አሰልጣኝ መሠረት ማኒ ስለተበረከላት ሽልማት እና ከሊዮን ክለብ ጋር ስለፈጠረችው ግንኙነት ትናገራለች

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ሥማቸው ከፍ ብሎ ከሚጠሩ እንስት አሰልጣኞች አንዷ የሆነችው አሰልጣኝ መሠረት ማኔ በፈረንሳይዋ ሊዮን ከተማ በተዘጋጀ ሥነ-ስርዓት ሆርን ኦፍ አፍሪካ ከተባለ ተቋም ሽልማት ተበርክቶላታል። አሰልጣኟም ስለ ሽልማቱ እና ከሊዮን እግር ኳስ ክለብ ጋር ስላደረገችው ግንኙነት ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጋለች።


ስለ ሽልማቱ እናውራ፤ የተሰጠሽ ሽልማትስ ምንድን ነው?

ሆርን ኦፍ አፍሪካ የተባለ ተቋም የሚያዘጋጀውና ትልቅ ሥራ ለሰሩ ባለሙያዎች የሚሰጠው ሽልማት ነው፡፡ መድረኩ ላይ የተገለፀው እኔ ይሄን ስወስድ ሁለተኛ ተሸላሚ እንደሆንኩኝ ነው፡፡ ከዚህ በፊት አንድ ሰው ተሸልሟል፡፡ (ማን እንደሆነ አላወቅኹም) መድረኩ ላይ ሲወራ ነበር የሰማሁት፤ ሽልማቱ ይሄ ነው፡፡

ሽልማቱን የሰጠሽ ድርጅት ምንድን ላይ ነው የሚሰራው? ከእግር ኳሱ ጋርስ ግንኙነት አለው?

ድርጅቱ በአብዛኛው ድጋፍ ላይ ትኩረት የሚያደርግ ነው። ኢትዮጵያ ላይ ለትምህርት ቤት መፅሐፍ መርዳት፣ ግንባታዎችን ማከናወን፣ ህንፃ እና የዕርዳታ ተቋማት ሲገነቡ ለነሱ አስተዋጽኦ ማድረግ እንዲሁም ማኅበራዊ ችግሮች ላይ በደንብ የሚሳተፍ ተቋም ነው፡፡

ተቋሙ ለአንቺ ሽልማት አበርክቶልሻል። ለሽልማት ያበቃሽ ምንድነው?

ለሌሎች አርዓያ መሆን የሚያስችሉ ሥራዎችን በመስራቴ ነው። በእግር ኳስም ሆነ ከእግርኳስ ውጪ በርካታ ሥራ ሰርቻለሁ፤ በዛም ስኬታማ ነኝ። መፅሀፌ ላይ በአብዛኛው ተገልጿል። በእግርኳስ በአፍሪካ የመጀመሪያ ሴት አሰልጣኝ ነኝ፤ ወንዶችን ያሰለጠንኩ። ከብሔራዊ ሊግ ወደ ፕሪምየር ሊግ ያሳደኩ ሁለተኛ ሴት ነኝ። ሴት ሆኜ አካዳሚ የከፈትኩ፤ ይሄ በየትኛውም ቦታ የለም። የተሻለ ሥራን ለሀገራችን ሊሰሩ የሚችሉ ተስፋ ያላቸው ታዳጊዎች ያሉበት፤ ሀገርን የሚጠቅሙ ልጆችን የሚያፈራ ይሄ የኔ አካዳሚ ነው፡፡ ለገንዘብ አይደለም የምንሰራው፤ በነፃ ነው። ከዛ በተረፈ በሴትነቴ እና በሥራ ግንኙነቴ ውስጥ ብዙ ያሳካዋቸው ትልልቅ ነገሮች አሉ። ድሬዳዋ ላይ በሰርከሱ፣ በቲያትሩ፤ ከዛም አልፎ ወጣቶችን በማደራጀት ለተሻለ አላማ እንዲዘጋጁ ማድረግ፤ ስብዕናቸውን ከፍ በማድረግ ስኬታማ እንዲሆኑ ከመርዳት አንፃር በርካታ ሥራዎችን ሰርቻለሁ። እነኚህን ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው የተሸለምኩት።

ሽልማቱ ሲበረከትልሽ ምን ተሰማሽ ?

በእውነት እኔ አልጠበኩትም፤ ምንም የሰማሁትም ነገርም አልነበረም። በአጋጣሚ እዚሁ ነበርኩ። ከዚህ በፊት በፕሮግራም ነበር የምንቀሳቀሰው፤ ፕሮግራም ተይዞልኝ መቼ በምን ሰዓት የት ቦታ እንደምሄድ ይነገረኝ ነበር። እዚህ ፕሮግራም ላይ ሲሆን ግን ምንም አልጠበኩም። ንግግር እንደማደርግ ብቻ ነበረ የተነገረኝ፤ ለንግግሩ ነበር ስዘጋጅም የነበረው። የመጣሁበትን አላማ እና የሰራዋቸውን ነገሮች፤ ይህን ፕሮግራም ያዘጋጁት አካላት እዛም መጥተው አካዳሚውን እንዲደግፉ እውቅና ሰርተፍኬት ለመስጠት ከዚህ አዘጋጅቼ ይዤ ሄጄ ነበር። ለማመስገን ነበር የሄድኩት። እነሱ ግን ይሄን አስበው ሲፈፅሙልኝ ውስጤን ነበር የወረረኝ። በጣም ደስ ብሎኛል። ከሰራን የተሻለ ደረጃ እንደምንደርስ ነው የማየው። ብዙ ኃላፊነት ይጠበቅብኛል፤ ከአሁን በኃላ ብዙ መስራት አለብኝ። እንድበረታታ አድርጎኛል። ጥሩ ስሜት ሰጥቶኛል። ኢትዮጵያን በዚህ ከፍ በማድረጌም ደስታ ተሰምቶኛል፡፡

ከሽልማቱ በኃላ መልዕክት አስተላልፈሽ ነበር። ምን ነበር ?

ዋና የሄድኩበትም አላማ ይሄ ነው (መልዕክት ማስተላለፍ)። አንደኛ በሴቶች እግር ኳስ ላይ እየሰራሁ እንደመሆኔ የፈረንሳዩ ሊዮን ክለብ ደግሞ የአውሮፓ ሻምፒዮን ቡድን ነው። ስለዚህ ወደ ኢትዮጵያ ቢመጡ የተሻሉ ተጫዋቾችን ማግኘት እንደሚችሉ ተናሬያለሁ። ኢትዮጵያ መጥተው እንዲያዩ የሴቶቹንም ሊግ እንዲጎበኙ ጋብዣለሁ። ሎዛ አበራ በውጪ እየተጫወተች ነው። እሷንም እንዲያዩዋት ዕድሉ ከተገኘ እዛ ሄዳ የምትጫወትበትን ዕድሎች እንዲፈጥሩ መልዕክት አስተላልፌያለሁ። በተለይ የነሱ ውድድር ሲያልቅ ወደዚህ የሚመጡበትን ሁኔታ ለማመቻቸት አቅጃለሁ፤ እነሱም ለመምጣት ፍቃደኞች ናቸው፡፡ ድጋፍ ያስፈልገናል።

ሊዮን ከተማ ከዚህ በፊትም ከድሬዳዋ ከተማ ጋር የእህትማማችነት ግንኙነት አላቸው። በፖለቲካ እና በማህበራዊ ሁኔታው እንዲሁም በሌሎች ይገናኛሉ። በስፖርት ደግሞ ከመሲ ድሬ እግር ኳስ አካዳሚ ጋር በመሆን ልጆች በልጅነታቸው የተሻለ ምልመላ ተደርጎ ወደ ሊዮን የሚሄዱበትን እድል ማመቻቸት፤ እዛ ያሉ አሰልጣኞች መጥተው እዚህ ስልጠና የሚሰጡበት ያላቸውንም ልምድ የሚያካፍሉበት እድል እንዲመቻች ጠይቄያለሁ። የኛ መሰረታዊ ችግሮች ደግሞ እነኚህ ናቸው። ጥሩ አሰልጣኝ ካለ ጥሩ እግር ኳስ ይኖረናል። ጥሩ እና የጠሩ በእውቀት የዳበሩ አሰልጣኞች ባሉን ቁጥር ኳሳችን እንደሚያድግ ስለማምን እሱ ላይ በደንብ ነው ከአምባሳደሩም ጋር የተነጋገርነው። አምባሳደሩም በጣም ደስተኛ ናቸው፡፡ ከሁሉም በላይ ፍላጎት ያለው ሰው ነው። እነኚህን ነገሮች አስቀምጨለታለሁ። ወደ ፅሁፍም እንድንቀይረው ነግረውኛል። በቀጣይ ጥሩ ነገሮች ይኖራሉ ብዬ አምናለሁ። የኛ በርትቶ መስራት ግን ያስፈልጋል። እዚህ እኔ የጀመርኳቸው ነገሮች አሉ። እግር ኳሱ የሚመለከታቸው ደግሞ ከኮሚሽን ቢሮ ጀምሮ ያለውን በሙሉ እነግራቸዋለሁ። ግንኙነትም ፈጥርላቸዋለሁ። ስለዚህ በቀጣይ ከፈጣሪ ጋር የተሻለ ነገር ይኖራል ብዬ አስባለሁ፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ