ሪፖርት | ነብሮቹ ወሳኝ የሜዳ ውጪ ድል አስመዘገበው ከግርጌው ተላቀዋል

በስምንተኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ወደ መቐለ ያመራው ሀዲያ ሆሳዕና በቢስማርክ ኦፖንግ ብቸኛ ግብ ወሳኝ የሊጉ መሪ የነበረው ወልዋሎ ላይ ያልተጠበቀ ድል አስመዝግበዋል።

ቢጫ ለባሾቹ ባለፈው ሳምንት ድሬዳዋ ከተማን ካሸነፈው ስብስብ ጠዓመ ወልደኪሮስን በሰመረ ሀፍታይ ተክተው ሲገቡ ሀዲያዎች ባለፈው ሳምንት ሲዳማን ካሸነፈው ስብስብ ሄኖክ አርፊጮ እና በኃይሉ ተሻገርን በፍራውል መንግስቱ እና ዓብዱልሰመድ ዓሊ ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ብዙም ሳቢ ባልነበረው እና ጥቂት የግብ ሙከራዎች በታየበት የመጀመርያው አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ብዙ የግብ ዕድል ያልተፈጠረበት ነበር። በአጋማሹ በሁሉም ረገድ የተሻሉ የነበሩት ሆሳዕናዎች ከባለሜዳዎቹ በተሻለ ተንቀሳቅሰው ሙከራዎችም አድርገዋል። ከነዚህም ይሁን እንደሻው ከሳጥን ውጭ አክርሮ መቷት ጃፋር ደሊል ያዳናት ኳስ እና ቢስማርክ አፓንግ እና ቢስማርክ አፕያ በጥሩ ተግባቦት የፈጠሯት ዕድል ይጠቀሳሉ። በሰላሳ ሶስተኛው ደቂቃም ሱራፌል ዳንኤል መቷት ቋሚውን ገጭታ የተመለሰችውን ቢስማርክ አፖንግ አስቆጥሯት ጨዋታውን መምራት ችለዋል።

በአጋማሹ በረጃጅም ኳሶች የግብ ዕድል ለመፍጠር ጥረት ያደረጉት ወልዋሎዎችም አብዛኛው ሙከራቸው በግዙፎቹ ተከላካዮች ከሽፎባቸዋል። ሆኖም በአንድ አጋጠሚ አቻ ለመሆን ተቃርበው ነበር። ሙከራውም ጁንያስ ናንጂቡ ከሰመረ ሀፍታይ የተላከለት ኳስ መቶ ግብጠባቂው መልሶበታል።

ከመጀመርያው አጋማሽ በተሻለ በርካታ ሙከራዎች እና የታየበት እና ሁለተኛው አጋማሽ ወልዋሎዎች በተሻለ ሲንቀሳቀሱ ነብሮቹ ውጤቱን አስጠብቀው ለመውጣት አፈግፍገው የተጫወቱበት ነበር።

እንደ መጀመርያው አጋማሽ በረጃጅም ኳሶች ግብ ለማግኘት ሙከራዎች ያደረጉት ቢጫ ለባሾቹ በርካታ ሙከራዎች አድርገዋል። ከነዚህም ሳሙኤል ዮሐንስ ከቅጣት ምት መቶት ኦቤር ኦቮኖ ያዳነው ኳስ እና ሰመረ ሀፍታይ ራምኬል ሎክ አክርሮ መቶት ተከላካዮች የተደረቡት ኳስ አግኝቶ መቶት ኦቤር ኦቮኖ በድጋሜ ያዳነው ኳስ እጅግ ለግብ የቀረቡ ነበሩ።

ቢጫ ለባሾቹ ከተጠቀሱት ሁለት ሙከራዎች ውጭ በጁንያስ ናንጂቡ እና ሰመረ ሀፍታይ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች አድርገዋል። በተለይም ምስጋናው ወልደዮሐንስ አሻምቷት ጁንያስ ናንጂቡ በግንባሩ ገጭቶ ኦቤር ኦቮኖ እንደምንም ያዳናት ኳስ ባለሜዳዎቹን አቻ ለማድረግ ተቃርባ ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ ወደ ግባቸው አፈግፍገው መጫወትን የመረጡት ሆሳዕናዎችም በቢስማርክ ኦፖንግ እና አብዱሰመድ ዓሊ አማካኝነት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች እድርገዋል። በተለይም አብዱልሰመድ አክርሮ መቷት ቋሚውን ገጭታ የተመለሰች ኳስ የነብሮቹን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ለማድረግ ተቃርባ ነበር።

ድሉን ተከትሎ ሀዲያ ሆሳዕና ለሁለተኛ ጊዜ እየተሳተፈበት በሚገኘው ፕሪምየር ሊግ በታሪኩ የመጀመርያ የሜዳ ውጪ ድሉን በማሳካት የሰንጠረዡን ግርጌ ለወላይታ ድቻ ሲያስረክብ ወልዋሎ ሽንፈቱን ተከትሎ ከመሪነት ወደ ሦስተኛ ደረጃ ወርዷል።


© ሶከር ኢትዮጵያ