መቐለ 70 እንደርታዎች በልማደኛው አማኑኤል ገብረሚካኤል ብቸኛ ግብ ከወልቂጤ ሦስት ነጥብ ይዘው ተመልሰዋል።
በጨዋታው ወልቂጤዎች ጅማን ከገጠመው ስብስብ ውስጥ ኤፍሬም ዘካሪያስ ፣ መሐመድ ሻፊ እና ሙሐጅር መኪን በማሳረፍ ዳግም ንጉሴ ፣ ሔኖክ አወቀ እና በረከት ጥጋቡን ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል። መቐለዎች ደግሞ ባለፈው ሳምንት አዳማ ከተማን ካሸነፈው ስብስብ ውስጥ አሸናፊ ሀፍቱ እና ሄኖክ ኢሳይያስን በአንተነህ ገብረክርስቶስ እና ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስን ለውጠዋል።
በሜዳው የፕሪምየር ሊጉን ሁለተኛ ጨዋታ ያከናወነው ወልቂጤ እጅግ በሚማርክ የደጋፊዎች ድባብ ታጅቦ የጀመረው ጨዋታው ጥቂት የግብ ሙከራዎች እና የባለሜዳዎቹ ሙሉ ብልጫ የታየበት ነበር። በጨዋታው ወልቂጤዎች ከሌላው ጊዜ በተሻለ የግብ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ ኳስ ይዘው የተጫወቱ ሲሆን መቐለዋች እንደ ባለፈው ጨዋታ ሁሉ ተገማቹ የማጥቃት አጨዋወታቸው አስፈሪ ሆኖ አልታየም።
ከጨዋታው መጀመር አንስቶ ጥሩ የማጥቃት ፍላጎት የነበራቸው ወልቂጤዎች በጫላ ተሽታ እና ጃኮ አራፋት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች አድርገዋል። በተለይም ጫላ ተሽታ በ5ኛው ደቂቃ በግንባሩ ገጭቶ የውስጠኛውን አግዳሚ ለትሞ የወጣበት እንዲሁም አቤኔዜር ኦቴ ከቀኝ መስመር የተሻገረለት ኳስ ተጠቅሞ ያደረጋት ሙከራ ለግብ የቀረቡ ነበሩ።
በጨዋታው በተጋጣሚያቸው ብልጫ የተወሰደባቸው መቐለዋች ምንም እንኳ በርካታ የግብ ዕድሎች ባይፈጥሩም በተወሰኑ አጋጣሚዎች የግብ ሙከራዎች አድርገዋል። ከነዚህም ውስጥ ዳንኤል ደምሴ እንዲሁም አማኑኤል ገብረሚካኤል ከርቀት መትተው ግብ ጠባቂው ያዳነባቸው ሙከራዎች በመጀመሪያው አጋማሽ ተጠቃሽ ሙከራዎች ናቸው። መቐለዋች ከተጠቀሱት ሙከራዎች ውጪም በኦኪኪ አፎላቢ አማካኝነት ከረጅም ርቀት ሙከራ አድርገው ነበር።
የመጀመሪያው አጋማሽ መጠናቀቂያ ላይ ጫላ ተሽታ በግሩም ሁኔታ ያሳለፈበትን ኳስም ጃኮ አረፋት ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ወደ ግብ ለወጠው ሲባል የመታው ኳስ የግብ አግዳሚውን ለትሞ ወጥቷል።
ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ተቀራራቢ ፉክክር የታየበት ሁለተኛው አጋማሽ በርካታ ሙከራዎችን አስመልክቶናል። በተወሰነ መልኩ ተሻሽለው በገቡት መቐለዋች በኩል 50ኛው ደቂቃ ኦኪኪ አፎላቢ ሁለት ተጫዋቹችን ቀንሶ ወድ አደጋ ክልል ውስጥ በመግባት በግራ እግሩ አክርሮ የመታውን ኳስ ይድነቃቸው በሚገርም ሁኔታ አውጥቶበታል። በሁለተኛው አጋማሽ የተደረገ እጅግ ለግብ የቀረበ ዕድል ያባከኑት ባለሜዳዎቹ በመልሶ ማጥቃት የተገኘውን የግብ ዕድል ጫላ ተሽታ እና ኦቮኖ ተገናኝተው ጫላ ከፍ አድርጎ በግብ ጠባቂው አናት ላይ ለማስቆጠር ቢሞክርም ኳሱ የግቡን አግዳሚ ታኮ ወጥቶበታል።
ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ በታየባቸው ቀጣይ ደቂቃዎች ሁለቱም ቡድኖች ወደ ተቃራኒ ግብ ክልል በመድረስ ሙከራ ያደረጉ ሲሆን ሰራተኞቹ በአብዱልከሪም እና መሀመድ ኑርሁሴን ለግብ የቀረበ ሙከራ ሲደርጉ በተቃራኒው መቐለዎች ከተጠቀሰው ሙከራ ውጪም በአማኑኤል ገብረሚካኤል እና ኦኪኪ ኦፎላቢ አማካይነት የወልቂጤዎችን የግብ ክልል መፈተሻቸው አልቀረም።
በ85ኛው ደቂቃ አማኑኤል ገብረሚካኤል ግብ የግብ ጠባቂውን አቆቆም በማያት ከፍ አድርጎ የሰዳዳት ኳስ በስተመጨረሻ መቐለን አሸናፊ ማድረግ ችላለች። ከግቡ መቆጠር በኋላ እጅጉን ተጭነው የተጫወቱት ወልቂጤዎች በተጨማሪ ደቂቃ ከማዕዘን ምት የተሻማ ኳስ በእጅ ተነክቷል በሚል ቅሬታቸውን አሰምተዋል። ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ የወልቂጤ ደጋፊዎች ለመቐለ 70 እንዳርታ ደጋፊዎች “በሰላም ግቡ” በማለት ያዜሙበት መንገድ እጅግ ማራኪና ትኩረት ሳቢ ነበር።
ውጤቱን ተከትሎ ወልቂጤ ባለበት በ8 ነጥብ ሲረጋ መቐለ ነጥቡን ወደ 16 ከፍ አድርጓል።
© ሶከር ኢትዮጵያ