ቅድመ ዳሰሳ | ፋሲል ከነማ ከ ኢትዮጵያ ቡና

በቡድኖቹ የአጨዋወት ባህርይ ምክንያት የ8ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተጠባቂ መርሐ ግብር የሆነውን የፋሲል ከነማ እና የኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ እንደሚከተለው ተመልክተነዋል።

በሜዳቸው የማይቀመሱት ዐፄዎቹ ዳግም ወደ አሸናፊነት እና ወደ ሊጉ መሪነት ለመመለስ የነገውን መርሐ ግብር ይጠባበቃሉ።

የፋሲል ከነማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም
አቻ አሸነፈ አቻ አሸነፈ ተሸነፈ

በአሰልጣኝ ሥዩም ከበደ የሚሰለጥነው ቡድኑ በሜዳው ሲጫወት ከፍተኛ የጨዋታ የበላይነትን ሲወስድ ይታያል። በተለይ ቡድኑ ያላቸውን ለመስጠት በማይቦዝኑት የአማካይ መስመር ተጫዋቾቹ ብቃት በመታገዝ ኳስን በትዕግስት ሲያንሸራሽሽር እና የተጋጣሚን ክፍተት ከመፈለግ ባሻገር ከተለያዩ አቅጣጫዎች ፋታ የለሽ ጥቃት በመሰንዘር የጎል ዕድል ሲፈጥር ይታያል። ነገር ግን በነገው ጨዋታ ይህን የጨዋታ የበላይነት ተጋጣሚው ኢትዮጵያ ቡና ከሚከተለው የጨዋታ ዘይቤ አንፃር በቀላሉ እንደማያገኘው ይታሰባል። ይህንን ተከትሎ በነገው ጨዋታ ቡድኑ ፈጣን ሽግግሮችን እንደሚከተል እና ረጃጅም ተሻጋሪ ኳሶችን በመስመር በኩል እንደሚያዘነብል ይገመታል።

ፋሲሎች በነገው ጨዋታ የኢትዮጵያ ቡናን የኳስ ቅብብሎች መስመር ለማጨናገፍ በማሰብ ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይታሰባል። በተለይ በተከላካይ እና በአማካይ መስመር ተጨዋቾች መካከል የሚደረጉ የቅብብል አማራጮችን መስመር (passing line) በመዝጋት በጎ ነገሮችን ለቡድናቸው ለማምጣት እንደሚጥሩ ይጠበቃል።

በማጥቃት እንቅስቃሴ እንዲሳተፉ በአብዛኛው ፍቃድ የሚሰጣቸው የፋሲል የመስመር ተከላካዮች በነገው ጨዋታ ከቡና የመስመር አጥቂዎች ፈተናን እንደሚቀበሉ ይታሰባል። በተለይ ተጨዋቾቹ ከማጣየጥቃት ወደ መከላከል በሚያደርጉት ሽግግር በፍጥነት ቦታቸውን የማያስከብሩ ከሆነ ከፊታቸው ከተሰለፉት ፈጣን እና ቀልጣፋ የመስመር አጥቂዎች (ምናልባት አቡበከር እና ሚኪያስ) ችግር ውስጥ ሊገቡ ይችላል።

ፋሲል ከነማዎች ምንም የጉዳት እና የቅጣት ዜና የለባቸውም። በአንፃሩ ለአጭር እና ረጅም ጊዜ ጉዳት አስተናግደው ከጨዋታ ርቀው የነበሩት ሰለሞን ሀብቴ፣ እንየው ካሳሁን፣ ያሬድ ባዬ እና አብዱረህማን ሙባረክ ቀላል ልምምድ በመጀመር ወደ ስብስቡ ገብተዋል።

የኢትዮጵያ ቡና ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም
ተሸነፈ አሸነፈ አቻ አሸነፈ አቻ

ከጨዋታ ጨዋታ መሻሻሎችን እያሳየ ያለው ኢትዮጵያ ቡና የመጀመሪያ የሜዳ ውጪ ድሉን ጎንደር ላይ ለማጣጣም ወደ ሜዳ ይገባል።

ለኳስ ቁጥጥር ከፍተኛ ቦታን የሚሰጠው ቡድኑ በነገው ጨዋታ ከባለሜዳዎቹ ፈተናን ያስተናግዳል ተብሎ ይጠበቃል። በተለይ ሁለቱ ቡድኖች ለኳስ ቁጥጥር የሚያደርጉት የበላይነት ከወዲሁ በጉጉት የሚጠበቅ የትኩረት ነጥብ ነው።

ሁለተኛው ብዙ ግቦች (12) ካስቆጠሩ ክለቦች (ከባህር ዳር እና ሲዳማ ቡና ጋር እኩል) መካከል አንዱ የሆነው ኢትዮጵያ ቡና የሊጉ ጅማሮ ላይ ሲቸገርበት የነበረውን የግብ ማስቆጠር ቀመር አሁን ያገኘው ይመስላል። ይህ የጎል ማስቆጠር ሂደት ደግሞ የቡድኑን የራስ መተማመን ወደተሻለ ደረጃ እንዲሸጋገር ያደርገዋል።

በመሐል ለመሐል እንዲሁም በመስመር አጨዋወት ተጋጣሚን ለማስጨነቅ የሚጥረው ቡድኑ ነገም የጨዋታ ስልቱን እየቀያየረ ፋሲልን እንደሚረብሽ ይጠበቃም። በተለይ የቡድኑ የመስመር አጥቂዎች በደንብ የሜዳውን የጎንዮሽ ስፋት በመጠቀም የፋሲልን የመከላከል አደረጃጀት ለማፋለስ እንደሚጥሩ ይታሰባል።

ኳስ ከግብ ጠባቂ ሲጀምሩ አደጋን ራሳቸው ላይ በሚጋብዝ መልኩ የሚጀምሩት ቡናዎች በነገው ጨዋታም ከታታሪዎቹ የፋሲል ከነማ ተጫዋቾች ጫናዎች እንደሚፈጠሩባቸው ይገመታል። ከዚህ የማስጨነቅ አጨዋወት ራሳቸውን ለማውጣት እቅዶችን ነድፈው ወደ ሜዳ ካልገቡ ሊቸገሩ ይችላሉ።

ቡናማዎቹ በነገው ጨዋታ የአቤል ከበደን ግልጋሎት በቅጣት አያገኙም። በአንፃሩ እንዳለ ደባልቄ እና ታፈሰ ሰለሞን ከጉዳታቸው በማገገማቸው ለነገው ጨዋታ ዝግጁ መሆናቸው ተጠቁሟል።

እርስ በእርስ ግንኙነት

– ከ2009 የውድድር ዓመት ጀምሮ ክለቦቹ በተገናኙባቸው ስድስት ጨዋታዎች ተመጣጣኝ ውጤት አላቸው። ሁለት ሁለት ጊዜ ሲሸናነፉ ሁለት ጊዜ ያለግብ ተለያይተዋል። ኢትዮጵያ ቡና ሰባት ፋሲል ከነማ ደግሞ አምስት ግቦችን አስቆጥረዋል

ግምታዊ አሰላለፍ

ፋሲል ከነማ(4-3-3)

ሚኬል ሳማኬ

ዓለምብርሀን ይግዛው – ሰዒድ ሀሰን – ከድር ኩሊባሊ – አምሳሉ ጥላሁን

በዛብህ መለዮ – ሀብታሙ ተከስተ – ሱራፌል ዳኛቸው

ኦሲ ማውሊ – ሙጂብ ቃሲም – ሽመክት ጉግሳ

ኢትዮጵያ ቡና(4-3-3)

በረከት አማረ

ኃይሌ ገ/ተንሳይ – ፈቱዲን ጀማል – ወንድሜነህ ደረጀ – አስራት ቱንጆ

ፍ/የሱስ ተ/ብርሃን – ዓለምአንተ ካሣ – አማኑኤል ዮሐንስ

ሚኪያስ መኮንን – እንዳለ ደባልቄ – አቡበከር ናስር


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ