የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ሽኝት ተደረገላቸው

ነገ የመጀመርያ የማጣርያ ጨዋታውን ለማድረግ ወደ ቡሩንዲ የሚያቀናው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ምሽቱን በኢትዮጵያ ሆቴል ሽኝት ተደርጎለታል።

በሽኝት መርሐ ግብሩ ላይ የዋልያዎቹ አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ፣ የሉሲዎቹ ዋና አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው፣ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል እና የሴቶች እግርኳስ ልማት ኮሚቴ ሰብሳቢ ሶፊያ አልማሙን እንዲሁም አቶ ኢብራሂም አህመድ እና አቶ ሰለሞን ገብረሥላሴ የተገኙ ሲሆን ንግግር ከተደረገ በኋላ የመልካም ምኞታቸውን ገልፀዋል። በኤልሽዳይ ቤከማ ኢንተርቴይንመንት የተዘጋጀ የቪድዮ ትንታኔ ቀርቦ የባንዲራ ርክክብ ከተደረገ በኋላ የመርሐ ግብሩ ማሳረጊያ ሆኗል።

በኮስታሪካ እና ፓናማ አስተናጋጅነት የሚካሄደው የሴቶች ከ20 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ የማጣርያ ጨዋታ በሳምንቱ መጨረሻ ሲከናወን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከቡሩንዲ ይጫወታል። በአሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል እና ህይወት አረፋይኔ የሚመራው ቡድኑ ለዚህ ጨዋታ ዝግጅት ይረዳው ዘንድ በአዲስ አበባ ስታዲየም በቀን ሁለት ጊዜ ልምምድ ሲያከናውን የቆየ ሲሆን ሁለት የአቋም መለኪያ ጨዋታ ከሀገር ውስጥ ቡድኖች ጋር አከናውኗል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ