ሲዳማ ቡና ከጉዳት እያገገመ የሚገኘውን አማካይ ውል አራዘመ

በጉዳት ረዘም ያለ ጊዜ ከሜዳ ርቆ የቆየው የሲዳማ ቡናው የአማካይ ስፍራ ተጫዋች ወንድሜነህ ዓይናለም በክለቡ ለተጨማሪ ዓመት ውሉን ለማራዘም ከስምምነት ደርሷል፡፡

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከርቀት ግብ በማስቆጠር ከሚጠቀሱ ተጫዋቾች አንዱ የሆነው ወንድሜነህ በ2010 የውድድር ዘመን ደቡብ ፖሊስን ለቆ ወደ ሲዳማ ቡና ካመራ በኋላ ጥሩ ጊዜ በክለቡ ያሳለፈ ሲሆን በተለይ እስከመጨረሻው ሳምንት ድረስ በዋንጫ ፉክክር ውስጥ በቆየው የዐምናው ሲዳማ ቡና ቡድን ላይ ጎልተው ከወጡ ተጫዋቾች አንዱ ነበር፡፡ ሆኖም በገጠመው የተረከዝ ጅማት መበጠስ ያለፉትን ስድስት ወራት ከሜዳ ለመራቅ ተገዷል፡፡

አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፁት ተጫዋቹ ኦፕራሲዮን በማድረግ አሁን ላይ በመልካም ጤንነት ላይ የሚገኝ ሲሆን ወደ ሜዳ ሲመለስ የሚሰጣቸውን ግልጋሎት ቴሳቢ በማድረግ ለተጨማሪ አንድ ዓመት ውሉ እንደተራዘመ ገልፀዋል፡፡

የአማካይ ሥፍራ ተጫዋቹ ወንድሜነህ በቅርቡ ወደ ልምምድ የሚመለስ ሲሆን ከሁለተኛው ዙር ጀምሮም ለክለቡ ግልጋሎት እንደሚሰጥ አሰልጣኙ ጨምረው ገልጸዋል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ