ክለቦች በደሞዝ ክፍያ ቅሬታ መታመሳቸውን ቀጥለዋል

ወርኃዊ ደሞዝ አልተከፈለንም በማለት ተደጋጋሚ ቅሬታ የሚያሰሙ ቡድኖች እየተበራከቱ በመጡበት ሊጋችን የአዳማ ከተማ ተጫዋቾች ልምምድ አቋርጠዋል።

በፕሪምየር ሊጉ ተገማች ያልሆነ ጉዞ እያደረገ የሚገኘው አዳማ ከተማ ነባር ተጫዋቾቹ የአራት ወር፣ አዲስ ፈራሚዎች የሁለት ወር ወርኃዊ ደሞዝ ይከፈለን የሚል ተደጋጋሚ ቅሬታ እያቀረቡ ቢገኙም የሚሰማቸው በማጣታቸው ልምምድ መስራት ካቋረጡ ሁለተኛ ቀናቸው ሆኗል።

ለቡድኑ ዋና አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለም እስካሁን የፊርማ ገንዘብ እንዳልተከፈላቸው እየተሰማ ሲሆን በቡድኑ ተጫዋቾች ዘንድ ያላቸው የመጫወት ፍላጎት እየቀዘቀዘ መምጣቱን ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ተጫዋቾች ገልፀውልናል። ልምምዳቸውን እስከ መቼ እንደሚያቋርጡ ባይታወቅም የፊታችን ቅዳሜ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ከሜዳቸው ውጭ ለሚያደርጉት ጨዋታ ይጓዙ ይሆን የሚለው ጉዳይም እስከ አመሻሹ ድረስ የሚታወቅ ይሆናል።

በዚት የውድድር ዓመት በደሞዝ ክፍያ መዘግየት ባህር ዳር ከተማ እና ጅማ አባ ጅፋርን ጨምሮ ሌሎችም ክለቦች ቅሬታ እየቀረበባቸው ይገኛል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ