንቹላን አስወጥተው በምትካቸው ኢብራሂም ከድር እና ባኑ ዲያዋራን ወደ መጀመርያ ተሰላፊነት በማስገባት ሲጀምሩ በአንፃሩ ጅማዎች ወልቂጤን ከረታው ስብስብ ውስጥ አምረላ ደልታታ እና ብዙዓየሁ እንደሻውን አስወጥተው በምትካቸው ጀሚል ያዕቆብ እና ሱራፌል ዐወልን በማካተት ጨዋታውን ጀምረዋል።


ብዙም ጠንካራ ፉክክር ባልተመለከትንበት የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ገና ጨዋታው ብዙም ሳይጓዝ በ6ኛው ደቂቃ መላኩ ወልዴ በኃይለሚካኤል አደፍርስ ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ፍፁም ገ/ማርያም አስቆጥሮ ቡድኑን ገና ከጅምሩ መሪ ማድረግ ችሏል።

ከጅምሩ ግብ በመቆጠሩ ጨዋታው ይነቃቃል ተብሎ ቢጠበቅም ጨዋታው ላይ ይህ ነው የሚባል እንቅስቃሴ መመልከት አልቻልንም። ጅማዎች ምንም እንኳን ግብ ቢዳስተናግዱም እንደ ወትሮው ሁሉ በራሳቸው ሜዳ ላይ ከምቸት ብለው ሲጫወቱ ተስተውሏል። በአንፃሩ የተሻሉ የነበሩት ሰበታዎች በ16ኛው ሳሙኤል ታዬ ከማዕዘን ያሻማውን ኳስ ባኑ ዲያዋራ ነጻ አቋቋም ላይ ሆኖ በግንባር የገጨውና ወደ ውጭ የወጣበት እንዲሁም በ22ኛው ደቂቃ ራሱ ባኑ ዲያዋራ ከረጅም ርቀት ወደ ጎል የላካትና ለጥቂት ወደ ውጭ በወጣችበት ግሩም የቅጣት ምት ኳስ ሙከራዎች ማድረግ ችለዋል።


ከዕረፍት መልስ ልክ እንደመጀመሪያው ሁሉ ሰበታዎች ገና በጊዜ ነበር ልዩነታቸውን ያሰፉበትን ግብ ያስቆጠሩት። በ50ኛው ደቂቃ ባኑ ዲያዋራ ከግራ መስመር መላኩ ወልዴን አታሎ ወደ መሀል ያሳለፈውን ኳስ መስዑድ መሐመድ እንደመጣ በመምታት በግሩም ሁኔታ የቡድኑን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ያደረገችውን ግብ ማስቆጠር ችሏል።
በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ የማጥቃት ባህሪ ያላቸውን ተጫዋቾች በማስገባት ውጤቱን ለመቀልበስ ጥረት ያደረጉት ጅማዎች ከመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ ሆነው እንዲቀርቡ አስችሏል። በ55ኛው ደቂቃ መሐመድ ያኩቡ ከቅጣት ምት በቀጥታ አክርሮ የመታት ኳስ የግቡን አግዳሚ ለትማ ስትመለስ በ65ኛው ደቂቃ በጨዋታው ሲታትር የዋለው መሐመድ ያኩቡ ኤልያስ አህመድ ከቀኝ መስመር ያሻገረለትን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ በማስቆጠር ቡድኑን ወደ ጨዋታ ልትመልስ የምትችል ግብ ማስቆጠር ችሎ ነበር።

በተመሳሳይ በ72ኛው ደቂቃ በሁለተኛው አጋማሽ በጅማዎች በኩል ተቀይሮ የገባው ኤርሚያስ ኃይሉ በግሩም የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚ ከንጋቱ ገ/ሥላሴ የደረሰውን ግሩም ኳስ ሳይጠቀምበት ቀረ እንጂ ቡድኑን አቻ ማድረግ የምትችል አጋጣሚ ነበረች። ከ3 ደቂቃዎች በኋላም ከመሐል የተሻገረውን ኳስ ሲይላ ዓሊ የጅማ ተከላካዮች እና ግብጠባቂው ሙንታሪን ስህተት ተጠቅሞ የቡድኑን አሸናፊነት ያረጋገጠች ሦስተኛ ግብ በቀላሉ ማስቆጠር ችሏል።

በጨዋታው መገባደጃ ደቂቃዎች ላይ ባኑ ዲያዋራና ሲይላ ዓሊ ለሰበታ ከተማ ተጨማሪ ግብ ማስቆጠሪያ አጋጣሚዎች ቢያገኙም መጠቀም ሳይችሉ ቀርተው ጨዋታው በሰበታ 3ለ1 አሸናፊነት ሊጠናቀቅ ችሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ