ቅድመ ዳሰሳ | ሲዳማ ቡና ከ ባህር ዳር ከተማ

ነገ 9 ሰዓት በሃዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ የሚደረገውን የሲዳማ ቡና እና የባህር ዳር ከተማ ጨዋታ እንደሚከተከው ዳሰነዋል።

የዐምና ጥንካሬያቸውን ያጡ የሚመስሉት ሲዳማ ቡናዎች በተከታታይ በድሬዳዋ እና ሀዲያ ሆሳዕና ከደረሰባቸው ሽንፈት ለማገገም እንዲሁም ወደ ደረጃ ሰንጠረዡ አናት ለመጠጋት ነገ ባህር ዳርን ይገጥማሉ።

የሲዳማ ቡና ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም
ተሸነፈ ተሸነፈ አሸነፈ ተሸነፈ አሸነፈ

ግቦችን ለማስቆጠር የማይቸገረው ቡድኑ የገነባው የላላ የመከላከል አደረጃጀት ዋጋ እያስከፈለው ይገኛል። በተለይ ፈጥነት የታከለበት የማጥቃት አጨዋወት የሚከተለው ሲዳማ ከማጥቃት ወደ መከላከል በሚያደርጋቸው የዘገዩ ሽግግሮች እና በተከላካዮቹ መሐል በሚፈጠሩ የመናበብ ችግሮች ሲፈተን ይስተዋላል።

በፈጣኖቹ የመስመር አጥቂዎች ትጋት ታግዞ የተጋጣሚን የግብ ክልል በተደጋጋሚ የሚጎበኘው ቡድኑ በነገው ጨዋታም የመስመር አጨዋወቱን አጠናክሮ እንደሚገባ ይገመታል። በተለይ በፈጣኑ አጥቂ አዲስ ግዳይ ታግዞ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን በተደጋጋሚ እንደሚፈጥር ይታሰባል።

እስካሁን በተደረጉ ሁሉም ጨዋታዎች ቢያንስ 1 ጎል ሲያስተናግድ የቆየው ሲዳማ በነገውም ጨዋታ ግቦችን ሊያስተናግድ ይችላል። በተለይ ተጋጣሚው ባህር ዳር ከተማ ካለው የወገብ በላይ ጥንካሬ አንፃር ቡድኑ ችግሮችን እንደሚጋፈጥ መናገር ይቻላል።

ረጅም ጊዜ ጉዳት የገጠመው ሚሊዮን ሰለሞን፣ ዮናታን ፍሰሀ፣ ሙሉቀን ታሪኩ እና አዲሱ አቱላ በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጪ መሆናቸው ተጠቁሟል።

እስካሁን ምንም ጨዋታ ከሜዳቸው ውጪ ማሸነፍ ያልቻሉት ባህር ዳር ከተማዎች በሜዳቸው ኢትዮጵያ ቡና ላይ የተቀዳጁትን ድል ለመድገም ወደ ሀዋሳ አምርተዋል።

የባህር ዳር ከተማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም
አሸነፈ ተሸነፈ አቻ አሸነፈ ተሸነፈ

በአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ የሚመራው ባህር ዳር በሜዳው እና ከሜዳው ውጪ እያሳየ ያለው አቋም የተለያየ ነው። በተለይ ቡድኑ በሜዳው ሲጫወት ማጥቃትን መሰረት ያደረገ አጨዋወት ሲከተል ቢስተዋልም ከሜዳው ውጪ ግን አጨዋወቱን በመገደብ ሲንቀሳቀስ ይታያል። በነገውን ጨዋታ ጥቃቶችን እንደ ተጋጣሚው አጨዋወት በመቃኘት ጨዋታውን እንደሚያከናውን ይታሰባል።

ኳስን ለመቆጣጠር የማይቦዝነው ቡድኑ በነገው ጨዋታ እንደተለመደው ኳሱን በቁጥጥሩ ስር እንደሚያውል ይገመታል። ነገር ግን ፈጥነታቸውን ተጠቅነው ለማጥቃት የሚወጡትን የሲዳማ የመስመር ተጨዋቾች ክፍተት ለመጠቀም እንደየአጋጣሚዎቹ ረጃጅም ኳሶችን ለመስመር አጥቂዎቹ በመጣል ጥቃቶችን ለመሰንዘር እንደሚያስብ ይገመታል። ከዚህ አጨዋወት በተጨማሪ ቡድኑ ቁመተ መለሎው አጥቂ ማማዱ ሲዲቤን ኢላማ ያደረጉ ተሻጋሪ ኳሶችን በመጠቀም የባለሜዳዎቹን ጊዜ ከባድ ሊያደርግ ይችላል።

እንደ ባለሜዳዎቹ ሁሉ ባህር ዳሮችም ግቦችን በቀላሉ የማስተናገድ ችግር ተጠናውቶዋቸዋል። ከዚህ የተነሳ የሲዳማ ፈጣን ተጨዋቾች ለቡድኑ ፈተና እንደሚሆኑ ግልፅ ነው።

ባህር ዳሮች በነገው ጨዋታ ወሳኝ ተጨዋቾቻቸውን በጉዳት ሳይዙ ወደ ሀዋሳ አምርተዋል። በዚህም ወሰኑ ዓሊ፣ ፍፁም ዓለሙ፣ ሳምሶን ጥላሁን እና አቤል ውዱ ከነገው ጨዋታ ውጪ መሆናቸው ታውቋል። ነገር ግን የኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ ያመለጠው የቡድኑ አምበሉ ፍቅረሚካኤል ዓለሙ ከጉዳቱ በማገገሙ ለጨዋታው ዝግጁ ነው።

እርስ በእርስ ግንኙነት

– ዐምና በመጀመርያ ግንኙነት ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች ሀዋሳ ላይ አንድ አቻ ሲለያዩ ባህር ዳር ላይ ባህር ዳር ከተማ 1-0 አሸንፏል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሲዳማ ቡና (4-2-3-1)

መሳይ አያኖ

ግሩም አሰፋ – ጊት ጋት – ግርማ በቀለ – ተስፉ ኤልያስ

ብርሀኑ አሻሞ – ዮሴፍ ዮሀንስ

አዲስ ግደይ – ዳዊት ተፈራ – ሀብታሙ ገዛኸኝ

ይገዙ ቦጋለ

ባህር ዳር ከተማ (4-3-3)

ሀሪስተን ሄሱ

ሚኪያስ ግርማ – አዳማ ሲሶኮ – ሰለሞን ወዴሳ – ሳላምላክ ተገኝ

ዳንኤል ኃይሉ – ደረጄ መንግስቱ – ዳግማዊ ሙሉጌታ

ፍቃዱ ወርቁ – ማማዱ ሲዲቤ – ግርማ ዲሳሳ


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ