ከፍተኛ ሊግ | ለገጣፎ ለገዳዲ መሪነቱን ሲያጠናክር ሻሸመኔ እና ጌዴኦ ዲላ አሸንፈዋል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ አምስተኛ ሳምንት ዛሬ በየምድቡ በተደረጉ አንድ አንድ ጨዋታዎች ሲጀመር ለገጣፎ ለገዳዲ፣ ሻሸመኔ ከተማ እና ጌዴኦ ዲላ ድል አስመዝግበዋል።

ምድብ ሀ

ወደ መቐለ ያቀናው ለገጣፎ ለገዳዲ ደደቢትን 2-1 በማሸነፍ የምድብ መሪነቱን አጠናክሯል። ጥሩ ፉክክር እና ማራኪ እንቅስቃሴ በታየበት ጨዋታ ግብ ያስተናገደው ገና በአንደኛው ደቂቃ ነበር።
ልደቱ ለማ በግል ጥረቱ ከግብ ጠባቂው ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ግብ በማስቆጠር ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል። ከግቡ መቆጠር በኃላ እንግዶቹ ከጥሩ እንቅስቃሴ በዘለለ ሙከራዎች ያላደረጉ ሲሆን በአንፃሩ ደደቢቶች በርካታ ሙከራዎች አድርገዋል።

ከነዚህም አፍቅሮት ሰለሞን በሁለት አጋጣዎች የሞከራቸው ሙከራዎች ይጠቀሳሉ። በተለይም አማካዩ አክርሮ መቷት አግዳሚው ለትማ የወጣችው ሙከራ ለግብ የቀረበች ነበረች። ደደቢቶች ከተጠቀሰው ሙከራ ውጭም በከድር ሳልህ እና አፍቅሮት ሰለሞን ሙከራዎች አድርገዋል። በሰላሳ ሶስተኛው ደቂቃም ዓብዱልበሲጥ ከማል ከፉሴይኒ ኑሁ የተላከለትን ኳስ በግሩም ሁኔታ ወደ ግብነት ቀይሮ ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል።

በመጀመርያው ደቂቃ ግብ ካስቆጠሩ በኃላ የግብ ዕድሎች ያልፈጠሩት ለገጣፎዎች በመጨረሻዎቹ አስራ አምስት ደቂቃዎች ጥቂት የማይባሉ ሙከራዎች አድርገዋል። በተለይም ልደቱ ለማ ከመአዝን የተላከለትን ኳስ ተጠቅሞ ያደረጋት ሙከራ እና ራሱ ልደቱ ለማ የተከላካዮች ስህተት ተጠቅሞ ባገኛት ኳስ ያደረገው ሙከራ ይጠቀሳሉ።

ከመጀመርያው አጋማሽ አንፃር ጥቂት ሙከራዎች የታዩበት ሁለተኛው አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ጥሩ የፉክክር መንፈስ የታየበት ነበር። በስልሳ አንደኛ ደቂቃም ለገጣፎዎች በጨዋታው ጥሩ እንቅስቃሴ ባደረገው ልደቱ ለማ ሁለተኛ ግብ አግብተዋል። አጥቂው የተከላካይ እና የግብ ጠባቂው አለመናበብ ተጠቅሞ ነበር ግቧን ያስቆጠረው። አጥቂው ከግባ በተጨማሪ በግንባሩም ጥሩ ሙከራ አድርጓል።

ባለሜዳዎቹ ደደቢቶችም በፉሰይኒ ኑሁ እና አንቶንዮ አብዋላ ከእጅ ውርወራ በረጅሙ በሚወረውራቸው ኳሶች ሙከራዎች አድርገዋል በተለይም ፉሰይኒ ኑሁ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ያመከናት ዕድል ቡድኑን አቻ የምታደርግ ነበረች።

ምድብ ለ

ሻሸመኔ ላይ ሀምበሪቾ ዱራሜን ያስተናገደው ሻሸመኔ ከተማ 1-0 በማሸነፍ ነገ ጨዋታውን ከሚያደርገው ነቀምቴ ከተማ መሪነቱን ተረክቧል። ለሻሸመኔን ብቸኛ የድል ጎል ያስቆጠረው ሙሉቀን ተሾመ ነው።

ምድብ ሐ

ዲላ ላይ ደቡብ ፖሊስን የገጠመው ጌዴኦ ዲላ ወልዳይ ገብረሥላሴ ባስቆጠረው ጎል 1-0 አሸንፏል። በዚህም ነገ ከሚጫወተው መሪው አርባምንጭ ያለውን ልዩነት ወደ አንድ አጥብቧል።


© ሶከር ኢትዮጵያ