ክለብ አልባው አሰልጣኝ ዳግም ወደ ፈረሰኞቹ ቤት ይመለሱ ይሆን ?

ከግብፁ ክለብ ዛማሌክ ጋር ከተለያዩ በኋላ ያለ ሥራ የተቀመጡት አሰልጣኝ ሰርዮቪች ሚሉቲን “ሚቾ” ዛሬ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታውን መመልከታቸው ትኩረት ስቧል።

ዛሬ በአዲስ አበባ ስታድየም በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 8ኛ ሳምንት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ድሬዳዋ ከተማን አስተናግደው 3-2 በረቱበት ጨዋታ የቀድሞ አሰልጣኛቸው ሰርዮቪች ሚሉቲን “ሚቾ” በስታድየም በመገኘት ሙሉ ጨዋታውን ተከታትለዋል። አሰልጣኙ ክለብ አልባ መሆናቸው እና ጨዋታውን በስታድየም ተገኝተው መታደማቸውም ዳግመኛ ወደ ቀድሞ ክለባቸው ይመለሱ ይሆን የሚል ጥያቄ አስነስቷል።

ጉዳዩን ለማጣራት ለክለቡ ቅርብ ከሆነ የመረጃ ምንጫችን እንደሰማነው ከሆነ በአጋጣሚ አዲስ አበባ በመኖራቸው ጨዋታውን ለመከታተል መገኘታቸውን እንጂ ፈረሰኞቹን ለማሰልጠን እንዳልታሰበ ለማወቅ ችለናል። በቀጣይ የሚቀየር አዳዲስ ነገር ካለ ተከታትለን የምንመለስበት ይሆናል።

ሚቾ ከዚህ ቀደም ከ1997 እስከ 98 እንዲሁም ከ2000 እስከ ከ2002 በፈረሰኞቹ በቆዩባቸው አምስት የውድድር ዓመታት በሁሉም የሊግ ዋንጫ ማንሳታቸው የሚታወስ ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ