ነገ በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚደረገውን የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የድሬዳዋ ከተማን ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።
እጅግ ወጣ ገባ አቋም በማሳየት ላይ የሚገኙት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በሜዳቸው የዓምና የሊጉ ዋንጫ ባለቤት መቐለ 70 እንድርታን በመርታት ያገኙትን የማሸነፍ መንገድ ዳግም ለማግኘት እና ከደጋፊ ጫና ለመውጣት 9 ሰዓትን ይጠባበቃሉ።
የቅዱስ ጊዮርጊስ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም | ||||
አቻ | አሸነፈ | ተሸነፈ | አቻ | አቻ |
የሚከተሉት የጨዋታ ዘይቤ እስካሁን ጥርት ብሎ ያልታወቀው ቅዱስ ጊዮርጊሶች በአመዛኙ ቀጥተኛ አጨዋወትን በመከተል ጨዋታዎችን እያደረጉ ይገኛል። በተለይ አንጋፋዎቹ አጥቂዎቻቸውን ቶሎ ቶሎ በእንቅስቃሴ ውስጥ ለማግኘት የሚጥሩት ጊዮርጊሶች ብዙም ፍሬያማ ሲሆኑ አይታይም። ነገር ግን ተጋጣሚያቸው ድሬዳዋ ከተማዎች ካላቸው የደከመ የመከላከል አደረጃጀት አንፃር ቡድኑ በጎ ነገሮችን ከነገው ጨዋታ እንዲያገኝ ሊሆን ይችላል።
ጨዋታው ሲጀምር በ4-4-2 የተጨዋች አደራደር ቅርፅ ነገር ግን በእንቅስቃሴ ውስጥ በተደጋጋሚ ወደ 4-3-3 የጨዋታ አስተላለፍ በመሄድ የሚጫወቱት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በነገው ጨዋታ ከተለያዩ አማራጮች ግቦችን ለማስቆጠር እንደሚጥሩ ይገመታል። በተለይ ከመስመር አማካይነት ከሚነሱት ተጨዋቾቻቸው ልዩነቶችን ለመፍጠር እንደሚታትሩ ይታሰባል። ከዚህ በተጨማሪም አቤል፣ ጌታነህ እና ሳልሃዲን የሚፈጥሩት የእርስ በእርስ መስተጋብር ለድሬዳዋ ተከላካዮች ራስ ምታት እንደሚሆን ቀድሞ ማስቀመጥ ይቻላል።
ቡድኑ በወረቀት ደረጃ አስፈሪ የፊት መስመር ቢይዝም ግቦችን የማስቆጠር የበዛ ችግር እንዳለበት ታይቷል። በሰባተኛው ሳምንት ከሀዋሳ ከተማ ጋር በተደረገው ጨዋታ እጅግ በርካታ የጎል እድሎችን ፈጥረው ወደ ግብነት መቀየር አለመቻላቸውም ይህን በነገው ጨዋታ አርመው መግባት ይጠበቅባቸዋል። በተቃራኒው ድሬዳዋዎች ያለባቸውን የመከላከል ችግር አስተካክለው ከቀረቡ እና በይበልጥ ወደ ራሳቸው የግብ ክልል አፈግፍገው ቦታዎችን ከነፈጓቸው ቡድኑ ሊፈተን ይችላል።
ቅዱስ ጊዮርጊሶች በነገው ጨዋታ የግብ ጠባቂያቸው ለዓለም ብርሃኑ እና የአማካያቸው ናትናኤል ዘለቀን ግልጋሎት በጉዳት ምክንያት አያገኙም።
የድሬዳዋ ከተማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም | ||||
ተሸነፈ | አሸነፈ | አቻ | ተሸነፈ | አሸነፈ |
ባሳለፍነው ሳምንት በሜዳቸው በወልዋሎ ዓ/ዩ 2-0 የተረቱት ተጋባዦቹ ሲዳማ ቡና ላይ የተቀዳጁትን የሜዳቸው ውጪ ድል ለመድገም እና ካሉበት የወራጅ ቀጠና ቦታ ፈቀቅ ለማለት ወደ ሜዳ ይገባሉ።
ግቡን በሚገባ መጠበቅ ያልቻለው የስምዖን ዓባይ ቡድን እስካሁን በተደረጉ 7 የሊጉ ጨዋታዎች 14 ግቦችን አስተናግዷል። እርግጥ ቡድኑ ከወገብ በታች የተፍረከረከ ቢሆንም ከተጋጣሚው ቅዱስ ጊዮርጊስ በአንድ የበለጠ (5) የሊግ ግቦችን አስቆጥሯል። በነገው ጨዋታም ካለበት ድክመት በመነሳት ወደ ራሱ የግብ ክልል በመጠጋት ጨዋታውን እንደሚያከናውን ይጠበቃል። ለዚህ የጨዋታ እንቅስቃሴ ደግሞ በርከት ያሉ የአማካይ መስመር ተጨዋቾችን ወደ ሜዳ በማስገባት ወንፊት የሆነውን የኋላ መስመር ለማጠናከር እንደሚሞክር ይታሰባል።
ከዚህ ውጪ ቡድኑ ሪችሞንድ አዶንጎን ያነጣጠሩ ረጃጅም ኳሶችን ከፈጣን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴዎች ጋር በማጀብ ለጨዋታው እንደሚቀርቡ ይገመታል። ይህንን እንቅስቃሴ ለማስጀመር እና ለማፋጠን ደግሞ የኤሊያስ ማሞ ብቃት ወሳኝ ነው። ስለዚህ በድሬዳዋዎች በኩል ኤሊያስ ማሞ ቁልፍ ኳሶችን ወደ ፊት መስመር በማድረስ ጊዮርጊሶችን ለመፈተን እንደሚጥር ይገመታል። ሆኖም በተሻጋሪ እና የአየር ላይ ኳሶች የመከላከል ጥንካሬው የሚታወቀው ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ ጎል ማስቆጠር ፈታኝ ሊሎንባቸው ይችላል።
ከላይ ለማስቀመጥ እንደተሞከረው ቡድኑ ያለበትን የግብ ማስተናገድ አባዜ ካላስተካከለ በነገው ጨዋታ በቀላሉ እጁን ሊሰጥ ይችላል። በተለይ በመስመር ላይ የሚደረጉ ጥቃቶችን በአግባቡ የማይመክት ከሆነ ሦስት ነጥቦችን አስረክቦ ሊመለስ ይችላል።
ድሬዎች በነገው ጨዋታም ምንያህል ተሾመ ፣ አማኑኤል ተሾመ ፣ ሳሙኤል ዘሪሁን እና በረከት ሳሙኤልን በጉዳት አያሰልፉም። ባለፈው ሳምንት ያልተሰለፈው ሳምሶን አሰፋም የመድረሱ ነገር አጠራጣሪ ነው።
እርስ በእርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ቡድኖች በፕሪምየር ሊጉ 16 ጊዜ ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 11 በማሸነፍ የበላይነቱን ሲይዝ ድሬዳዋ ከተማ 3 አሸንፏል፡፡ ሁለት ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል፡፡ ጊዮርጊስ 28 ጎሎችን ሲያስቆጥር ድሬዳዋ 12 ጎሎች አሉት።
ግምታዊ አሰላለፍ
ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-4-2)
ባህሩ ነጋሽ
ደስታ ደሙ – አስቻለው ታመነ – ኤድዊን ፍሪምፖንግ – ሄኖክ አዱኛ
ጋዲሳ መብራቴ – ሙሉዓለም መስፍን – ሀይደር ሸረፋ – አቤል ያለው
ጌታነህ ከበደ – ሳላሀዲን ሰዒድ
ድሬዳዋ ከተማ (4-4-1-1 / 4-5-1)
ፍሬው ጌታሁን
ፍሬዘር ካሣ – ዘሪሁን አንሼቦ – ያሲን ጀማል – አማረ በቀለ
ዋለልኝ ገብሬ – ፍሬድ ሙሸንዲ – ቢኒያም ፆመልሳን – ያሬድ ታደሰ
ኤልያስ ማሞ
ሪችሞንድ ኦዶንጎ
© ሶከር ኢትዮጵያ