ቅድመ ዳሰሳ | ወልዋሎ ከ ሀዲያ ሆሳዕና

የሊጉ መሪ ወልዋሎ እና ግርጌ ላይ የሚገኘው ሀዲያ ሆሳዕናን የሚያገናኘውን ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

ከተከታታይ ድል አልባ ጉዞ በኃላ ከሜዳቸው ውጪ ድሬዳዋ ከተማን አሸንፈው ወደ ሊጉ አናት የተመለሱት ቢጫ ለባሾቹ በተከታታይ ጨዋታዎች በሜዳቸው ላይ ያጡትን ሦስት ነጥብ ለማሳካት ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይገመታል።

የወልዋሎ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም
አሸነፈ አቻ ተሸነፈ አቻ አሸነፈ

በወሳኝ ተጫዋቾች ጉዳት ምክንያት የአማራጭ ጥበት ያጋጠማቸው ወልዋሎዎች ተጫዋቾቹ ከጉዳት ባለመመለሳቸው ለውጦች ያደርጋሉ አይጠበቅም። ቡድኑ ባለፉት ጨዋታዎች በጨዋታ መሀልም በማይቀያየር የረጅም ኳስ አጨዋወት የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት ያደረገ ሲሆን በዚ ጨዋታ ግን በተጋጣሚ አቀራረብ ምክንያት አጨዋወታቸው የሚቀይሩበት ዕድል የሰፋ ነው።

ቢጫ ለባሾቹ የተጋጣሚን ረጃጅም ኳሶች ለመመከት የማይቸገሩት እንደ ደስታ ጊቻሞ ፣ አዩብ በቀታ እና በረከት ወልደዮሐንስን አይነት ግዙፍ ተከላካዮች ያሏቸው ዲድያዎች እንደመግጠማቸው በነገው ጨዋታ ከተለመደው አጨዋወት ወጣ ብለው በመስመር በሚደረጉ የማጥቃት አጨዋወት ይገባሉ ተብሎ ይገመታል።

ወልዋሎዎች በነገው ጨዋታ አምበሉ ዓይናለም ኃይለ፣ ካርሎስ ዳምጠው እና አቼምፖንግ አሞስን በጉዳት አያሰልፉም። አብዱላዚዝ ኬይታም በቅጣት አይኖርም።

ባለፈው ሳምንት የመጀመርያ ድላቸው ያሳኩት ነብሮቹ ማንሰራራታቸው ለማስቀጠል አልመው ወደ ሜዳ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የሀዲያ ሆሳዕና ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም
አሸነፈ ተሸነፈ አቻ ተሸነፈ ተሸነፈ

ከሜዳቸው ውጪ ባደረጓቸው ጨዋታዎች ወደ ግብ ክልላቸው ተጠግተው እና በቁጥር በዝተው በመልሶ ማጥቃት የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት የሚያደርጉት ሀድያዎች በነገው ጨዋታው ከዚህ የተለየ አቀራረብ ይኖራቸዋል ተብሎ አይገመትም።

ከዚህ በተጨማሪ በአዳማ ዋንጫ የቅድመ ውድድር ቆይታቸው ጨምሮ በአንዳንድ የሊጉ ጨዋታዎችም ኳስን ተቆጣጥሮ የመጫወት አዝማሚያ ያሳዩት ነብሮቹ በነገው ጨዋታ የተጠቀሰው አጨዋወት ይዘው የሚገቡበት ዕድልም የሰፋ ነው።

ሆሳዕናዎች በነገው ጨዋታ መሐመድ ናስር እና ኢዩኤል ሳሙኤልን በጉዳት አያሰልፉም።

እርስ በርስ ግንኙነት

የነገው ጨዋታ ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ የሚያደርጉት የመጀመርያ ግንኙነት ነው።

ግምታዊ አሰላለፍ

ወልዋሎ (4-2-3-1)

ጃፋር ደሊል

ምስጋናው ወልዮሐንስ – ገናናው ረጋሳ – ሳሙኤል ዮሐንስ – ሄኖክ መርሹ

ፍቃድ ደነቀ – ጣዕመ ወልደኪሮስ

ሰመረ ሀፍታይ – ራምኬል ሎክ – ኢታሙና ኬይሙኔ

ጁንያስ ናንጂቡ

ሀድያ ሆሳዕና (3-5-2)

ታሪክ ጌትነት

ፀጋሰው ዴልሞ – ደስታ ጊቻሞ – አዩብ በቀታ

ሱራፌል ዳንኤል – አፈወርቅ ኃይሉ – ይሁን እንደሻው – ዓብዱልሰመድ ዓሊ – ሄኖክ አርፊጮ

ቢስማርክ ኦፖንግ – ቢስማርክ አፒያ


© ሶከር ኢትዮጵያ