ቅድመ ዳሰሳ | ባህር ዳር ከተማ ከ ወልዋሎ

በነገው ዕለት ከሚደረጉት ጨዋታዎች መካከል የጣና ሞገዶቹ ቢጫ ለባሾቹን የሚያስተናግዱበት ጨዋታን እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

በሜዳቸው ጠንካራ ከሆኑ ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው ባህር ዳር ከተማ የሜዳ ላይ ድንቅ ግስጋሴውን ለማስቀጠል እና ወደ ደረጃ ሰንጠረዡ አናት ለመጠጋት ወደ ሜዳ ይገባል።

የባህር ዳር ከተማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
ተሸነፈ አሸነፈ ተሸነፈ አቻ አሸነፈ

 

በሜዳቸው ሲጫወቱ ኳስን ለመቆጣጠር የሚጥሩትና በፈጣን ጥቃቶች ጎሎች ለማስቆጠር የማይቸገሩት የጣናው ሞገድ ተጨዋቾች በነገውም ጨዋታም ከባለፉት ጨዋታዎች የተለየ አቀራረብ ይኖራቸዋል ተብሎ አይጠበቅም። ከዚህ በተጨማሪ ተጋጣሚያቸው ከኳስ ቁጥጥር ይልቅ ለረጃጅም ኳሶች ቅድምያ ሰጥቶ እና በመልሶ የሚጫወት ቡድን እንደመሆኑ አብዛኞቹ በኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወስደው ለመጫወት የሚመርጡ ቡድኖች እንደሚገጥማቸው ፈጣን መልሶ ማጥቃት የመቋቋም ፈተና እና ቶሎ ወደ የመከላከል ቅርፅ አለመያዝ ችግሮችን ፈትተው ወደ ሜዳ መግባት ግድ ይላቸዋል።

በዚህ ጨዋታ ከጉዳት አገግሞ ልምምድ የጀመረው የአማካይ መስመር ተጨዋቹ ፍፁም ዓለሙ ወደ ራሱ ሳጥን አፈግፍጎ እና ጥቅጥቅ ብሎ የሚከላከለው ወልዋሎን ለማስከፈት ወሳኝ የማጥቃት ሚና ይሰጠዋል ተብሎ ይገመታል።

ለነገው ጨዋታ አቤል ውዱ እና ወሰኑ ዓሊ ከስብስቡ ውጪ ሲሆኑ ፍፁም ዓለሙ ወደ ሜዳ ተመልሶላቸዋል።

የወልዋሎ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
ተሸነፈ አሸነፈ አቻ ተሸነፈ አቻ

 

በቆሙ ኳሶች አጠቃቀም እየተሻሻሉ የመጡት የጣናው ሞገዶች በነገው ጨዋታም ከመዓዘን፣ ከተሻጋሪ እና ከቅጣት የሚሻሙ ኳሶችን እንደ ሁለተኛ የጎል ማግኛ መንገዳቸው ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

በተጫዋቾች ምርጫና እና በአንዳንድ ታክቲካዊ ውሳኔዎቻቸው ምክንያት ለመገመት የሚከብድ ቡድን የሰሩት አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ በባለፉት ጨዋታዎች የተለያየ አቀራረባቸው ምክንያት የነገው አቀራረባቸው ለመገመት አዳጋች ነው።
ሆኖም አሰልጣኙ ሌሎች ያልተጠበቁ ውሳኔዎች ሲወስኑም የማይቀይሩት የረጅም ኳስ አጨዋወታቸው በነገው ጨዋታም ይቀይራሉ ተብሎ አይጠብቅም።

ቢጫ ለባሾቹ በነገው ዕለት ዓይናለም ኃይሌ እና ካርሎስ ዳምጠው በጉዳት ሲያጡ አቼምፖንግ አሞስ ከጉዳት ተመልሶላቸዋል። ግብ ጠባቂው አብዱልዓዚዝ ኬይታም ቅጣቱን ጨርሶ ተመልሷል።

እርስ በርስ ግንኙነት 

በሊጉ ሁለት ጊዜ ተገናኝተው ባህር ዳር ላይ ያለ ጎል አቻ ሲለያዩ መቐለ ላይ ወልዋሎ 1-0 አሸንፏል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ባህር ዳር ከተማ (4-3-3)

ሀሪሰን ሄሱ

ሳላምላክ ተገኝ – አዳማ ሲሶኮ – ሰለሞን ወዴሳ – ሚኪያስ ግርማ

ዳንኤል ኃይሉ – ፍቅረሚካኤል ዓለሙ – ፍፁም ዓለሙ

ዜናው ፈረደ – ማማዱ ሲዲቤ – ግርማ ዲሳሳ

ወልዋሎ (4-2-3-1)

አብዱላዚዝ ኬይታ

ምስጋናው ወልደዮሐንስ – ገናናው ረጋሳ – ሳሙኤል ዮሐንስ – ሄኖክ መርሹ

ፍቃዱ ደነቀ – ጠዓመ ወልደኪሮስ

ሰመረ ሀፍታይ – ራምኬል ሎክ – ኢታሙና ኬሙይኔ

ጁንያስ ናንጂቡ


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ