የአሰልጣኞች አስተያየት | ፋሲል ከነማ 2-1 ኢትዮጵያ ቡና

በስምንተኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ፋሲል ከነማ ኢትዮጵያ ቡናን አስተናግዶ 2-1 ካሸነፈ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች እንደ ሚከተለው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል ።

👉 “ብዙም እንደጠበቅነው አላስጨነቁንም” ሥዩም ከበደ (ፋሲል ከነማ)

ስለጨዋታው

ጥሩ ነው! ቡና የኳስ ቁጥጥራቸው ላይ የተሻሉ ነበሩ። እነሱ ጋር የተበላሸን ኳስ እኛ በመቆጣጠር ተደጋጋሚ ወደ ግብ መድረስ አስበን ነበር። እስከዛሬ ያልተጠቀምነውን አደራደር (4-2-2) ነው በዛሬው ጨዋታ የተጠቀምነው። ግን በዚህ ውጤታማ አልሆንም፤ ከዛም በሁለተኛው አጋማሽ ወደ ቀድሞው በተጠቀምንባቸው 4-2-3-1 በትንሹም ጨዋታውን መቆጣጠር ችለናል።

ቡና ኳሱን በመቆጣጠር ደረጃ ጥሩ ነበሩ። ግን ብዙም እንደጠበቅነው አላስጨነቁንም። አጠቃላይ እዚህ ሜዳችን ላይ እንደመጫወታችን ማሸነፋችን ጥሩ ነጥብ ነው። ሁሌም በፕሪማች ላይ የሰበታውን የመጨረሻ ደቂቃ ክስተት ስለምናስታውስ በዚህ ጨዋታ ላይ በመጨረሻ ደቂቃዎች የተገኘ ጎል ጥሩ ነገር ነው። ለኛ ትልቅ መነሳሳት አጋዥ ውጤት ነው።

👉 “ወደ ተቃራኒ ጎል ስንደርስ በአግባቡ የመጠቀም ድክመት ነበር” ካሣዬ አራጌ (ኢትዮጵያ ቡና)

ስለ ጨዋታው

አጠቃላይ ጥሩ ነው! ጨዋታው ባመዛኙ በምንፈልገው መንገድ ሄዷል። ምክንያቱም እንደዚህ ደጋፊ ያላቸው ቡድኖች ሜዳ ላይ ስትጫወት ደጋፊው በራሱ ሌላ ኃይል ስለሆነ ከዛ ጋር ተያይዞ ተጫዋቾቹ ቶሎ በፍጥነት አንተ ላይ ጫና የመፍጠር ነገር አለ። አንዱ ያንን ማጥፋት ነበር የፈለግነው። (ደጋፊውን ከቡድኑ የመለየት) ያንን ደግሞ እንቅስቃሴውን በመቆጣጠር ለማድረግ ነበር ያሰብነው፤ ተሳክቶልናል። በተለይ ከዕረፍት በኋላ ያንን ማድረግ ተችሏል። እግዲህ በኛ በኩል ከመሀል ሜዳ ቀስ እያልን የምናልፋቸው ኳሶች ተቃራኒ ጎል አካባቢ ስንደርስ እነዛን ነገሮች በአግባቡ የመጠቀም ድክመት ነው። በአጠቃላይ ግን በሁለቱም በኩል ጥሩ ጨዋታ ነበር።

የአቡበከር በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች መጎዳት

የመጀመሪያ 11 ውስጥ የሚሰለፉ ተጫዋቾች ሲጎዱብህ የሚፈጥረው ነገር አለ። ግን ከዛ ጋር ተያይዞ ደግሞ ተጠባባቂ ላይ የምናስቀምጣቸው ተጫዎቾች እነዛን ተክተው የነሱን ሚና ሊሰሩ ይችላሉ ብለን የምናምን ስለሆን ይበልጥ የቡድን ስራ ላይ ነው ትኩረት የምንሰጠው። እያንዳንዱ ተጫዋች ዋጋ አለው። ምናልባት እንደዚህ አይነት ተጫዎቾች በጉዳት ለረዥም ጊዜ ልናጣ እንችላለን። እና ያንን ምክንያት ማድረግ አግባብ አይመስለኝም። ሌሎቹ ተጫዋቻችን ማድረግ ይችላሉ፤ የገቡትም ጥሩ ነበሩ።


© ሶከር ኢትዮጵያ