መከላከያ በሜዳው ተሸንፎ የማለፍ ተስፋውን አጨልሟል

በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳታፊ የሆነው መከላከያ በቅድመ ማጣርያው የመጀመርያ ጨዋታ የግብፁ ምስር አል ማቃሳን አስተናግዶ 3-1 ተሸንፏል፡፡ ወደ 1ኛው ዙር ለማለፍ ያለውን እድልም አጣብቂኝ ውስጥ ከቷል፡፡

ምስር አል ማቃሳዎች ቀዳሚ ግባቸውን ለማስቆጠር የፈጀባቸው ከ10 ያነሰ ደቂቃ ብቻ ነበር፡፡ የመከላከያ ተከላካዮች እና ግብ ጠባቂውን አለመግባባት ተጠቅሞ በ9ኛው ደቂቃ ግብ ያስቆጠረው ሁሴን ራጋብ ነው፡፡ ግቧ ከተቆጠረች በኋላ ፍሬው ሰለሞን መከላከያን አቻ የምታደርግ መልካም የግብ የማስቆጠር አጋጣሚ ቢያገኝም ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡ በ21ኛው ደቂቃ ኦማር መሃመድ በረካት ከመስመር የተነሳውን ኳስ ከቡድን አጋሩ ጋር አንድ ሁለት በመቀባበል ወደ ግብነት ቀይሮ የአል ማቃሳን መሪነት ወደ ሁለት አስፍቷል፡፡ የመጀመርያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የተጠናቀቀውም በግብፁ ክለብ 2-0 መሪነት ነበር፡፡

ከእረፍት መልስ መከላከያ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ሲያደርጉ ምስር አል ማቃሳዎች ከመጀመርያው አጋማሽ የቀዘቀዘ እንቅስቃሴ አሳይተዋል፡፡ በ55ኛው ደቂቃ ባዬ ከግብ ጠባቂው ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ያመከነው ኳስ ከመከላከያ የምትጠቀስ የግብ ሙከራ ነበረች፡፡

በ86ኛው ደቂቃ ሃምዲ ኤል ሰኢድ የማቃሳን 3ኛ ግብ ከመስመር ተነስቶ በግሩም ሁኔታ ከመረብ ማሳረፍ ችሏል፡፡ ግቧ ከተቆጠረች በኋላ ብዙም ሳይቆይ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው መሃመድ ናስር የግል ጥረቱን ተጠቅሞ መከላከያን በባዶ ከመሸነፍ በቀር ፋይዳ ያልነበራትን ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡ ጨዋታውም በምስር አል ማቃሳ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

በጨዋታው መከላከያ ከተጠበቀው እጅግ የወረደ እንቅስቃሴ ያሳየ ሲሆን የምስር አል ማቃሳ ፈጣን አጀማመር እና የተጫዋቾቹ ልምድ ለአሸናፊነታቸው ከፍተኛውን አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡

የመልሱ ጨዋታ ከ15 ቀን በኋላ በግብጽ ሲካሄድ መከላከያ ወደ ተከታዩ ዙር የማለፍ ጠባብ እድልን ይዞ ወደ ስፍራው ያመራል፡፡

ያጋሩ