ሪፖርት | ስሑል ሽረዎች ሦስተኛ ተከታታይ ድላቸውን አስመዘገቡ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 9ኛ ሳምንት ዛሬ በተደረገ አንድ ጨዋታ ሲጀመር ስሑል ሽረዎች ከጨዋታ ብልጫ ጋር ፋሲል ከነማን 2-0 በማሸነፍ የመሪዎቹን ተርታ ተቀላቅለዋል።

ስሑል ሽረዎች ባለፈው ሳምንት ወላይታ ድቻን ካሸነፈው ስብስብ ሸዊት ዮሐንስ፣ ክብሮም ብርሀነ እና በረከት ተሰማን በአዳም ማሳላቺ፣ ዓወት ገብረሚካኤል እና ዓብዱልለጢፍ መሐመድ ተክተው ሲገቡ ዐፄዎቹ ኢትዮጵያ ቡናን ካሸነፈው ስብስብ ምንም ለውጥ ሳያደርጉ ነበር ወደ ሜዳ የገቡት።

በጨዋታው ስሑል ሽረዎች የተለመደው የመልሶ ማጥቃት አጨዋወታቸውን ይዘው ሲገቡ ዐፄዎቹ ኳስን ተቆጣጥሮ ለመጫወት ጥረት አድርገዋል። ሆኖም በአጨዋወቱ ንፁህ የግብ ዕድል መፍጠር አልቻሉም።

የተሳካ የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ለመተግበር ያልተቸገሩት ባለሜዳዎች በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች በጨዋታው ጥሩ ከነበረው ያስር ሙገርዋ የግል ጥረት በርከታ ዕድሎች ፈጥረዋል። አማካዩ በመልሶ ማጥቃት የመጣውን ኳስ መጥቶ የግቡን ቋሚ ገጭቶ የተመለሰበት እና በድጋሚ በሳጥን ውስጥ ለሳሊፍ አቀብሎት አጥቂው ያመከነው ወርቃማ ዕድል ለግብ የቀረቡ ነበሩ። ሽረዎች ከተጠቀሰው ሙከራ ውጭም በያሳር ሙገርዋ እና በሳሊፍ ፎፋና ሙከራዎች አድርገዋል።

በጨዋታው ጥሩ አጀማመር አድርገው የነበሩት ሆኖም ኋላ ላይ የተጋጣሚን የመልሶ ማጥቃት ለመቋቋም የተቸገሩት ዐፄዎቹ በተጫዋቾች ግል ጥረት ከፈጠሯቸው ዕድሎች ውጭ እንደ ቡድን አመርቂ እንቅስቃሴ ማድረግ አልቻሉም። በዚህም በሙጂብ ቃሲም ፣ በዛብህ መለዮ እና ሱራፌል ዳኛቸው ሙከራዎች አድርገዋል። የሁለቱ አማካዮች ሙከራ ከረጅም ርቀት የተደረጉ ሙከራዎች ሲሆን ሙጂብ ቃሲም የሞከራት ሙከራ ግን እጅግ ለግብ የተቃረበች ነበረች።
አጥቂው በተከላካዮች ትኩረት ማጣት ያገኛትን ኳስ መትቶ የግቡን አግዳሚ መልሶበታል።

እንደመጀመርያው አጋማሽ ሁሉ የባለሜዳዎቹ አጠቃላይ ብልጫ በታየበት አጋማሽ ዐፄዎቹ ሁለት ቅያሬዎች ካደረጉ በኃላ የተሻለ ተንቀሳቅሰዋል። በተለይም ተቀይሮ የገባው ጋብርኤል አሕመድ የቡድኑ ሚዛን በመጠበቅ ረገድ ጥሩ ሚና ነበረው።

ዓብዱልለጢፍ መሐመድ በመስመር ሰብሮ በመግባት ለሳሊፍ ፎፋና አቀብሎት አጥቂው ባመከነው ሙከራ ጥቃታቸው የጀመሩት ስሑል ሽረዎች በመልሶ ማጥቃት በርካታ ዕድሎች ፈጥረዋል። ከነዚህም ሳሊፍ ፎፋና እና ዲድየ ለብሪ አንድ ሁለት ተቀባብለው ዲድየ ለብሪ መቶ ሚካኤል ሳማኪ በሚያስደንቅ ብቃት ያወጣው ሙከራ እና ዲድየ ሌብሪ በመስመር ገብቶ አሻግሮት አለምብርሀን ይግዛው የመለሰው ኳስ ይጠቀሳሉ።

በሁለተኛው አጋማሽ የተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ያሳዩት ዐፄዎቹም ተቀይሮ በገባው ኢዙ አዙካ እና ሙጂብ ቃሲም ሙከራዎች አድርገዋል። በተለይም ዓለምብርሀን ይግዛው ከመስመር አሻምቷት ሙጂብ ቃሲም በግምባሩ ጨርፏት የወጣችው ኳስ ፋሲሎችን መሪ ለማድረግ ተቃርባ ነበር። በኢዙ አዙካ በሁለት አጋጣሚዎች ከርቀት ሙከራ አድርገውም የቀድሞ ግብ ጠባቂያቸው ምንተስኖት አሎ መልሶባቸዋል።

በመጨረሻዎቹ የጨዋታው ደቂቃዎች ሽረዎች ድል ያስመዘገቡባቸውን ጎሎች ማግኘት ችለዋል። በዚህም በሰማንያ ሰባተኛው ደቂቃ ከረጅም ርቀት የተሻማውን ኳስ ሚካኤል ሳማኪ በሚመልስበት ወቅት በሳሊፍ ፎፋና ተነክቶበት ወደ ግብነት ተቀይሯል። ከደቂቃዎች በኃላም (በተጨማሪ ደቂቃ) ዓብዱልለጢፍ መሐመድ ከመስመር ሰብሮ ገብቶ ግብ በማስቆጠር የቡድኑን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችሏል። ጨዋተውም በሽረ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ ተከታታይ ሦስተኛ ድላቸውን ያሳኩት ስሑል ሽረዎች ነጥባቸውን 15 በማድረስ ደረጃቸውን ሲያሻሽሉ ፋሲል ከነማዎች ባሉበት 15 ነጥብ ረግተዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ