የአሰልጣኞች አስተያየት | ወልቂጤ ከተማ 0-1 መቐለ 70 እንደርታ

በ8ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ወልቂጤ ከተማ እና መቐለ 70 እንደርታ ካደረጉት ጨዋታ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች ተከታዮቹን አስተያየቶች ሰጥተዋል።

👉 “ስንመጣ አሸናፊ መሆን እንችላለን ብለን ነው የመጣነው” ገብረመድን ኃይሌ (መቐለ 70 እንደርታ)

ስለጨዋታው

ጨዋታው በጣም ጥሩ ነው ፤ ጨዋታው ተጀምሮ እስከሚያልቅ የነበረው ድባብም ጥሩ ነው። ከዛም ስንመጣ አሸናፊ መሆን እንችላለን ብለን ነው የመጣነው። ይህንን ማሳካት ችለናል። ከሜዳችን ውጪ ነው የተጫወትነው። ሜዳው ላይ የገጠምነው ቡድንም ጥሩ መጫወት የሚችል ነው። በሁለታችንም በኩል ብርቱ ፉክክር አድርገናል። በመጀመሪያው አጋማሽ እነሱ የተሻሉ ነበሩ። በሁለተኛው አጋማሽ ያለንን ሁሉ ተጠቅመን ለማጥቃት ሞክረናል በዚህም ስኬታማ ሆነናል።

ስለዳኝነቱ

በጨዋታው መጀመሪያ ላይ የእኛም መታየት ነበረበት። ያም ሆነ ይህ የዳኛው ውሳኔ ነው።

👉 “የዛሬው ጨዋታ ውጤት አይገባንም” ደግአረግ ይግዛው (ወልቂጤ ከተማ)

ስለጨዋታው

ጨዋታው ጠንካራ ፉክክር የታየበት ነበር። በእኛ በኩል እጅጉን አስቆጪ የግብ ዕድሎች ያባከንበት ነበር። ተጋጣሚያችን በመጀመሪው አጋማሽ ይህ ነው የሚባል አደጋ የሚፈጥሩ ዕድሎችን ሳይፈጥሩ ቀርተዋል። በእኛ በኩል ያገኘነውን መጠቀም አለመቻላችን እንዲሁም እነሱም ያገኙትን መጠቀም በመቻላቸው ውጤቱ ይህ ሆኗል። በቶሎ ወደ አሸናፊነት እንመለሳለን። ተጫዋቾቼ ጋር ትልቅ መነሳሳት ነው ያለው። የዛሬው ጨዋታ ውጤት አይገባንም። እግር ኳስ እንዲህ ነው ፤ አንዳንዴ ያላሰብከው ውጤት ይገጥማል። በቀጣይ ወደ አሸናፊነት እንመለሳለን።

ስለዳኝነቱ

በዚህ ላይ ምንም አልልም ፤ የእውነት እሱ ይፍረድ። እጅግ ነው ያዘንኩት። በግልፅ ወደ ግብ የሚሄድ ኳስ ነው በእጅ የተነካው። በሰዓቱ እኛ ያገኘነውን አጋጣሚ ባለመጠቀማችን እያስቆጨን ባለበት ሰዓት ዳኛው ህጉ የሚለውን በራሱ መተርጎም መቻል ነበረበት። የእውነት አሳዛኝ ድርጊት ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ