ቅድመ ዳሰሳ | መቐለ 70 እንደርታ ከ ሰበታ ከተማ

በሊጉ ዘጠነኛ ሳምንት መሪው መቐለ 70 እንደርታዎቹ ሰበታ ከተማን ነገ የሚያስተናግድበት ጨዋታን እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

ወሳኝ የሜዳ ውጪ ድልን ጨምሮ ተከታታይ ጨዋታዎች አሸንፈው ከአናት በመቀመጥ በጥሩ ጉዞ ላይ የሚገኙት መቐለዎች በነገው ዕለት በሜዳቸው ሰበታ ከተማን በማሸነፍ መሪነታቸውን ለማጠናከር ወደ ሜዳ ይገባሉ።

የመቐለ 70 እንደርታ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
አሸነፈ አሸነፈ ተሸነፈ አሸነፈ አሸነፈ

አሰልጣኝ ገብመድህን ኃይሌ ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ወቅት ከነበራቸው ቡድን በእጅጉ የሚመሳሰል ቡድን ገንብተዋል። በሊጉ መጀመርያ ከነበራቸው አቀራረብ ለየት ባለ መልኩ አጨዋወታቸው ቀጥተኛ በማድረግም ቡድኑ በውጤት ረገድ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል እንዲያሳይ አድርገውታል።

በዋነኝነት አማኑኤል ገብረሚካኤል፣ ዮናስ ገረመው እና ያሬድ ከበደን የሚያሳትፈው የቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት ጎሎች እያገኘ ያለው በግለሰቦች ጥረት ቢሆንም በሒደት ኦኪኪ ኦፎላቢን ማሳተፍ መጀመሩ የማጥቃት ጥምረቱን ጥንካሬ አላብሶታል። ከዚህ በተጨማሪ በርካታ የመስመር ተጫዋቾች አማራጭ ያላቸው መቐለዎች የመስመር አጨዋወትም ሁለተኛው አማራጫቸው የሚሆንበት ዕድል የሰፋ ነው።

መቐለዎች ሚካኤል ደስታን በጉዳት አያሰልፉም። በትናንትናው ዕለት ልምምድ ያልሰራው ኦኪኪ ኦፎላቢም የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ ነው።

የሰበታ ከተማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
አሸነፈ ተሸነፈ አሸነፈ አቻ አሸነፈ

በሜዳቸው ባሳኳቸው ተከታታይ ነጥቦች ደረጃቸው ያሻሻሉት አዲስ አዳጊዎቹ ከሜዳቸው ውጭ ከመቐለን ነጥብ ይዘው መመለስን አቅደው ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይታመናል።

ከሜዳቸው ውጭ ባደረጓቸው ጨዋታዎች በአብዛኛው ቀጥተኛ እና በመስመር በሚደረጉ ፈጣን የማጥቃት አጨዋወት የግብ ዕድል ጥረት የሚያደርጉት ሰበታዎች በዚህ ጨዋታ የኳስ ቁጥጥር መሰረት ያደረገ አቀራረብ ይኖራቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

በዚህም ሰበታዎች የተጠቀሰው አጨዋወት መርጠው የሚገቡ ከሆነ በመሀል ሜዳ የመከላከል ባህሪ ካላቸው ሁለቱ የመቐለ አማካዮች የሚኖረው ፍልሚያ እና ቡድኑ የመቐለን ረጃጅም ኳስ ለመመከት ያለው አቅም የጨዋታውን ውጤት ሊወስኑ ከሚችሉ ነጥቦች እንደሚሆኑ ይገመታል። ሆኖም ሰበታዎች በአጨዋወቱ ወሳኝ ሚና ያለው አማካዩ ዳዊት እስጢፋኖስ በጉዳት ማጣታቸው ለቡድኑ መጥፎ ዜና ነው።

አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከዳዊት በተጨማሪ አስቻለው ግርማ፣ በኃይሉ አሰፋ እና ሳቪዮ ካቩጎን በጉዳት አያሰልፉም። በተቃራኒው አንተነህ ተስፋዬ ከረጅም ጊዜ ጉዳት በኃላ ወደ ሜዳ ተመልሷል።

ግምታዊ አሰላለፍ

መቐለ 70 እንደርታ (4-4-2)

ፊሊፕ ኦቮኖ

ሥዩም ተስፋዬ – አሌክስ ተሰማ – ላውረንስ ኤድዋርድ – አንተነህ ገብረክርስቶስ

ዮናስ ገረመው – ሙልጌታ ወልደጊዮርጊስ – ዳንኤል ደምሴ – ያሬድ ከበደ

አማኑኤል ገብረሚካኤል – ኦኪኪ ኦፎላቢ

ሰበታ ከተማ (4-3-3)

ዳንኤል አጃይ

ጌቱ ኃይለማርያም – አዲስ ተስፋዬ – ወንድይፍራው ጌታሁን – ኃይለሚካኤል አደፍርስ

መስዑድ መሐመድ – ደሳለኝ ደባሽ – ታደለ መንገሻ

ሲይላ ዓሊ ባድራ – ፍፁም ገብረማርያም – ባኑ ዲያዋራ


© ሶከር ኢትዮጵያ