ሪፖርት | ስሑል ሽረ ከሜዳው ውጪ ጣፋጭ ድል ተቀዳጅቷል

በሁለተኛ ቀን የ8ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መርሐ ግብር ወላይታ ድቻ በሜዳው በስሑል ሽረ 2-0 ተሸንፏል።

በወላይታ ድቻ በኩል በ7ኛው ሳምንት በሜዳው ከፋሲል ከነማ አቻ ከተለያየው ስብስብ አዛርያስ አቤልን በፀጋዬ አበራ፣ ፀጋዬ ብርሀኑን በዳንኤል ዳዊት ምትክ ጨዋታውን ሲጀምሩ እንግዶቹ በአዳማ ማሳላቺ እና አብዱለጢፍ መሐመድ ምትክ በረከት ተሰማ እና ሸዊት ዮሐንስን አካተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

በጨዋታው ጅማሮ ላይ ባለሜዳዎቹ ወላይታ ድቻዎች በተደጋጋሚ የስሑል ሽረ የግብ ክልል በመድረስ የግብ ማግባት ሙከራዎችን አድርገዋል። ገና ጨዋታው በተጀመረ በአንደኛው ደቂቃም ቸርነት ጉግሳ ከደጉ ደበበ የተቀበለውን ኳስ ወደ ግብ መትቶ ለጥቂት ወጥቶበታል። ከ7 ደቂቃዎች በኋላም ቡድኑ ዳግም ወደ ሽረዎች የግብ ክልል በመድረስ ተጨማሪ ሙከራ ሰንዝሯል። በዚህ ደቂቃ ባዬ ገዛኸኝ ያሻገረውን ኳስ ፀጋዬ ብርሃኑ በግምባሩ መትቶት መክኖበታል።

ሙከራ መሰንዘራቸውን የቀጠሉት የአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ተጫዋቾች በ10ኛው ደቂቃ በባዬ እንዲሁም በ11ኛው ደቂቃ በፀጋዬ ጥሩ ሙከራዎች መሪ ለመሆን ጥረዋል። በተጋጣሚያቸው ጥቃት እጅግ እየተፈተኑ ጨዋታውን የቀጠሉት ስሑል ሽረዎች በይበልጥ ወደ ራሳቸው የግብ ክልል በመጠጋት ግባቸውን መጠበቅ ጀምረዋል። ከመከላከል አጨዋወት በተጨማሪ ረጃጅም ኳሶችን ወደ ዲቻዎች የግብ ክልል የሚልኩት ሽረዎች በ20ኛው ደቂቃ በተከሰተ የተከላካዮች የመዘናጋተ ስህተት የተገኘን እድል በረመዳን አማካኝነት ወደ ግብ ቀይረውት መሪ ሆነዋል።

ካለባቸው የውጤት ጫና አንፃር ከጨዋታው 3 ነጥብ እጅግ ፈልገው የነበረው ወላይታ ድቻዎች ለተቆጠረባቸው ጎል በቶሎ ምላሽ ለመስጠት እና ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረቶችን አድርገዋል። በ28ኛው ደቂቃም ባዬ ከእዮብ የተላከለትን ኳስ ወደ ግብ መትቶ ቡድኑን አቻ ለማድረግ ሞክሯል። ጠንካራውን የሽረን የኋላ መስመር በቀላሉ መክፈት ያልቻሉት ድቻዎች የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ 3 ደቂቃ ሲቀረው ጥሩ ሙከራ አድርገዋል። በዚህ ደቂቃ የተገኘን የቅጣት ምት ደጉ በግምባሩ መትቶት ለጥቂት ወጥቶበታል። የመጀመሪያው አጋማሽም በተጋባዦቹ 1-0 መሪነት ተጠናቋል።

ጨዋታው በሚፈልጉት መልኩ እየተጓዘላቸው ያለው ሽረዎች የሁለተኛው አጋማሽ በተጀመረ በ5ኛው ደቂቃ በያሰር ሙገርዋ አማካኝነት ሁለተኛ ጎል ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ነበር። በተቃራኒው በዚህኛው አጋማሽ ከጨዋታው ነጥብ ይዞ ለመውጣት ጥረቶችን አጠናክረው የቀጠሉት ድቻዎች በ52ኛው ደቂቃ በበረከት ወልዴ ጥብቅ ኳስ ወደ ግብ ቀርበው ነበር። ከዚህ ሙከራ በተጨማሪ ቡድኑ በ3 ደቂቃዎች ውስጥ አስቆጪ አጋጣሚዎች አምልጠውታል። በ56ኛው ደቂቃ በፀጋዬ እንዲሁም በ59ኛው ደቂቃ በአንተነህ አማካኝነት ወደ ግብ የተሞከሩት ኳሶች ወደ ግብነት ሊቀየሩ ተቃርበው ነበር።

ድል የራቃቸው ወላይታ ድቻዎች ከየአቅጣጫው ጥቃቶችን መሰንዘር ቀጥለዋል። በ64ኛው ደቂቃም ፀጋዬ ከመስመር ያሻገረውን ኳስ ባዬ ተገልብጦ ወደ ግብ መቶት የነበረ ሲሆን በጨዋታው ጥሩ ጥሩ ኳሶችን ሲያመክን የነበረው ምንተስኖት አሎ በቀላሉ በቁጥጥሩ ስር አውሎበታል። ከዚህ ሙከራ በተጨማሪ ቡድኑ በ71 እና 79ኛው ደቂቃ የሽረን የግብ ክልል ጎብኝቶ ተመልሷል።

ጨዋታው ሊጠናቀቅ 3 ደቂቃ ሲቀረው ድቻዎች ነቅለው ወደ ሽረ የግብ ክልል በመድረስ በተስፋዬ አለባቸው አማካኝነት የአቻነት ግብ ፈልገው ነበር። ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ሊጠናቀቅ ሰከንዶች በቀሩት ሰዓት ተጋባዦቹ መሪነታቸውን ወደ ሁለት ከፍ ያደረጉበትን ግብ በፍፁም ቅጣት ምት አስቆጥረዋል። በዚህ ደቂቃ አንተነህ ጉግሳ በሳሊፍ ፎፋና ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ሀብታሙ ወደ ግብነት ቀይሯል። ጨዋታውም በተጋባዦቹ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የወላይታ ድቻ ደጋፊዎች በቡድኑ አመራሮች ላይ የተቃውሞ ድምፅ ሲያሰሙ ተስተውሏል።

ውጤቱን ተከትሎ ወላይታ ድቻ ከነበረበት 15ኛ ደረጃ አንድ ደረጃ ሸርተት በማለት የሊጉ ግርጌ ላይ ሲቀመጥ ጨዋታውን ያሸነፉት ስሑል ሽረዎች ደግሞ ከነበሩበት 10ኛ ደረጃ ወደ 6ኛ ደረጃ ተሸጋግሯል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ