የባህር ዳር ከተማ ተጫዋቾች ልምምድ አልሰሩም

ትናንት ከሰዓት ከሀዋሳ ወደ ባህር ዳር የገቡት የጣናው ሞገድ ተጫዋቾች ዛሬ መደበኛ ልምምዳቸውን እንዳላከናወኑ ተሰምቷል።

ከዚህ ቀደም ሦስቱ የባህር ዳር ከተማ የውጪ ተጨዋቾች (ሀሪስተን ሄሱ፣ ማማዱ ሲዲቤ እና አዳማ ሲሶኮ) ከደሞዝ ጋር በተያያዘ 4 መደበኛ ልምምድ እና 1 የነጥብ ጨዋታ (ከፋሲል ከነማ ጋር) እንዳመለጣቸው ይታወሳል። ዛሬ ደግሞ ሁሉም የቡድኑ ተጫዋቾች ቃል የተገባላቸው ደሞዝ እና ማበረታቻ (ኢንሴንቲቭ) ስላልተሰጣቸው መደበኛ ልምምዳቸውን እንዳላከናወኑ ታውቋል።

ይህንን አስመልክቶ ጥያቄ ያቀረብንላቸው የቡድኑ ሥራአስኪያጅ አቶ ልዑል የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተውናል። “ልክ ነው። ዛሬ ልምምድ አልሰሩም። ቀድመን ዛሬ ክፍያውን እንደምንፈፅምላቸው ነግረናቸው ነበር። ነገር ግን ተጫዋቾቹ ወደ ሜዳ አልተጓዙም። አመሻሽ 11 ሰዓት ላይ ግን ለሁሉም ተጨዋቾች ገንዘቡን አስገብተናል። ይህንን የሚያሳይ ደረሰኝ ደግሞ የቡድኑ ካምፕ ድረስ በመሄድ ለአሰልጣኙ እና ለቡድን መሪው አሳይተናል። ስለዚህ ቡድኑ ከነገ ጀምሮ መደበኛ ልምምዱን ይጀምራል።”

ቡድኑ የ9ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መርሃ ግብሩን ቅዳሜ ወልዋሎን በሜዳው በመጋበዝ የሚያከናውን ይሆናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ