“የወላይታ ድቻ ህጋዊ አሰልጣኝ እኔ ነኝ ” አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ

ከወላይታ ድቻ ጋር ስልክ ዘግተው ጥለው ሄደዋል በሚል ክለቡ እንደተሰናበቱ የተገለፀው አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ አሁንም የወላይታ ድቻ አሰልጣኝ እንደሆኑ ገልፀው ነገ ልምምድ ለማሰራት እንደተዘጋጁ በተለይ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡

ከአሰልጣኙ ጋር ያደረግነውን አጭር ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡-

ስለመሰናበታቸው

” እነሱ ከክለቡ ወጥቷል ብለው ገልፀዋል፤ በራሳቸው ገፅ ላይ ያንን ነው እኔም ያየውት። ሆኖም እኔ ከወላይታ ድቻ አልተባረርኩም፤ አሁንም የወላይታ ድቻ ህጋዊ አሰልጣኝ ነኝ። ምክንያቱም ባለፈው የተነጋገርነው ከሁለት ጨዋታ በኃላ እንገመግማለን የሚል ነው። ያ ማለት ከግምገማ በኃላ ማባረር ሊኖር ይችላል፤ ወይም ሌሎች ያበላሹ ተጫዋቾች አልያም እኔም ከሆንኩ እርምጃ ይወሰዳል። እነዚህ ነገሮች ደግሞ ሳይደረጉ ነው ስለመሰናበቴ የገለፁት።”

በድሕረ ጨዋታ አስተያየት ላይ “ከወላይታ ድቻ ጋር ያለኝን ነገር ጨርሻለሁ” ስለማለታቸው

“አስተያየቴ በሌላ መልኩ ተተርጉሞ ሊሆን ይችላል። እኔ ያልኩት ‘የሁለት ጨዋታ እድል ተሰጥቶን ነበር። ውጤት ስላልመጣ በኛ በኩል ጨርሰናል። ቦርዱ ተነጋግሮ መቀጠልም ሆነ ማሰናበት ይችላል።’ ነው ያልኩት።”

ስልክ ዘግተው ጠፍተዋል ስለመባሉ

“..ትላንት ሀዋሳ ህክምና ነበረኝ። ከፈለጋችሁ ዶክተር ሙላት (ሀኪሜ ስለሆነ) መጠየቅ ይቻላል። እጄ ላይ የወጣ ሽፍታ ነበር፤ ውሀ ሲነካኝ ቀኝ እጄ ላይ ሽፍ እያለ ይወጣል፡፡ አውራ ጣቴንም ስለሚደነዝዘኝ ነርቭ እንዳይሆን ብዬ ነው የመጣሁት። በዚህ መሐል ግን ማንም የደወለልኝ የለም። እነሱ ራሱ ጥሎ ሄዶ ነው ይላሉ። አንደኛ እኔ የምገናኘው ከቴክኒክ ዳይሬክተሩ ጋር ብቻ ነው። ከዛ ውጪ በስራዬ ከማንም ጋር ተገናኝቼ አላውቅም። ህጉ የሚለው በቴክኒክ ዳይሬክተሩ በኩል ነው ወደነሱ ልቀርብ የምችለው። ወደ ተጫዋች ደግሞ በእኔ በኩል ማንም ሊመጣ አይችልም፡፡ ይሄን ነው ያልተረዱኝ እንጂ የሚያሸሸኝም ነገር የለም። የሚያስፈራኝም ነገር የለም። ደጋፊው ከጎኔ ነው። ስልኬንም የዘጋሁት ሁሉም ሚዲያዎች ሊያስቸግሩኝ ስለሚችሉ ብዬ ብቻ ነው። ከምሰማቸው ነገሮች ተነስቼ ግን ለክለቡ ኃላፊ ለወላይታ ድቻ መልካሙን እመኛለሁ ብዬ ቴክስት ልኬያለሁ። ይህን ያልኩት ወጥተሀል የሚሉ ነገሮች ስለሰማሁ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውጪም የምላቸው ነገሮች የሉም። እኔ እኮ ለመልቀቅ ከፈለግኩ በደብዳቤ መግለፅ እችላለሁ፤ ግን ያንን አላደረግኩም። ለቀሀል ተብዬ ደብዳቤም አልደረሰኝም። ነገ ሶዶ እመለሳለሁ፤ ለህክምና ስለመጣሁ የግድ እመለሳለሁ። እንደውም ስለቀጣይ ስለማሰራቸው የልምምድ መርሐግብሮች እየተዘጋጀሁ ነው የምገኘው፡፡”


© ሶከር ኢትዮጵያ