የአሰልጣኞች አስተያየት | ወላይታ ድቻ 0-2 ስሑል ሽረ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ስምንተኛ ሳምንት ስሑል ሽረ ወደ ሶዶ ተጉዞ ወላይታ ድቻን 2-0 ከረታ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

👉 ” አቅደን የገባነው የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ውጤታማ ሆኖልናል” ሳምሶን አየለ (ስሑል ሽረ)

ስለ ጨዋታው

ጨዋታው እንደታየው ውጥረት የበዛበት ነበር። ከሜዳችን ውጪ እንደመጫወታችን በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ነበር የሞከርነው። ይህ አጨዋወታችንም ውጤታማ ሆኖልናል። ቡድናችን ካለፉት ሁለት እና ሦስት ጨዋታዎች ጀምሮ ወደ ጥሩ ፎርም እየመጣ ስለሆነ ይህን ማጠናከር ነው አላማችን። በዚህ አጋጣሚ የወላይታ ድቻን ደጋፊ ማመስገን እንፈልጋለን።

ስለ መልሶ ማጥቃት አቀራረባቸው

አምናም ነጥብ ተጋርተን የወጣነው በዚህ ነው። ከሜዳ ውጪ ከመጫታችንም፤ ከመጫወቻ ሜዳውም አንፃር በዚህ መልኩ ተጫውተን ውጤት ይዘን ለመውጣት ነበር ስንዘጋጅ የነበረው። በቀጣይም እንደተጋጣሚዎቹ የአጨዋወት ባህርይ እየተዘጋጀን ለጨዋታ እንቀርባለን።

👉 “ሀቁን ነው የምናገረው፤ ከድቻ ጋር ስላለኝ ጉዳይ ጨርሻለሁ” ገብረክርስቶስ ቢራራ (ወላይታ ድቻ)

ስለ ጨዋታው

ምንም የምገልፀው ነገር የለም። እስከዛሬ ከነበሩት በባሰ በጣም መጥፎ ጨዋታ ነበር። በግልፅ ነው የምናገረው፤ የረባን ስላልነበርን ነው የተሸነፍነው።

ስለ ቡድኑ አቀራረብ

(ሽንፈቱ የመጣው በአጨዋወት ምክንያት ነው የሚለው) የአረዳድ ጉዳይ ነው። እንደኔ ታክቲክ ጨዋታን አያሸንፍም፤ የተጫዋቾች ፍላጎት እንጂ። ኳስ ወደፊት ቢሄድም የሚጠቀምበት ከሌለ ዋጋ የለውም። በሦስት አጥቂዎች ብንጫወትም ከፊት ምንም መፍጠር አልቻልንም። ባዬ ትንሽ ይፍጨረጨራል። ተጫዋቾችም በእንዲህ አይነት ጫና መጫወት አይችሉም።

አሁን ያለው ሁኔታ ተጫዋቾችን ሊያጫውት አይችልም። ጫናው እስከ ቤት ነው ያለው፤ በመንገድ ሲሄዱ ጫና አለ፤ ሜዳ ሲገቡ ጫና አለ፤ ስለዚህ በዚህ ውጥረት ውስጥ እንዴት ነው ኳሱን መቆጣጠር እና መጫወት የሚችሉት። ስለዚህ ተጫዋቾቼ ላይም መፍረድ አልችልም። ጨዋታው ላይ አበረታተውን ካለቀ በኋላ ቢሰድቡን ምንም አልቀየምም። ተፎካካሪ ቡድንን እያበረታታህ እንዴት ይሆናል።

ድቻ ለአራት ዓመታት ላለመውረድ ነው የተጫወተው። ስለዚህ ባንድ ጊዜ በነዘለህ ወጣት ተጫዋቾች ለውጥ ማምጣት አንችልም። አንድ ቀን ይታያል፤ አንድ ቀን ይጠፋል። ይህ ደግሞ ሊበረታታ ይገባል። ይሄን ቡድን ሙሉ 90 ደቂቃ ቢበረታታ ወደ ጥሩ ውጤት ይመጣ ነበር።

ስለ ቀጣይ …

ለኔ ይህ የመጨረሻ ጨዋታዬ ነው። ባለፈውም ከቦርዱ ጋር ተነጋግረናል። በሁለቱ ጨዋታ በደጋፊ በኩል ያለውን ነገር ተመልክቼ እጫወታለሁ በሚል ነበር። ቦርዱም በቀጣይ ጨዋታዎች ውጤት የማይመጣ ከሆነ እኔም አልመጣም ነው ያልኩት። ነገ ስብሰባ አለ፤ ግን አልገኝም። ሀቁን ነው የምናገረው። ከድቻ ጋር ስላለኝ ጉዳይ ጨርሻለሁ። እነሱም ከሁለት ጨዋታ በኋላ ውጤት ካልመጣ የአሰልጣኝ ቡድኑን እናሰናብታለን ብለዋል። ስለዚህ ጨርሰናል ነው የምለው።


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ