ድሬዳዋ ከተማ አሰልጣኝ እና ተጫዋቾችን አስጠነቀቀ

በወራጅ ቀጠናው ውስጥ የሚገኘው ድሬዳዋ ከተማ ናይጄርያዊው አጥቂው ባጅዋ አደገሰንን ጨምሮ ለአምስት ተጫዋቾች እና የአሰልጣኝ ቡድን አባል ማስጠንቀቂያ መስጠቱን አስታውቋል።

ክለቡ በይፋዊ ገፁ እንዳስታወቀው ” በስምንተኛ ሳምንት የሊግ ጨዋታ አዲስ አበባ ላይ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያደረገው ጨዋታ ከተጠናቀቀ በኋላ በጥቂት የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ያልተገባ በደል ቢደርስባቸውም ክለቡ የሚታወቅበትንና መልካም ሥነምግባር ወደ ጎን በመተው 4 ተጫዋቾቹን እና 1 አሰልጣኝ ሁኔታዎችን በጨዋነትና በመልካም ስነምግባር ማረጋጋት ነበረባቸው።” በማለት በቃል ደረጃ መገሰፁን አስታውቋል፡፡ ክለቡ የገሰፃቸውን ተጫዋቾች እና አሰልጣኝ ስም ከመግለፅ ግን ተቆጥቧል።

ሌላው ማስጠንቀቂያ የደረሰው ናይጄርያዊው አጥቂ ባጅዋ አደገሰን ነው። ክለቡ በፌስቡክ ገፁ እንዳለው ወደ ቡድኑ ከመጣበት ጊዜ አንስቶ የሚጠበቅበትን ግልጋሎት ማበርከት ባለመቻሉ ከ15 ቀናት በፊት የቃል ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ አቋሙን ባለማሻሻሉ በድጋፊ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።

በውድድር ዓመቱ መጀመርያ ብርቱካናማዎቹን የተቀላቀለው ባጅዋ ስምንት ሳምንታትን ባስቆጠረው ፕሪምየር ሊግ አንድ ጨዋታ ላይ ብቻ የመጀመርያ ተሰላፊ ሆኖ የተጫወተ ሲሆን በሌሎቹ ጨዋታዎች ተቀይሮ እየገባ ቢጫወትም ምንም ጎል ባለማስቆጠር ተጽዕኖ መፍጠር አልቻለም።

ለሁለተኛ ጊዜ ተጫዋቾችን ያስጠነቀቀው ድሬዳዋ ከተማ በ9ኛው ሳምንት በደሞዝ ምክንያት ጨዋታውን ስለማድረጉ እያጠራጠረ ከሚገኘው አዳማ ከተማ ጋር በሜዳው ይጫወታል።

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ