ለተጫዋቾች ደሞዝ የመክፈል ችግር ሰለባ ከሆኑ ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው አዳማ ከተማ ተጫዋቾቹ ልምምድ ካቋረጡበት አራተኛ ቀን ሆኖታል።
በዘጠነኛው ሳምንት ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ላለባቸው ጨዋታ እስካሁን ምንም ዓይነት የጉዞ እንቅስቃሴ ያላደረጉት አዳማዎች በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ የክለቡን ጊዜያዊ ተወካይ አቶ ለማ በተደጋጋሚ በእጅ ስልካቸው ብንደውልም ስብሰባ ነኝ በሚልና ኋላ ላይ ደግሞ ስልክ ባለማንሳት ክለቡ ያለበትን ወቅታዊ ሁኔታ ለማወቅ ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
የክለቡ አመራሮች ትናንት አመሻሽ ላይ የቡድኑ አሰልጣኞች እና አንበሉን በመጥራት “ያለውን ችግር ለመፍታት ጥረት እያደረግን ነው። እናንተ ተጫዋቾችን በማሳመን ወደ ድሬደዋ ለመሄድ ዝግጅት አድርጉ።” ብለው የሰጧቸውን ሀሰብ ይህንን ዘገባ እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ አብዛኛው ተጫዋቾች “ክፍያው እስካልተፈፀመልን ድረስ ምንም አይነት እንቅስቃሴ አናደርግም።” በማለት ውድቅ ማድረጋቸውን ሰምተናል።
ተጫዋቾቹ በዚህ አቋማቸው መፅናታቸው ያሳሰባቸው የክለቡ አመራሮች ክፍያውን ለመፈፀም እየተሯራጡ ሲሆን ዛሬ አመሻሽ አልያም ነገ ክፈረያውን ፈፅመው ለድሬዳዋ ጨዋታ ሊያመሩ እንደሚችሉ ሰምተናል።
አዳማ ከተማ ክፍያው ባለመፈፀሙ የድሬዳዋ ጨዋታ የሚያመልጠው ከሆነ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መሳተፍ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ፎርፌ የሰጠበትን ታሪክ ያፃፋል ማለት ነው።
በክለቡ ጉዳይ ያሉትን አዳዲስ መረጃዎች እንዳገኘን የምናቀርብ ይሆናል።
© ሶከር ኢትዮጵያ