ሪፖርት | ሲዳማ ቡና ከተከታታይ ሽንፈት በኋላ ወደ ድል ተመለሰ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ስምንተኛው ሳምንት ጨዋታ ሲዳማ ቡና በሜዳው ሀዋሳ ሰው-ሰራሽ ሜዳ ላይ ከተከታታይ ሽንፈት ማግስት ባህር ዳር ከተማን 3ለ1 በማሸነፍ ወደ ድል ተመልሷል፡፡

ሲዳማ ቡናዎች በሰባተኛው ሳምንት በሆሳዕና ከተረቱበት ጨዋታ የመጀመሪያ ተሰላፊዎቹ መሀል ለውጥን አድርገው ወደ ሜዳ ገብተዋል፡፡ መሳይ አያኖ፣ ግሩም አሰፋ፣ ጊት ጋትኮች እና ብርሀኑ አሻሞን በማሳረፍ ፍቅሩ ወዴሳ፣ አማኑኤል እንዳለ፣ ሰንደይ ሙቱኩ እና አበባየው ዮሀንስ ለዛሬው ጨዋታ ተተክተው ሲገቡ በአንፃሩ የአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኙ ባህር ዳር ከተማ በጉዳት ባጧቸው ፍፁም ዓለሙ እና ሳምሶን ጥላሁን ምትክ ፍቅረሚካኤል ዓለሙ እና ደረጄ መንግስቱን ቀዳሚ ተመራጭ አድርገው ጨዋታውን ጀምረዋል፡፡

ለተመልካች ሳቢ እና ፋታ የለሽ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን በተመለከትንበት የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ሲዳማ ቡናዎች ከሁለት ጨዋታ ሽንፈት እንደመመለሳቸው ሙሉ የጨዋታ መንገዳቸውን በማጥቃት ላይ ብቻ መሠረት አድርገው ለመጫወት ጥረት ያደረጉ ሲሆን በተሻጋሪ ኳሶች ወደ ማማዱ ሲዲቤ በሚጣሉ ኳሶች ዕድሎችን ለመፍጠር ሲታትሩ የታዩት የጣና ሞገዶቹም የጨዋታውን ሂደት ለመቆጣጠር ያደረጉት ጥረት ጥሩ የሚባል ነበር።

በጨዋታው ገና ከጅምሩ ነበር በክፍት አጋጣሚዎች ግብ ሙከራዎችን መመልከት የቻልነው፡፡ 2ኛው ደቂቃ ላይ አማካዩ ዳዊት ተፈራ በግራ አቅጣጫ ለሀብታሙ ገዛኸኝ ሰቶት ፈጣኑ አጥቂ ወደ ሳጥኑ በደንብ ከተጠጋ በኃላ የመታትን ኳስ ቤኒናዊው ግብ ጠባቂ ሀሪስተን ሄሱ በግሩም ሁኔታ ያወጣበት አጋጣሚ የጨዋታውን መንፈስ ያመላከተች ነበረች፡፡ ከሁሉም የሜዳ ክፍል መነሻ በማድረግ ለማጥቃት ያልቦዘኑት ቡናማዎቹ ሌሎች በርካታ ዕድሎችንም ፈጥረዋል፡፡ በተለይ አማካዩ ዳዊት ተፈራ ከርቀት አክርሮ መቶ ሀሪሰን ሲተፋው አዲስ ግደይ ደርሶባት ወደ ግብ ሲመታት ተከላካዩ ሰለሞን ወዴሳ ከግቡ ጠርዝ ላይ ተንሸራቶ ያወጣት ክስተት ምናልባት ሲዳማዎችን መሪ የምታደርግ ነበረች፡፡

30ኛው ደቂቃ ላይ ሲዳማ ቡናዎች ሲያደርጉት የነበረው ጥረት ተሳክቶላቸው ግብ አስቆጥረዋል፡፡ ዳዊት ተፈራ ከአዲስ ግደይ ጋር ባደረገው ቅብብል የባህርዳር ተከላካይ አዳማ ሲሶኮ ኳሷ እግሩ ስር ልትገባ ስትል ዳዊት ተፈራ በፍጥነት ነጥቆ ኳሷ ወደ አበባየው እግር አምርታ አማካዩም በግሩም ሁኔታ ወደ ግብነት ለውጧት ሲዳማን መሪ አድርጓል፡፡ ግቧ ስትቆጠር ኳስ በእጅ ተነክቷል በማለት የባህርዳር ተጫዋቾች ዳኛው ሲከቡ የታየ ሲሆን የአስልጣኝ ቡድን አባላትም ባሰሙት መጠነኛ ተቃውሞ ጨዋታው ለሁለት ደቂቃዎች ተቋርጦ ዳግም ጀምሯል፡፡ ባህር ዳሮች 35ኛው ደቂቃ በሰለሞን ወዴሳ አማካኝነት ግብ ቢያስቆጥሩም ከጨዋታ ውጪ ተብላ ተሽራለች፡፡

ከእረፍት መልስ ሲዳማ ቡናዎች በባህር ዳር ከተማ ላይ ብልጫን ወስደው የተጫወቱበት ከመሆን ባለፈ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ ማራኪ ፍሰት ያለው የጨዋታ እንቅስቃሴን ዳግም የተመለከትንበትም ጭምር ነበር፡፡ አሁንም የጠሩ የኳስ ቅብብሎችን ሲያደርጉ የታዩት ባለሜዳዎቹ በፈጣን አጥቂዎቹ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ፈጥረዋል፡፡

53ኛው ደቂቃም አበባየው ዮሀንስ መሀል ለመሀል ለአዲስ ግደይ አሾልኮ የሰጠውን ኳስ አምበሉ ወደ ሳጥን እየነዳ ሲገባ አዳማ ሲሶኮ ከኃላ በግብ ክልል ውስጥ ጠልፎ በመጣሉ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ራሱ አዲስ ግደይ ከመረብ አሳርፏት የሲዳማን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ አድርጓል፡፡
አሁንም ከማጥቃት ያልቦዘኑት ሲዳማ ቡናዎች በሀብታሙ እና አዲስ ያለቀላቸው ዕድሎች ፈጥረው ተጨማሪ ግብን 70ኛው ደቂቃ ላይ አግብተዋል፡፡ አበባየው ዮሀንስ ባህርዳሮች መሀል ሜዳው ላይ ሲቀባበሉ በፍጥነት ነጥቆ ያገኘውን ኳስ ለአዲስ ግደይ ሰጥቶት አዲስም በነፃ አቋቋም ለነበረው ሀብታሙ አመቻችቶ የመስመር አጥቂው በግሩም አጨራረስ ሲዳማን ወደ 3ለ0 ያሸጋገረች ግብን ከመረብ አዋህዷል፡፡ ከግቧ በኃላ ሲዳማ ቡናዎች ተጨማሪ ግብ የምትሆን ኳስን በአዲስ ግደይ አማካኝነት ቢያገኙም ቋሚ ብረቱ መልሶበታል፡፡

ጨዋታው ሊጠናቀቅ አምስት ተጨማሪ ደቂቃዎች በተሰጡበት ሰዓት ሁለት ፈጣን ሙከራዎችን አድርጎ የነበረው ተቀይሮ የገባው የባህርዳሩ አጥቂ ስንታየው መንግስቱ 90+3 ላይ የሲዳማ ቡና የተከላካይ ክፍል መዘንጋትን ተመልክቶ በቀላሉ ሳይቸገር ከመረብ አሳርፎ ጨዋታው በሲዳማ ቡና 3ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

*በጨዋታው የሲዳማ ቡናው የህክምና ባለሙያ አበባው በለጠ በእጁ ላይ ከጨዋታው በፊት የመውደቅ አደጋን አስተናግዶ ህክምናውን ባደረገበት ቅፅበት በዛሬው ጨዋታ ላይ አንድ እጁ ታስሮ የህክምና አገልግሎቱን ሲሰጥ ያየንበት ተጠቃሽ የጨዋታው ክስተት ነበር፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ