ሪፖርት | ፋሲል ከነማ በሙጂብ ጎሎች ቡናን አሸንፏል

በስምንተኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጎንደር ላይ ፋሲል ከነማ ኢትዮጵያ ቡናን አስተናግዶ 2-1 በሆነ ጠባብ ውጤት ማሸነፍ ችሏል።

በጨዋታው መጀመሪያ ላይ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ባነር አሰርተው ወደ ሜዳ በመግባት ”ቡናማዎቹ እና ዐፄዎቹ ለኢትዮጰያ እግርኳስ ለውጥ ሁሌም በጋራ እንሰራለን ”  እና ”እምዬ ጎንደር ታሪካዊ ምድር፤ እንግዳ ተቀባይ ህዝብ ያለብሽ ከተማ ሠላምሽ ይብዛ” የሚሉ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል። ከዚህ በተጨማሪ የፋሲል ከነማ ስፖርት ክለብ የደጋፊ ማኅበር ለውጥ ያደረገ ሲሆን ለተለወጡት አባላት የዋንጫ ስጦታ ተበርክቶ ለነባሮቹ እና ለአዲሶቹ የማበረታቻ የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል። በሥነስርዓቱ ላይም አራተኛው ትውልድ የተባለው አዲሱ የደጋፊዎች ማኅበር ክለቡን ”ቻምፒዮን” እንደሚያደርግ ቃል ገብቷል።


ባለሜዳዎቹ ከባለፈው ሳምንት ሶዶ ላይ ወላይታ ድቻ ጋር 1-1 ከተለያየው ስብስብ ጋብሬል አህመድን በማሳረፍ ሀብታሙ ተከስተን በማስገባት ነበር ወደ ሜዳ የገቡት። በኢትዮጵያ ቡና በኩል ደግሞ በባህርዳር ከተማ 3-2 ከተሸነፈው ቡድን ውስጥ በቀይ ካርድ ከሜዳ በተሰናበተው አቤል ከበደ ምትክ ሚኪያስ መኮነንን እንዲሁም በኃይሌ ገ/ትንሳይ ቦታ አህመድ ረሽድን ተክተው ጨዋታውን ጀምረዋል። 

በመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥር ረገድ ኢትዮጵያ ቡናዎች የተሻሉ ቢሆንም የሰላ የአጥቂ መስመር ያላቸው ዐፄዎቹ በመጀመሪያ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራቸውን ግብ ማስቆጠር ችለዋል። 10ኛው ደቂቃ ላይ ሱራፌል ዳኛቸው ወደ ሳጥን እየገፋ በሚጠጋበት ወቅት በተከላካዮች ተጨናግፎ የቀረውን ኳስ ሙጅብ ቃሲም ከሳጥን ውጪ እክርሮ በመምታት ግብ አስቆጥሮ ባለሜዳዎቹን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።


ገና በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ከሳማኬ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ የቡድኑን የመጀመሪያ ሙከራ ባደረገበት ወቅት ከግብ ጠባቂው ጋር የተጋጨው አቡበከር ናስርን በጉዳት ያጡት ኢትዮጵያ ቡናዎች የማጥቃት እንቅስቃሴዎቻቸው ላይ ተፅእኖ የፈጠረባቸው ሲሆን በመጀመሪያ አጋማሽ መሀል ሜዳ ላይ ከሚንከባለሉ ኳሶች እንዲሁም ከርቀት ወደ ግብ ክልል የሚመቱ ኳሶች በስተቀር ስኬታማ የሆኑ ኳሶችን እምብዛም ሲሞክሩ አልታዩም።


በፋሲሎች በኩል ግብ አስቆጣሪው ሙጂብ ቃሲም በቡድኑ ሙከራዎች ላይ ዋና ታሳታፊም ነበር። 26ኛው ደቂቃ ላይ ሙጂብ ከኢትዮጵያ ቡና ግብ ጠባቂ በረከት አማረ ጋር ተገናኝቶ በረከት ሲያድንበት ከ3 ደቂቃዎች በኋላ በዛብህ መለዮ ሳጥን ውስጥ ጥሩ ኳስ አመቻችቶለት አጥቂው በቀጥታ ወደ ግብ የመታው ኳስ የግቡን የቀኝ ቋሚ ተጠግቶ ወጥቶበታል። 

በእንግዶቹ በኩል 33ኛው ደቂቃ ላይ ሚክያስ መኮንን በመስመር ይዞት የገባውን ኳስ ለአህመድ ረሽድ አሻግሮለት አህመድ በቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮ በተከላካዮች የተጨረፈበት ሲሆን ከዚሁ ኳስ የተገኘውን የማዕዘን ምት ደግሞ ሚኪያስ በጭንቅላቱ ቢገጨውም ኢላማውን መጠበቅ ሳይችል ቀርቷል። ከነዚህ በተጨማሪም ቡናዎች 40ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ በሚኪያስ መኮነን እንዲሁም 44ኛው ደቂቃ ላይ በአላዛር ሽመልስ ያደረጓቸው ሙከራዎች ፍሬ ሳያፈሩ ቀርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን ይዘው የቀጠሉት ኢትዮጵያ ቡናዎች የፋሲል ከነማን የተከላካይ ክፍል ሰብረው ለመግባት በርካታ ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል። በሁለተኛው አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ያደረጓቸው አንድ አንድ ኳሶች ሲሆኑ እነሱም ወደ ግብ ተቀይረዋል። በቡናማዎቹ በኩል 78ኛው ደቂቃ ላይ አማኑኤል ዮሃንስ ሳጥን ውስጥ ለሀብታሙ ታደለ አቀብሎት በግራ በኩል ሰብሮ መግባት የቻለው ሀብታሙ ድንቅ ግብ አስቆጥሮ ቡናማዎችን አቻ አድርጓል።


ሆኖም የቡና የአቻነት ጎል ለደቂቃዎች ብቻ ነበር የዘለቀው በፍጥነት ምላሽ መስጠት የጀመሩት ፋሲሎች ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ወደ መሪነት ተመልሰዋል። 80ኛው ደቂቃ ላይ ሙጂብ ቃሲም ከማዕዘን ምት የተሻማውን ኳስ በጭንቅላት ገጭቶ ወደ ግብ በመቀየር ነበር ቡድኑን ወደ መሪነት የመለሰው።

ፋሲል ከነማ የትኛውንም ያህል ቢቸገሩ በሜዳቸው አሸንፎ መውጣት የሚችሉበትን አቅም ያሳዩ ሲሆን የሰበታ ከተማውን ስህተት ላለመድገም ሙጅብ ቃሲምን ወደ መሐል ተከላካይ ቦታ በመመለስ የመከላከል አቅማቸውን አጠናክረው ውጤቱን አስጠብቀው ወጥተዋል።


ውጤቱን ተከትሎ ዐፄዎቹ በደረጃ ሰንጠረዡ 2ኛ ደረጃ ላይ በ15 ነጥብ ሲቀመጡ ቡናማዎቹ በ9 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።


© ሶከር ኢትዮጵያ