የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 8ኛ ሳምንት ዓበይት ትኩረቶች

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 8ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅዳሜና እሁድ ተካሂደው የሊጉ መሪ የነበረው ወልዋሎ በሀዲያ ሆሳዕና በሜዳው ሳይጠበቅ ሲሸነፍ ሲዳማ ቡና ቅዱስ ጊዮርጊስና ሰበታ ወደ አሸናፊነት የተመለሱበትን ድል አስመዝግበዋል። መቐለ 70 እንደርታና ስሁል ሽረ ወሳኝ የሜዳ ውጭ ድል ያስመዘገቡበትን ሳምንትም አሳልፈዋል። እኛም የዚህኛው ሳምንት ትዝብታችን በተከታዩ መልኩ አቅርበነዋል።

1. ክለብ ትኩረት

– ሀዲያ ሆሳዕና ከሰመመን የነቃ ይመስላል

በዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አስከፊ የሊግ ጅማሮ ያደረጉት ሆሳዕናዎች በ6ኛ ሳምንት በኢትዮጵያ ቡና የገጠማቸው ሽንፈት የማንቂያ ደውል የሆነላቸው ይመስላል። ምንም ጨዋታ ሳያሸንፍ ለ6 ሳምንታት ተጎዞ የነበረው ቡድኑ ባሳለፍነው ሳምንት ሲዳማ ቡናን በሜዳው እንዲሁም በዚህኛው ሳምንት ደግሞ የሊጉን መሪ ወልዋሎ ሳይጠበቅ በትግራይ ዓለምአቀፍ ስታዲየም ማሸነፍ ችሏል።

የተጫዋቾች የጥራት ደረጃ ችግር የሌለበት ቡድኑ የፕሪምየር ሊጉን ውጤታማነት ቀመር ለመግኘት ሳምንታት ቢፈጁበትም አሁን ላይ ያገኘው ይመስላል ፤ ከፍተኛ ጫና ውስጥ የሰነበቱትና ስራቸውን ሊያጡ ይችላል በሚል ስጋት ላይ የከረሙት አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ በሰሞነኛ ሁለት ድሎች በመጠነም ቢሆን እፎይታን የቸራቸው ሲሆን ቡድን በቀጣይ ሳምንት ቅዱስ ጊዮርጊስን በሜዳው በሚያስተናግድበት ጨዋታ ይሄን የአሸናፊነት መንፈስ ለማስቀጠል ከፍተኛ ርብርብ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

– ስሜታዊው የድሬዳዋ ከተማ የአሰልጣኞች ቡድን

ትላንት በአዲስአበባ ስታዲየም ቅዱስ ጊዮርጊስ ድሬዳዋ ከተማን 3-2 በረታበት ጨዋታ በሁለተኛው አጋማሽ የድሬዳዋ ከተማው አምበል ያሬድ ዘውድነህ በጊዮርጊስ የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ በጊዮርጊስ ተጫዋቾች ጋር በተፈጠረ ንኪኪ በወደቀበትና ” አጨቃጫቂ የፍፁም ቅጣት ምት አጋጣሚ” ጨዋታውን የመራው ኢንተርናሽናል ዳኛ አማኑኤል ሀይለስላሴ በዝምታ ማለፉን ተከትሎ የድሬዳዋ ከተማ የአሰልጣኞች ቡድን አባላት እንዲሁም ተጠባባቂ ተጫዋቾች ለአጋጣሚው በተሻለ ቅርበት የነበረው የመስመር ዳኛ ላይ ብስጭታቸውን ተቋውማቸውን የገለፁበት መንገድ መታረም የሚገባው ነበር።

በከፍተኛ ደረጃ የማሰልጠን ልምድ በሌላቸው አዳዲስ አሰልጣኞች የሚመራው ቡድኑ በስሜት የመነዳት አዝማሚያዎች ስለመኖራቸው የቡድኑን ጨዋታዎች በተለያየ አጋጣሚ የተመለከተ ሰው ማስተዋል የሚችለው እውነታ ነው ፤ ዋና አሰልጣኛቸው በድህረ ጨዋታ ላይ በሰጡት ትችት አዘል አስተያየት በ3ኛ ሳምንት ጨዋታ ላይ ከአራት ጨዋታዎች መልስ ከቅጣት ያገኘው ቡድኑ አሁንም ቢሆን ስሜትን በመቆጣጠር ረገድ ያልተሰሩ ቀሪ የቤት ስራዎች ስለመኖራቸው የትላንቱ ጨዋታ አንዱ ማሳያ ነው።

ይባስ ብሎ ጨዋታው መጠናቀቁን ተከትሎ ከስምኦን ረዳቶች አንዱ የሆነው ወጣቱ አሰልጣኝ እዮብ ተዋበ ጨዋታውን ወደመሩት ዳኞች አቅንቶ ተቃውሞውን የገለፀበት እንዲሁም ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ በተወሰኑ የሁለቱ ክለብ ደጋፊዎች መካከል በተፈጠረው አለመግባባት ውስጥ የትኩረት ማዕከል መሆኑ አሰልጣኙ ገና እያበበ በሚገኘው የአሰልጣኝነት ህይወቱ ላይ መሰል ስሜታዊነት ጉዳዮች ጥላ እንዳያጠሉበት ስክነትን መላበስ ይገባዋል።

በሀገራችን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ መሰል ወጣት አሰልጣኞች በተለያዩ ቡድኖች ውስጥ በሀላፊነት ብቅ እያሉ መምጣታቸው በትውልድ ሽግግሮች ላይ ለሚታማው እግርኳሳችን መልካም ዜና ቢሆንም እነዚሁ አሰልጣኞች በስሜት ረገድ ስክነትን መላበስ እንደሚገባቸው የድሬዳዋ ከተማና ስሁል ሽረ ቡድኖች ሰሞነኛ ክስተት ማስተማሪያ ሆኖ አልፏል።

– ዕድለቢሱ ወልቂጤ ከተማ

በዘንድሮው የውድድር ዘመን ከከፍተኛ ሊግ ካደጉ ቡድኖች አንዱ የሆነውና በደግዓረግ ይግዛው የሚመሩት ወልቂጤ ከተማዎች በ8 ሳምንት የሊጉ ጉዞ ወጥ የሆነ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን በማሳየት ላይ ይገኛሉ። ቡድኑ ኳስን ለመቆጣጠር የማይቸገር በተደጋጋሚ የግብ እድሎችን የሚፈጥር ቢሆንም ከጨዋታዎች ሙሉ ሦስት ነጥብ ይዞ ለመውጣት ተቸግሯል። ቡድኑ በተከታታይ ባደረጋቸው ሦስት ጨዋታዎች ከተጋጣሚያቸው አንፃራዊ የበላይነት በመውሰድ ተደጋጋሚ አስቆጭ የግብ ሙራዎችን ማድረግ ቢችሉም ማሳካት የቻሉት አንድ ነጥብ ብቻ ነው። በትላንቱ ጨዋታ ምንም እንኳን በዐምናው የሊጉ ቻምፒዮን በጠባብ ውጤት ቢሸነፉም በሦስት አጋጣሚዎች የግቡ አግዳሚና ቋሚ ሙከራዎችን መክኖባቸዋል።

-የሚንገራገጨው ቅዱስ ጊዮርጊስና የተጫዋቾች ጉዳት

የቀደሙት ዓመታት ሞገሱ ቀስ በቀስ እየራቀው የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ በዘንድሮው የውድድር ዘመንም ወጥ የሆነ ብቃትን በሜዳ ላይ ለማሳየት እየተቸገረ ይገኛል። በአንድ የጨዋታ ሳምንት ጥሩ ነው ሲባል በቀጣይ ደግሞ በተጋላቢጦሽ ግራ የተጋባ ቡድን ሲሆን ተመልክተናል። ይህም ላለፉት ሁለት አየዓመታት ከሊጉ ክብር ለራቀው ክለብ ደጋፊዎች የሚዋጥ አልሆነም።

በትላንትናው ጨዋታ ምንም እንኳን ጨዋታውን በጠባብ ልዩነት ማሸነፍ ቢችሉም ከውጤቱ በላይ ትኩረት ሳቢ የነበረው የክለቡ ሁነኛ የግብ አምራቾች ሳልሀዲን ሰኢድና ጌታነህ ከበደ ባጋጠማቸው ጉዳት ተቀይረው ከሜዳ ለመውጣት መገደዳቸው ክለቡ ላይ ስጋት ፈጥሯል ፤ በቀጣይ ሁለቱ ተጫዋቾች በጉዳት ከሜዳ የሚርቁ ከሆነ ባለፉት ሶስት ሳምንታት በመጠኑም ቢሆን በግብ ማስቆጠር ረገድ መሻሻል ላሳየው ቡድኑ ትልቅ ጋሬጣ ይሆንበታል ተብሎ ይጠበቃል።

– በአቻ የተለከፈው አዳማ ከተማ

በ8ኛ ሳምንት ፕሪምየር ሊግ አዳማ ከተማ በሜዳውና በደጋፊው ፊት ከሀዋሳ ከተማ ጋር 1ለ1 በሆነ የአቻ ውጤት ተለያይቷል። ለወትሮው በሜዳው እጅግ አስፈሪ የሆነው አዳማ ከተማ ዘንድሮ ይህ አስፈሪነቱ አብሮት የለም እስካሁን በሜዳው ካደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች በሁለተኛ ሳምንት ወልቂጤ ከተማን ከረታበት ጨዋታ ውጭ የተቀሩትን አራት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ፈፅሟል።

በሊጉ እስካሁን ካደረጋቸው ስምንት ጨዋታዎች አንድ ብቻ አሸንፎ በስድስት ጨዋታዎች አቻ በመለያያየት በ12ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

– የሲዳማ ቡና የመለያ ለውጥ

ከዚህ ቀደም በዚሁ የሳምንቱ ዓበይት ጉዳዮች ላይ እንደጠቆምነው ክለቦች ለውድድር ዘመኑ የሚገለገሉባቸውንና የይዘት ማሻሻያ የተደረገባቸውን መለያዎች በብዛት በዓመቱ መጀመሪያ ለአዲሱ የውድድር ዘመን ይዘው ሲቀርቡ ቢስተዋልም እኛ ሀገር ግን ይህ ሁኔታ የተገላቢጦሽ ነው።

ሲዳማ ቡና አዲሱን የውድድር ዘመን ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲጠቀምበት በነበረው መለያ ቢጀምርም ትላንት በ8ኛ ሳምንት በአዲስ የመጀመሪያ መለያ ቀርቧል። መለያው ከቀደሙ መለያ አንፃር የተወሰኑ የይዘት ማሻሻያዎች ቢኖሩትም በዚህ ወቅት መሆኑ ግን ጥያቄ የሚያስነሳ ነው። የማልያ ለውጥ መኖሩ በክለቡ አመራሮች ዘንድ እርግጥ መሆኑ ከታወቀ የተለየ አስገዳጅ ሁኔታ እስካልኖረ ድረስ በውድድር ዘመኑ ጅማሮ ቢሆን የተሻለ ይሆን ነበር።

2. ተጫዋች ትኩረት

– የቀደመ ብቃቱን ዳግም ለማግኘት እየታተረ የሚገኘው ጋዲሳ መብራቴ

ሀዋሳ ከተማን ለቆ ያለፉትን ሁለት የውድድር ዘመናት በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት በተጠባባቂነት ያሳለፈው ጋዲሳ መብራቴ ዘንድሮ የቀደመ ብቃቱን መልሶ ለማግኘት በከፍተኛ ትጋት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።

ጥሩ ክህሎት እንዳለው በብዙዎች የሚታመነው ተጫዋቹ ዘንድሮ የቀደሙት ዘመናት መገለጫዎቹ የነበሩትን የፍላጎትና የትጋት ማነስ ችግሮች ለመቅረፍ ምን ያህል እየታተረ ስለመሆኑ የልጁን የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ መከታተል በቂ ማሳያ ነው። በትላንቱ የድሬዳዋ ከተማ ጨዋታም አንድ አስደናቂ የሆነች የቅጣት ምት ጎል ከማስቆጠር አልፎ ፤ ጌታነህ ያስቆጠራትን ሁለተኛ ጎል አመቻችቶ ሲሰጥ ለመጀመሪያዋም የመልሶ ማጥቃት ግብ እንቅስቃሴውን በማስጀመር በትላንቱ ጨዋታ ደምቆ ውሏል።

– አቡበከር ናስር ጉዳቶች እየተደጋገሙበት ይገኛል

ከሰሞኑ ድንቅ ብቃቱ ላይ የሚገኘው አቡበከር ናስር በአዲሱ የውድድር ዘመን ሁለተኛ ጉዳቱን በትላንትናው እለት ቡድኑ በፋሲል ከተማ በተሸነፈበት ጨዋታ የመጀመሪያ ደቂቃዎች አስተናግዷል።

በብሔራዊ ቡድን ግልጋሎት ምክንያት ዘግይቶ ክለቡን ተቀላቅሎ የነበረው አቡበከር ናስር የሊጉ የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታዎች በጉዳት ያመለጡት ሲሆን ከጉዳት መልስ መሻሻሎች ላሳየው ኢትዮጵያ ቡና ቁልፍ ተጫዋች መሆኑን እያስመሰከረ ቆይቷል። ከጉዳት መልስ ሶስት ግቦችን ማስቆጠር ችሎ የነበረው አቡበከር በውድድር ዘመኑ ሁለተኛ የሆነውን ጉዳት በትላንቱ ጨዋታ አስተናግዶ ገና በማለዳው ነበር በአላዛር ሽመልስ ተቀይሮ ከሜዳ የወጣው። ሜዳ ውስጥ ያለውን ያለስስት ሰጥቶ የሚጫወተው ተጫዋቹ ቀትላንቱ ጉዳት ከሁለት እስከ ሦስት ሳምንታት ከሜዳ ይርቃል።

– አማኑኤል ገ/ሚካኤል መቐለን መታደጉን ቀጥሏል

የአምናው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ አማኑኤል ገ/ሚካኤል በሂደት ጅማሮውን አሳሞሮ የሊጉን አናት ለተቆናጠጠው መቐለ ባለውለታ መሆኑን ቀጥሏል። ትላንት ቡድኑ ወደ ወልቂጤ አምርቶ በተቸገረበት ጨዋታ ወሳኝዋን ሶስት ነጥብ ያስገኘችላቸውን ብቸኛ ግብ በግሩም አጨራረስ ማስቆጠር ችሏል።

– ሙጂብን ቃሲም ግብ ማምረቱን ቀጥሏል

ፋሲል ከነማ ኢትዮጵያ ቡናን በረታበት ጨዋታ ልማደኛው ግብ አዳኝ ሙጂብ ቃሲም ሁለት ግቦችን አስቆጥሮ በውድድር ዘመኑ ያስቆጠራቸው የግብ መጠን 9 አድርሷል።
በሂደት ከጥሩ የመሀል ተከላካይነት ወደ ድንቅ የዘጠኝ ቁጥር አጥቂነት እየተሸጋገረ የሚገኘው ሙጂብ ዘንድሮ አምና በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ወቅት የነበሩበትን ክፍተቶች እያሻሻለ ይገኛል።

3. ድህረ ጨዋታ አስተያየት

– ካሳዬ አራጌ ስለተጫዋቾች ጉዳትና ስለቡድን ጥልቀት የሰጡት አስተያየት

የመጀመሪያ 11 ውስጥ የሚሰለፉ ተጫዋቾች ሲጎዱብህ የሚፈጥረው ነገር አለ። ግን ከዛ ጋር ተያይዞ ደግሞ ተጠባባቂ ላይ የምናስቀምጣቸው ተጫዋቾች እነዛን ተክተው የነሱን ሚና ሊሰሩ ይችላሉ ብለን ስለምናምን ይበልጥ የቡድን ስራ ላይ ነው ትኩረት የምንሰጠው። እያንዳንዱ ተጫዋች ዎጋ አለው። ምናልባት እንደዚህ አይነት ተጫዎቾች በጉዳት ለረዥም ጊዜ ልናጣ እንችላለን፤ ግን ያንን ምክንያት ማድረግ አግባብ አይመስለኝም። ሌሎቹ ተጫዋቾቻችንም ማድረግ ይችላሉ።

– ፋሲል ተካልኝ ቡድኑን በትላንቱ ጨዋታ ስላላገለገሉት ተጫዋቾችና ስለተፈጠረባቸው ተፅዕኖ

“ምንም ጥያቄ የለውም፤ ቋሚ ተሰላፊዎች ናቸው፤ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች ናቸው፤ ውጤትን መቀየር የሚችሉ ተጫዋቾች ናቸው። እነሱ አልጎዱኝም ማለት አልችልም። ግን በነሱ አለመኖር ጨዋታውን ማሳበብ አልፈልግም። በመጀመሪያው አርባአምስት ዕድሎች አግኝተን ነበር፡፡ በተለይ ጎል ከገባብን በኃላ ያንን አለመጠቀማችን በሁለተኛው አርባአምስት ከሜዳችን ወተን እንድናጠቃና በቂ የማጥቂያ ቦታ ለተጋጣሚያችን ለመስጠት ተገደናል፡፡

– ገብረክርስቶስ ቢራ ስለ ቡድኑ አቀራረብ እና ቆይታቸው

(ሽንፈቱ የመጣው በአጨዋወት ምክንያት ነው የሚለው) የአረዳድ ጉዳይ ነው። እንደኔ ታክቲክ ጨዋታን አያሸንፍም፤ የተጫዋቾች ፍላጎት እንጂ። ኳስ ወደፊት ቢሄድም የሚጠቀምበት ከሌለ ዋጋ የለውም። በሦስት አጥቂዎች ብንጫወትም ከፊት ምንም መፍጠር አልቻልንም። ባዬ ትንሽ ይፍጨረጨራል። ተጫዋቾችም በእንዲህ አይነት ጫና መጫወት አይችሉም።

አሁን ያለው ሁኔታ ተጫዋቾችን ሊያጫውት አይችልም። ጫናው እስከ ቤት ነው ያለው፤ በመንገድ ሲሄዱ ጫና አለ፤ ሜዳ ሲገቡ ጫና አለ፤ ስለዚህ በዚህ ውጥረት ውስጥ እንዴት ነው ኳሱን መቆጣጠር እና መጫወት የሚችሉት። ስለዚህ ተጫዋቾቼ ላይም መፍረድ አልችልም። ጨዋታው ላይ አበረታተውን ካለቀ በኋላ ቢሰድቡን ምንም አልቀየምም። ተፎካካሪ ቡድንን እያበረታታህ እንዴት ይሆናል።

ድቻ ለአራት ዓመታት ላለመውረድ ነው የተጫወተው። ስለዚህ ባንድ ጊዜ በነዘለህ ወጣት ተጫዋቾች ለውጥ ማምጣት አንችልም። አንድ ቀን ይታያል፤ አንድ ቀን ይጠፋል። ይህ ደግሞ ሊበረታታ ይገባል። ይሄን ቡድን ሙሉ 90 ደቂቃ ቢበረታታ ወደ ጥሩ ውጤት ይመጣ ነበር።

ለኔ ይህ የመጨረሻ ጨዋታዬ ነው። ባለፈውም ከቦርዱ ጋር ተነጋግረናል። በሁለቱ ጨዋታ በደጋፊ በኩል ያለውን ነገር ተመልክቼ እጫወታለሁ በሚል ነበር። ቦርዱም በቀጣይ ጨዋታዎች ውጤት የማይመጣ ከሆነ እኔም አልመጣም ነው ያልኩት። ነገ ስብሰባ አለ፤ ግን አልገኝም። ሀቁን ነው የምናገረው። ከድቻ ጋር ስላለኝ ጉዳይ ጨርሻለሁ። እነሱም ከሁለት ጨዋታ በኋላ ውጤት ካልመጣ የአሰልጣኝ ቡድኑን እናሰናብታለን ብለዋል። ስለዚህ ጨርሰናል ነው የምለው።

– ስምኦን ዓባይ ቡድን በተደጋጋሚ ግብ በመጀመሪያ ደቂቃ ማስተናገዱ ስለፈጠረባቸው የስነልቦና ጫና

“ከሁኔታው መደጋጋም የተነሳ ስራዎች እየሰራን ላይመስል ይችላል። ነገርግን በተቻለን አቅም ስራዎችን ለመስራት እየሞከርን እንገኛለን። ይህን ለማረም እየሄድንበት ባለነው አካሄድ ልጆቹን ከፍተኛ ጫና ውስጥ እየከተትናቸው እንገኛለን። ይህም ለስህተቶቹ በተደጋጋሚ መከሰት ምክንያት እየሆነብን ይገኛል።”

– አዲሴ ካሳ በሊጉ ስለተለመደው የሜዳ ውጭ ጨዋታዎች የጨዋታ አቀራረብ

እንደገለፅኩት ሁል ጊዜ ከሜዳ ውጪ ነጥብ ይዘህ ለመመለስ ነው መታተር ያለብህ። ለዚህም ነው ወደራሳችን የግብ ክልል ተጠግተን ጨዋታውን ያከናወነው። የመጀመሪያ እቅዳችን በመልሶ ማጥቃት ግብ ማስቆጠር የሚል ነበር። ግን እነሱ በጣም ጠጣር ስለነበሩ ይህንን ማድረግ አልቻልንም። በሁለተኛው አጋማሽ ግን ማድረግ የሚገባንን ተግብረን ነጥብ ይዘን ወጥተናል። ግብ ካስቆጠርንባቸው በኋላ ነቅለው ነበር ሲያጠቁ የነበረው። ይህንን ነገር በመልሶ ማጥቃት መጠቀም እንችል ነበር። ነገር ግን ይህንን አልተጠቀምንም።

4. በሁሉም የሚደቆሰው የስፖርት ሚዲያ

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሀገሪቱ በፍጥነት እየተስፋፋና እያደገ የሚገኘው አንዱ የሚዲያ ዘርፉ ነው። ከዚህ ጋር በየጊዜው እየጨመረ ከሄደው የቴሌቪዥንና ሬድዮ ቁጥር ጋር ተያይዞ የእግርኳስ ውድድሮች በተለይም በአዲስአበባ ስታዲየም የሚደረጉ ውድድሮች (የአብዛኛዎቹ የመገናኛ ብዙሀን ዋና መቀመጫ አዲስአበባ ከመሆኑ አንፃር) ከፍተኛ ሽፋን ሲያገኙ ይስተዋላል።

ይህ በጎ ጅምር በመልካምነቱ የሚወሰድ ቢሆንም በሚድያዎቹ ዘገባዎች ጥራት ላይ ችግሮች አሁንም በስፋት ይስተዋላሉ። በትላንቱ የቅዱስ ጊዮርጊስና ድሬዳዋ ጨዋታ መጠናቀቅ በኃላ በሁለቱ ክለብ ደጋፊዎች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ተከትሎ በስፍራው የአሰልጣኞች ድህረ ጨዋታ አስተያየት ለመቀበል የተገኙት የመገናኛ ብዙሀን አባላት ሁኔታውን በካሜራቸው እንዳያስቀሩ ሲደረግ የነበረው ማዋከብ እንዲሁም የነበረውን ሁነት በካሜራቸው ይዘዋል ብለው ባሳቧቸው ግለሰቦች ካሜራን ማህደር በመክፈት ፋይሎች እንዲያጠፉ የተሄደበት መንገድ እጅግ አሳዛኝ ገጠመኝ ነበር።

መገናኛ ብዙሀን በተገኙባቸው ቦታዎች የሚመለከቷቸው እያንዳንዱ ሁነት በግላዊ ምልከታቸው እንዲሁም የሙያ ስነ ምግባሩን በጠበቀ መልኩ የመሰነድም ሆነ የማሰራጨት መብት ቢኖራቸውም በሀገራችን ግን በተለያዩ ሜዳዎች የደጋፊ ማህበራት አመራሮች ጭምር የሚፈጠሩትን አላስፈላጊ ድርጊቶች ከማውገዝና እንዲታረሙ ከማድረግ ይልቅ ሁኔታውን በታዘቡ የመገናኛ ብዙሃን አባላት ላይ ሽፋን እንዳይሰጡ ጫና ማሳደር ሆነ ማስረጃዎችን ከማህደራቸው እንዲያስወግዱ ማስገደድ ሊታረም የሚገባ ጉዳይ ነው።

5. የተጫዋቾች የመለያ ቁጥር

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ ክለቦች በአመዛኙ በሜዳቸውና ከሜዳቸው ውጭ በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች የሚገለገሉባቸው ሁለት አለፍ ሲል ደግሞ ሦስት የተለያየ የቀለም አማራጮች የተዘጋጁ መለያዎች አሏቸው።

በእነዚህ የተለያዩ መለያዎች ላይ ግን የተጫዋቾች መለያ ቁጥሮች ግን ወጥነት ሲጎድላቸው ይስተዋላል። በብዛት ቡድኑ በሚገለገልበት የመጀመሪያ ተመራጭ መለያ ላይ በአንድ ቁጥር የሚታወቅ ተጫዋች በሁለተኛና ሦስተኛ ተመራጭ መለያዎች ላይ ሌላ ቁጥር ለብሶ መመልከት በሀገራችን እግርኳስ የተለመደ ጉዳይ ከሆነ ውሎ አድሯል።

ለማሳያነት ሰበታ ከተማ ፣ ወላይታ ድቻ ፣ ስሁል ሽረ ፣ ድሬዳዋ ከተማ ተጫዋቾች የመለያ ቁጥር በተደጋጋሚ ሲለዋወጥ ይስተዋላል። ክለቦች እጅግ ከፍተኛ በጀት አውጥተው የትጥቅ ግዥዎችን መፈፀማቸው ካልቀረ መሠል ተራ የሚመስሉ ነገርግን የክለቦቻችን ኃላ ቀር አሰራር የሚያሳብቁ አካሄዶች መታረም ይኖርባቸዋል።

ሁኔታው በተለይም እንደ ሶከር ኢትዮጵያ በየጨዋታው ቀጥታ የውጤት መግለጫ እና የመሳሰሉትን መረጃዎች ለሚያስተላልፍ ተቋም እክል የሚፈጥር ከመሆኑ በተጨማሪ ወደፊት ለጨዋታ ትንተና የሚያግዙ ሶፍትዌሮችን በጨዋታዎች ላይ ለመተግበር አዳጋች ያደርጋቸዋል። በስታዲየም ለሚገኝ ተመልካችም የቁጥር መቀያየር ብዥታ መፍጠሩ አይቀሬ ነው።

አወዳዳሪውም አካል በሌሎች ሀገራት እንደሚደረገው እስከ ቁጥር መፃፍያ ፎንትና ቀለም ስብጥር ድረስ ቁጥጥር ማድረግ እንኳን ባይቻል የተጫዋቾች የመለያ ቁጥር ወጥ እንዲሆን አስገዳጅ የህግ ማዕቀፍ ሊያበጅ ይገባል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ