ቅድመ ዳሰሳ | ሀዲያ ሆሳዕና ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

በ9ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከሰመመን የነቃው ሀዲያ ሆሳዕና በአቢዮ ኤርሳሞ በሊጉ ወጥ አቋም ማሳየት የተሳነው ቅዱስ ጊዮርጊስን የሚያስተናግድበት ጨዋታን በተከታዩ መልኩ ዳሰነዋል።

ከአስከፊ የሊጉ ጅማሮ ማግስት ተከታታይ ሁለት ጨዋታዎችን ድል ማድረግ የቻሉት በአሰልጣኝ ግርማ ታደሰ የሚመሩት ሆሳዕናዎች በዚህኛው ጨዋታ ድል ማድረግ የሚችሉ ከሆነ ለሳምንታት ተሰንቅረውበት ከነበረው የወራጅ ቀጠና ውስጥ መውጣት የሚችሉበትን አጋጣሚ መፍጠር ይችላሉ።

የሀዲያ ሆሳዕና ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
አሸነፈ አሸነፈ ተሸነፈ አቻ ተሸነፈ

ሀዲያ ሆሳዕናዎች ለወትሮው የሚጠቀሙበት በረጃጅም ተሻጋሪ ኳሶች ላይ የተመሠረተው የማጥቃት ሂደታቸው በአየር ኳስን በማሸነፍ ረገድ ውጤታማ ለመሆን በማይቸገሩት የቅዱስ ጊዮርጊሶች የተከላካይ መስመር ተሰላፊዎች እንደሚፈተን ይጠበቃል። ከዚህም የተነሳ የቡድኑ የማጥቃት ሂደት መሀል ለመሀል ሰብሮ ለመግባት በሚደረግ ጥረት ይቃኛልም ተብሎ ይገመታል።

በነገው ጨዋታ ሀዲያ ሆሳዕናዎች የአምበላቸው ሄኖክ አርፊጮ እና አጥቂው መሀመድ ናስርን ግልጋሎት ዳግም ሲያገኙ በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጡት ተጫዋች አይኖርም።

የቅዱስ ጊዮርጊስ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
አሸነፈ አቻ አሸነፈ ተሸነፈ አቻ

ባለፈው ሳምንት ወደ ድል የተመለሱት ፈረሰኞቹ የዓመቱን የመጀመርያ የሜዳ ውጪ ድል በማሳካት ወደ ሠንጠረዡ አናት ለመጠጋት አልመው ወደ ሜዳ ይገባሉ።

ጊዮርጊሶች ያለ ወሳኙ ግብ አዳኛቸው ሰልሀዲን ሰዒድ በሚያደርጉት በዚሁ ጨዋታ ላይ በተለይ ከሜዳቸው ውጪ በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ላይ እጅጉን ሲቸገሩ የሚስተዋል ቢሆንም ከክለቡ አመራሮች በቅርብ ማስጠንቀቂያ የደረሳቸው የክለቡ የአሰልጣኞች ቡድን እንዲሁም ተጫዋቾች የውድድር ዘመናቸውን መልክ ለማስያዝ መሰል የሜዳ ውጭ ጨዋታዎች ላይ ነጥቦችን ማስመዝገብ የግድ ይላቸዋል።

ከመሪው መቐለ በ3 ነጥብ አንሰው በ13 ነጥብ ሊጉን በ4ኛ ደረጃ ላይ በመቀመጥ ከመሪዎቹ ተርታ መሰለፍ የቻሉት ፈረሰኞቹ በነገው ጨዋታ ከወገብ በላይ እየተሻሻለ ባለው ቡድናቸው ውጤት ይዘው ለመውጣት ጥረት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። በተለይም ከጋዲሳ መብራቴ እና አቤል ያለው መነሻነ የሚደረጉ ጥቃቶች በሦስት የመሐል ተከላካዮች የሚገባውና በመከላከል እንቅስቃሴ ወደ አምስት ከፍ ከሚለው የሆሳዕና የኋላ ክፍል ጋር የሚኖራቸው ፍልሚያ ውጤቱን የመወሰን አቅም ይኖረዋል። በጥሩ አቋም ላይ የሚገኘው ጌታነህ ከበደ ጉዳት እንደተፈራው አለመሆንና ነገ ግልጋሎት የሚሰጥ መሆኑ ለጊዮርጊስ የምስራች የሚሆን ነው።

ባሳለፍነው ሳምንት በድጋሚ ጉዳት ያስተናገደው ሰልሀዲን ሰዒድን ጨምሮ ረዘም ያለ ጊዜ ጉዳት ላይ የሚገኙትን ናትናኤል ዘለቀ እና ለዓለም ብርሃኑ ከቡድኑ ጋር ወደ ሆሳዕና አልተጓዙም።

እርስበርስ ግንኙነት

ከዚህ ቀደም ሁለት ጊዜ በሊጉ ተገናኝተው ሁለቱንም ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ በተመሳሳይ 2-0 ውጤት አሸንፏል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሀዲያ ሆሳዕና (3-5-2)

አቤር ኦቮኖ

ደስታ ጊቻሞ – አዩብ በቀታ – ፀጋሰው ዲላሞ

ሱራፌል ዳንኤል – አብዱልሰመድ ዓሊ – ይሁን እንደሻው- አፈወርቅ ኃይሉ – ሄኖክ አርፊጮ

ቢስማርክ አፒያ – ቢስማርክ ኦፖንግ

ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-4-2)

ባህሩ ነጋሽ

ደስታ ደሙ – አስቻለው ታመነ – ኤድዊን ፍሪምፖንግ – ሄኖክ አዱኛ

ጋዲሳ መብራቴ – ሙሉዓለም መስፍን – ሀይደር ሸረፋ – አቤል ያለው

ጌታነህ ከበደ – ዛቦ ቴጎይ


© ሶከር ኢትዮጵያ