የአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ እና ወላይታ ድቻ ጉዳይ መቋጫ አግኝቷል

በዘንድሮ ዓመት ወላይታ ድቻን ለማሰልጠን ተረክበው ከስምንት ጨዋታ በላይ መሻገር ያቃታቸው አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ከወላይታ ድቻ ጋር በስምምነት ተለያይተዋል።

አሰልጣኙ ባሳለፍነው ቅዳሜ ከሱሑል ሽረ ሽንፈት በኃላ በሰጡት አስተያየት ከክለቡ ጋር የመቆየታቸው ጉዳይ ያበቃለት እንደሆነ ጠቁመው የነበረውና ኃላ ላይ የክለቡ ህጋዊ አሰልጣኝ መሆናቸውንና አለመለያየታቸውን መናገራቸው ብዙዎችን ሲያወዛግብ ቆይቷል። በአንፃሩ የወላይታ ድቻ አመራሮች አሰልጣኙ በገዛ ፍቃዳቸው ስልክ በማጥፋት ሊገኙ እንዳልቻሉ እና ጥር 04 ቀን በወጣ ማስታወቂያ ወደ መደበኛ ሥራቸው እንዲመለሱ መጠየቁ ይታወቃል።

ዛሬ አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ክለቡ ፅህፈት ቤት በመገኘት ከቡድኑ አመራሮች ጋር ውይይት ካደረጉ በኃላ በሁለቱም ወገኖች ስምምነት ለመለያየት መስማማታቸውን አረጋግጠናል። ይህም ተከትሎ አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ በ2012 የውድድር ዘመን ከክለባቸው ጋር የተለያዩ ቀዳሚ አሰልጣኝ ያደርጋቸዋል።

አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ክለቡን የተረከቡት በዚህ ዓመት ሲሆን ቡድኑ በሊጉ ከስምንት ጨዋታ አንድ ብቻ አሸንፎ በሠንጠረዡ ግርጌ ላይ ይገኛል።


© ሶከር ኢትዮጵያ