ሳላዲን ሰዒድ እና ተደጋጋሚ ጉዳቱ

ያለፉትን ሁለት ዓመታት ተደጋጋሚ ጉዳት እያስተናገደ የሚገኘው አንጋፋው አጥቂ ሳላዲን ሰዒድ ደግመኛ ለሳምንታት ከሜዳ ሊርቅ ይችላል።

በተለያዩ ጉዳቶች ምክንያት ከሜዳ እየራቀ እና እየተመለሰ በመጫወት በሚያጋጥመው ጉዳት ምክንያት የታሰበውን ያህል አገልግሎት ለፈረሰኞቹ መስጠት የተቸገረው ሳላዲን ሰዒድ ዳግመኛ የጉልበት ጉዳት አጋጥሞታል። በሰምንተኛው ሳምንት ከድሬደዋ ከተማ ጋር በነበረው ጨዋታ የጉልበት ጉዳት ያስተናገደው ሳላዲን የMRI ምርመራ በማድረግ ትናንት የጉዳቱ ውጤት ምንያህል ጊዜ ከሜዳ እንደሚያርቀው በህክምና ባለሙያዎች ተገልፆለታል። ጉዳቱ ብዙም የሚያሰጋ እንዳልሆነ ቢገለፅም በአግባቡ ለማገገም ለአራት ሳምንታት ከሜዳ እንደሚርቅ ተነግሮታል።

ይህም ማለት ለአራት ሳምንት እረፍት በማድረግ ከጉዳቱ በማገገም ወደ ልምምድ ተመልሶ ለጨዋታ ብቁ ሆኖ ወደ ሜዳ ለመመለስ ተጠባቂውን የሸገር ደርቢን ጨዋታ ጨምሮ ከዚህ በኋላ እስከ አንደኛው ዙር መጨረሻ ድረስ ለቅዱስ ጊዮርጊስ አገልግሎት ላይሰጥ እንደሚችል ተገምቷል።

ሳላዲን በዚህ ዓመት ብቻ ከጉዳት ጋር በተያያዘ ከአንዴም ሁለት ሦስት ጊዜ ከሜዳ እየራቀ ወደ ሜዳ በመመለስ ፈታኝ የሆነ የእግርኳስ ህይወትን እያሳለፈ ይገኛል።

ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በተያያዘ የጉዳት ዜና ድሬዳዋን 3-2 ባሸነፉበት ጨዋታ በጉዳት ተቀይሮ የወጣው ጌታነህ ከበደ ወደ ልምምድ መመለሱ እና ቅዳሜ ከሀዲያ ሆሳዕና ለሚያደርጉት ጨዋታ ብቁ መሆኑ ታውቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ