ቅድመ ዳሰሳ | ስሑል ሽረ ከ ፋሲል ከነማ

የፕሪምየር ሊጉ ዘጠነኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገ እና ከነገ በስቲያ ሲካሄዱ የነገውን ብቸኛ መርሐ ግብር እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

ስሑል ሽረ በአሰልጣኝ ሳምሶን አየለ ስር ከጨዋታ ጨዋታ እየተሻሻለ መጥቷል። በተለይም የቡድኑ የመልሶ ማጥቃት አጨዋወቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ጥሩ መሻሻሎች በማሳየት በዚ ሰዓት በሊጉ አስፈሪ የመልሶ ማጥቃት ካላቸው ቡድኖች አንዱ ሆኗል።

የስሑል ሽረ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
አሸነፈ አሸነፈ አቻ አቻ አቻ

ሽረዎች በሊጉ የመጀመርያ ጨዋታዎች እጅግ ደካማ የሚባል የተከላካይ ክፍል የነበራቸው ሲሆን ባለፉት ጨዋታዎች የአማካይ ክፍሉን ለተከላካይ ጥምረቱ ሽፋን እንዲሰጥ ካደረጉ በኃላ ችግራቸው በተወሰነ መልኩ ቀርፈው ጥሩ የመከላከል አደረጃጀት ሰርተዋል። የነገው ተጋጣሚያቸው ባለፉት ጨዋታዎች በርካታ ጎሎች ያስቆጠረውና የሊጉ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሲነት የሚመራ አጥቂ ባለቤት የሆነው ፋሲል ከነማ እንደመሆኑም የተከላካይ ክፍላቸው ይፈተናል ተብሎ ይጠበቃል።

የተለጠጡ የመስመር አማካዮች እና ከሳጥን ውጭ እምብዛም ተሳትፎ በሌላቸው አጥቂዎች የተዋቀረው ስሑል ሽረ ባለፉት ጨዋታዎች በመልሶ ማጥቃት እና ፈጣን የማጥቃት ሽግግር ላይ በርካታ ጥሩ ለውጦች ቢያሳይም ዕድሎች ወደ ግብ መቀየር ግን የቡድኑ ዋነኛ ደካማ ጎን ነው።

በሁሉም ረገድ ለውጦች ያደርጋሉ ተብለው የማይጠበቁት ስሑል ሽረዎች በነገው ጨዋታ በጉዳት የሚያጡት ተጫዋች የለም። ልምምድ የጀመረው አዳም ማሳላቺ ወደ መጀመርያ አሰላለፍ የሚመለስበት ዕድል እንዳለም ይገመታል።

የፋሲል ከነማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
አሸነፈ አቻ አሸነፈ አቻ አሸነፈ

ከሜዳቸው ውጪ ማሸነፍ የከበዳቸው ዐፄዎቹ በዚህ ወቅት በጥሩ መነቃቃት የሚገኘው እና በኃላ ክፍሉ በቀላሉ ክፍተት የማይሰጥ ቡድን ጋር መገናኘታቸው ፈተናውን ከፍ ያደርግባቸዋል።

በአመዛኙ በኳስ ቁጥጥር ተመስርተው መሐል ለመሐል በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ለማጥቃት ጥረት የሚያደርጉት 0ፄዎቹ የመከላከል ባህሪ ባላቸው አማካዮች የተሞላውን የስሑል ሽረ ቡድን ላይ በርካታ የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ይቸገራሉ ተብሎ ስለሚጠበቅ የማጥቃት አጨዋወታቸው መስመር ላይ የተመረኮዘ ይሆናል ተብሎ ይገመታል።

ከዚህ በተጨማሪ ባለፉት ጨዋታዎች ጎል ለማስተናገድ ያስገደዳቸው የመከላከል ቅርፅ የነበራቸው ዐፄዎቹ በነገው ዕለት የስሑል ሽረን መልሶ ማጥቃት ለመመከት የተለየ አቀራረብ ይኖራቸዋል ተብሎ ይጠበቃል። በተለይም የኳስ ቁጥጥርን በመቀነስና ሽረዎች ኳስ እንዲይዙ በማድረግ ክፍተቶችን ማግኘት የመጀመርያ ኢላማቸው እንደሚሆን ይጠበቃል።

ዐፄዎቹ ያሬድ ባዬ፣ አብዱራህማን ሙባረክ፣ እንየው ካሳሁን እና ሰለሞን ሀብቴ ከጉዳት ቢመለሱላቸውም ለጨዋታ ብቁ ባለመሆናቸው ወደ መቐለ አልተጓዙም።

ግምታዊ አሰላለፍ

ስሐል ሽረ (4-2-3-1)

ምንተስኖት አሎ

ክብሮም ብርሀነ – ዮናስ ግርማይ – አዳም ማሳላቺ – ረመዳን የሱፍ

ሀብታሙ ሽዋለም – ነፃነት ገብረመድኅን

ዲድዬ ለብሪ – ያስር ሙገርዋ – አብዱለጢፍ መሐመድ

ፋሲል ከነማ (4-2-3-1)

ሚኬል ሳማኬ

ዓለምብርሀን ይግዛው – ሰዒድ ሀሰን – ከድር ኩሊባሊ – አምሳሉ ጥላሁን

ጋብርኤል አሕመድ – ሀብታሙ ተከስተ

ሽመክት ጉግሳ – ሱራፌል ዳኛቸው – ኦሴይ ማውሊ

ሙጂብ ቃሲም


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ